የጀርመን ጦር ከቱርክ መዉጣት | ዓለም | DW | 06.06.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የጀርመን ጦር ከቱርክ መዉጣት

ቱርኮች የስደተኞች ጉዳይ ዉልን ለመሠረዝ ዝተዉም ነበር።የጀርመን የምክር ቤት እንደራሴዎች ኢንችርሊክ-ቱርክ የሠፈረዉን የጀርመን ጦር እንዳይጎበኙ አገዱ።ጀርመኖች እገዳዉን ለማስነሳት እንደማባበልም፤ እንደማስፈራራትም፤እንደመደራደርም ሞካክረዉ ነበር።የቱርኮች መልስ፤- ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሩ ትናንት እንዳሉት «ሳትሰጡ-አንሰጥም» አይነት ነዉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:50

የጀርመን ጦር ከቱርክ መዉጣት

አሸባሪዎችን ለመወጋት ቱርክ ዉስጥ የሠፈረዉ የጀርመን ጦር ከቱርክ እንዲወጣ የሁለቱ ሐገራት ባለሥልጣናት ወሰኑ።ቱርክ ጦርዋን ከቱርክ የምታስወጣዉ የጀርመን የምክር ቤት አባላት ጦሩን እንዳይጎበኙ የቱርክ መንግስት በመከልከሉ ነዉ።ቱርክ እርምጃዉን የወሰደችዉ የጀርመን ምክር ቤት የቱርክን ሉዓላዊነት የሚፃረር ዉሳኔ አሳልፏል፤ መንግሥትን በኃይል ለማስወገድ ላሴሩ ቱርካዉያን ድጋፍ ሰጥቷል በሚል ምክንያት ነዉ።የአንካራና የበርሊን ግንኙነት ቢሻክርም የጀርመንን ጦር ሥርዓት ተክትሎ እንዲወጣ ከቱርክ ባለሥልጣናት ጋር መስማማታቸዉን የጀርመን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አስታዉቀዋል።ነጋሽ መሐመድ ዝርዝር ዘገባ አለዉ።

የልዩነቱ ምክንያት እንደ ወዳጅነቱ ሁሉ፤ ዉስብስብ ነዉ።ጥቅም፤ መጠላለፍና ሴራ፤የተደበቀ ንቀትና ጥላቻ ከዉስጥ የሚገፋዉ ብዙ ነዉ።አደባባይ የወጣዉ ግን ከሰወስት አይበልጥም።ቱርክ ገሚስ ዓለምን ያስከበረ ክንዷ በዛለበት በ20ኛዉ መቶ-ክፍለ ዘመን መጀመሪያ በአርመኖች ላይ አድርሳዋለች የሚባለዉን በደል የጀርመን ምክር ቤት «የዘር-ማጥፋት ወንጀል» ብሎ መፈረጁ አንዱ ነዉ።
የፕሬዝደንት ሬጀብ ጠይብ ኤርዶኻንን መንግሥት በኃይል ለማስወገድ አሲረዋል ለሚባሉ 450 የቱርክ የቀድሞ ጦር ሠራዊት አባላት፤ዲፕሎማቶችና ጠበቆች ጀርመን ከለላ መስጠትዋ-ሁለት።ቱርክና ምዕራባዉያን አሸባሪ በሚሉት በኩርድ ሠራተኞች ፓርቲ (PKK) ላይ የጀርመን መንግሥት ጠንካራ

እርምጃ አልወሰደም የሚለዉ ወቀሳ-ያሰልሳል።
ለቱርክ የአዉሮጳ ሕብረት አባልነት ጥያቄ  ጀርመኖች ጀርባቸዉን መስጠታቸዉ፤ የቱርክ ባለሥልጣናት ጀርመን ለሚኖሩ ቱርካዉያን የሚያደርጉትን የምርጫ ቅስቀሳ የጀርመን ሹማምንት በሰበብ አስባቡ ማደነቃቀፋቸዉ፤ የጀርመን መገናኛ ዘዴዎች ፌዝ፤ዘለፋና የሰብአዊ መብት ጥሰት ወቀሳ አንካራዎችን እስከ ተራ ስድብ ለደረሰ አፀፋ ሳይገፋፋ አልቀረም።

አንካራዎች ካንዴም ሁለቴ የጀርመን መሪዎችን ተሳደቡ።የጀርመን እና የቱርክ ጥምር ዜግነት ያለዉን ጋዜጠኛ አሠሩ።ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሜቭሉት ካቩሶግሉ ትናንት እንዳሉት ግን ጋዜጠኛ ዴኒስ ዩቼል የታሰረዉ ጋዜጠኛ በመሆኑ አይደለም።«ምክንያቱን ጀርመንም በትክክል ታዉቀዋለች።ዴኒስ ዩቼል የታሰራዉ በጋዜጠኝነት ሥራዉ አይደለም።በአሸባሪነት ተጠርጥሮ ነዉ።አሸባሪነት ለኛ በጣም ጥንቃቄ የሚጠይቅ ጉዳይ ነዉ።» 

ቱርኮች የስደተኞች ጉዳይ ዉልን ለመሠረዝ ዝተዉም ነበር።አልበቃቸዉም።የጀርመን የምክር ቤት እንደራሴዎች ኢንችርሊክ-ቱርክ የሠፈረዉን የጀርመን ጦር እንዳይጎበኙ አገዱ።ጀርመኖች እገዳዉን ለማስነሳት እንደማባበልም፤ እንደማስፈራራትም፤እንደመደራደርም ሞካክረዉ ነበር።የቱርኮች መልስ፤- ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሩ ትናንት እንዳሉት «ሳትሰጡ-አንሰጥም» አይነት ነዉ።
                                 
«ኮኒያ የሚገኘዉን የኔቶ አየር ኃይል ሠፈር እንዲገበኙ ፈቅደናል።ከኮንያ እንጀምር።ከዚያ በኋላ ሁኔታዉ ሲሻሻል፤ ወደነበረበት ሲመለስ፤ ሁለቱ ወገኖች ስንቀራረብ ኢንሽርሊክን መጎብኘት ይቻል ይሆናል።ግን ባንድ

ወገን ብቻ አይሰራም።ሁለቱም ወገን እንጂ።» ጀርመኖች ጦራቸዉን ከቱርክ ነቅለዉ ዮርዳኖስ ለማስፈር ወሰኑ።የጀርመኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር  ዚግማር ጋብርኤል እንዳረጋገጡት ሁለቱ ወገኖች ላለመስማማት ተስማሙ።
                             
«የቱርኩ ባልደረባዬ እንደገለፁልኝ፤ ቱርክ ባሁኑ ወቅት እያንዳዱ የጀርመን ምክር ቤት አባል ኢንሽርሊክን እንዲጎበኝ መፍቀድ አይቻላትም።ምክንያቱ የዉስጥ ፖለቲካ ነዉ።በዚሕ አዝናለሁ።በተቃራኒዉ ግን እኛም በዉስጥ ፖለቲካዊ ምክንያት ኢንችሊክ የሠፈሩት ወታደሮች ሌላ ሥፍራ መስፈር ያለባቸዉ መሆንን እንድትገነዘቡት እንፈልጋለን።»
ሶሪያ ያሸመቀዉን የኢራቅና የሶሪያ እስላማዊ መንግስት (ISIS)ን እንዲወጋ ጀርመን ኢንችሊክ ያሰፈረችዉ ጦር 260 አባላት አሉት።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ
 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች