የጀርመን የጦር መሣሪያ በየመን ጦርነት | ዓለም | DW | 27.02.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የጀርመን የጦር መሣሪያ በየመን ጦርነት

የጀርመን ኩባንያዎች የጦር መሣሪያዎችን ለሳውድ አረቢያ እና ለተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች የመሸጣቸው መረጃ እያነጋገረ ነው። DWን ጨምሮ በጀርመን እና በሌሎች የአውሮጳ ሃገራት ለሚገኙ መገናኛ ብዙኃን የሚሠሩ ጋዜጠኞች የተረባረቡበት የምርመራ ዘገባ ጀርመን ሠራሽ መሣሪያዎች በየመን ጦርነት መሳተፋቸውን ይዘረዝራል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:37

የምርመራ ጋዜጠኝነት ዘገባ

በደቡባዊ የመን ግዛት አዋራማ ጎዳና ላይ አንድ ወታደራዊ አጀብ ይጓዛል። በገላጣው ተሽከርካሪ ላይ የሱዳን ወታዳራዊ የደንብ ልብስ የለበሱ ወታደሮች ተጭነዋል።  አንዳንዶቹም በፈገግታ ተውጠው የድል ምልክት በጣታቸው ያሳያሉ። ጦር መሣሪያዎቻቸውንም ከፍ አድርገዋል። ሑቲ አማጺያንን ለመውጋት የመን ላይ የዘመተው የሳውድ አረቢያን ኃይል ለመደገፍ  በባብ ኧል ማንዳብ የባሕር ወሽመጥ አድርገው ከሱዳን የመጡ ቅጥረኛ ወታደሮች ናቸው። ከጎርጎሪዮሳዊው 2015 ዓ.ም ጀምሮ ጦርነቱ የመን ውስጥ በሺህዎች የሚገመቱ ሲቪሎችን ሕይወት ቀጥፏል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተ.መ.ድ.) በዘመኑ ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ የታየው የመን ውስጥ መሆኑን ያመለክታል። በሀገሪቱ በሚሊየን የሚገመቱ በተለይ ሕጻናት ለጠኔ ተዳርገዋል። 


ጀርመን ሠራሽ ጦር መሣሪያዎች


በጎርጎርጎሪዮሳዊው 2015ዓ,ም የአሶሲየትድ ፕረስ ዘጋቢ ከየመኗ የወደብ ከተማ አደን ላይ የቀረፀው ፊልም ያሳየው የሱዳን ቅጥረኛ ወታደሮችን ብቻ አልነበረም። ንብረትነታቸው የተባበረው አረብ ኤሜሬቶች የሆኑ ታንኮችንም ጭምር እንጂ። ታንኮቹ ዩናይትድ ስቴትስ እና ጀርመን ሠራሽ ናቸው። የጀርመኑ የመከላከያ መሣሪያ ፋብሪካ ዱዩናሚት ኖቤል የ81 ሚሊኒየን ዩሮ ምርቱን  የመን ውስጥ የእግረኛ ጦር የሚሰነዘረውን ጥቃት ለምትመራው ኤሜሬትስ የመላክ ፈቃዱን ከፌደራል መንግሥቱ ያገኘው የዛሬ 10 ዓመት ነው።
«የጀርመን የጦር መሣሪያ በየመን ጦርነት ውስጥ ገብቷል ወይ?» በሚል DW በሙኒኩ የፀጥታ ጉባኤ ላይ ጥያቄ ያቀረበላቸው የጀርመን የኤኮኖሚ ሚኒስትር ፒተር አልትማየር ፤
«የማውቀው ነገር የለም፤ በጥምር መንግሥታችን በቀጥታ እና ወዲያው በየመን ግጭት ውስጥ ጣልቃ ለገቡ ወገኖች  ወታደራዊ መሣሪያዎች እንዳይሸጡ እጅግ ገዳቢ መመሪያዎችን አውጥተናል። ይህ ተግባራዊ እየሆነ ነው፤ እሱን በተመለከተ አዲስ ነገር አልሰማሁም።» ነው ያሉት።
ሆኖም ግን እነዚህ እንደሳውድ አረቢ እና ኤሜሬትስ ያሉት ሃገራት ከጎርጎሪዮሳዊው 2015ዓ,ም ጀምሮ የጀርመንን የጦር መሣሪያዎች ሲሸምቱ ነበር።  የኤኮኖሚ ሚኒስትሩ ግን መሣሪያዎቹ ለጦርነት እንደሚውሉ አለማወቃቸውን ለማስረዳት ሞክረዋል። ሆኖም ግን የጀርመን የጦር መሣሪያ አምራች ኩባንያ ምርቶች ፎቶግራፎች እና የቪዲዮ ምስሎች በኢንተርኔት ማለትም በትዊተር፤ በዩቲዩብ እና በጉግል ኧርዝ ይገኛሉ። የጀርመን ጦር መሣሪያዎች ላይ ምርመራ ያካሄዱ ተንታኞች ጦር መሣሪያዎቹ በየመኑ ጦርነት በምድር፣ በአየር እና በባሕር መሳተፋቸውን የሚያሳዩ በርከት ያሉ መረጃዎችን አግኝተዋል። 


አሰብ፤ ለየመኑ ጦርነት ተልእኮ መንደርደሪያ


ሌላው የኤርትራዋ አሰብ ወደብ ለየመኑ ጦርነት የዘመቻ ጣቢያ ሆናለች። በየመን እና በአሰብ ወደብ መካከል ያለው ርቀት 60 ኪሎ ሜትር ብቻ ነው። ከዚህ ስፍራ የሚነሱት የአረብ ኤሜሬቶች የጦር መርከቦች ወደ አደን ወደብ በቀላሉ ፈጥነው መድረስ ይችላሉ። ቅጥረኛ ወታደሮችም በዚሁ ወደብ አማካኝነት ወደ የመን እንዲገቡ በኤሜሬቶች እና በኤርትራ መካከል ስምምነት መደረጉንም የተመድ አመልክቷል። ድርጅቱ በጎርጎሪዮሳዊው 2009 ዓ,ም በኤርትራው ፈላጭ ቆራጭ መንግሥት ላይ የጣለውን የመሣሪያ ማዕቀብ ጥሷል ሲልም ይተቻል። ለእገዳው ቁብ ያልሰጠችው ኤሜሬትስ ጀርመን ሠራሽ የጦር መርከቦቿን በአሰብ ወደብ ላይ ማንሳፈፏን የሳተላይት ፎቶዎች ያሳያሉ። ሮኬት የተጠመደባቸው የጦር መርከቦች ብሬመን በሚገኝ የጀርመን ኩባንያ የተሠሩ እና 65 ሜትር ርዝመት ያላቸው ናቸው። 


አልጃዚራ ቴሌቪዥን በጎርጎሪዮሳዊው 2017 ጥቅምት ወር ዘገባው ለወትሮ ቡና ታስተናግድ የነበረችው የየመኗ ሞካ ወደብ በሳውዲ መራሹ ጥምር ኃይል ቁጥጥር ሥር መቆየቷን አመልክቷል። በዚህ ወቅትም የጀርመን ብቻ ሳይሆኑ የተለያዩ አውሮጳ ሃገራት የጦር መሣሪያዎችም ለዚሁ ተግባር ውለዋል። ለአብነትም ሳውዲ የተጠቀመችበት እና በያዝነው ዓመት ጥር ወር ላይ የመን ውስጥ የተከሰከሰው ቶርኔዶ ተዋጊ ጀትን ይጠቀሳል። የተዋጊ ጀት ነዳጅ ይሞሉ የነበሩ የኤርበስ ምርቶችም እንዲሁ ጀርመን ሠራሽ አካላት የተገጠሙላቸው አውሮፕላኖች መሆናቸውንም ምርመራው አሳይቷል። እንዲህ ያሉ ምርቶች ለጦርነት በመዋላቸው ጀርመን በቀጥታ በጦር መሣሪያ ንግዱ ተሳትፋለች ማለት አይቻልም በሚል የሚከራከሩ አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ጀርመን ስልታዊ ተጓዳኝ አድርጋ ከምትወስዳቸው ሳውዲ እና አረብ ኤሜሬቶች ጋር መናገዷ በቀጥታ በየመን ጦርነት እጇን እንደከተተች ያስመስላታል በሚልም የሚተቹ አልጠፉም። የፌደራል ጀርመን ተጣማሪ መንግሥት በየመን ጦርነት ለሚሳተፉ ሃገራት የጦር መሣሪያ እንዳይሸጥ ቢደነግጉም የሳውዲው ጋዜጠኛ ጀማል ኻሾግጂ ኢስታንቡል ውስጥ እስከተገደለበት ጊዜል ድረስ ውሳኔው ተግባራዊ እንዳልሆነ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። ይህ እገዳም ቢሆን የፊታችን መጋቢት መጀመሪያ ቀናት ላይ ያበቃል። ይህ በእንዲህ እንዳለም ከኤሜሬቶች ጋር ካለፈው ጥቅምት እስከ ታኅሳስ ወር በተደረገው ስምምነት ከ40 ሚሊየን ዩሮ በላይ የሚያወጣ የባሕር ኃይል መከላከያን የሚጨምረው የጦር መሳሪያ ሽያጭ ውል አሁንም አልተቋጨም። የመናዊቱ ጋዜጠኛ እና የሰላም ኖቤል ተሸላሚ ታዋኮል ካርማን ጀርመን ለሳውዲ እና ለኤሜሬትስ መሣሪያ መሸጥ እንድታቆም ጥሪ አቅርባለች። 

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች