የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጉብኝት | አፍሪቃ | DW | 28.02.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጉብኝት

ማሊን በመጎብኘት ላይ የሚገኙት የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃይኮ ማስ እዚያ የሚገኙ ወታደሮቻቸው ለረዥም ተልዕኮ እንዲዘጋጁ አሳሰቡ። በማሊ መንግሥት እና በአማፅያን መካከል የታቀደው የሰላም ስምምነት በተደጋጋሚ በአሸባሪዎች መደናቀፉን ያመለከቱት ሃይኮ ማስ፤ የታሰበውን እውን ለማድረግ ረዘም ያለ ትዕግሥት ማስፈለጉን ገልጸዋል።

ማሊን በመጎብኘት ላይ የሚገኙት የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃይኮ ማስ እዚያ የሚገኙ ወታደሮቻቸው ለረዥም ተልዕኮ እንዲዘጋጁ አሳሰቡ። በማሊ መንግሥት እና በአማፅያን መካከል የታቀደው የሰላም ስምምነት በተደጋጋሚ በአሸባሪዎች መደናቀፉን ያመለከቱት ሃይኮ ማስ፤ የታሰበውን እውን ለማድረግ ረዘም ያለ ትዕግሥት ማስፈለጉን ገልጸዋል። ጀርመን ማሊ ውስጥ በተሰማራው የተመድ የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ውስጥ 700 የሚሆኑ ወታደሮች አሏት። ባለፈው እሁድ የጀርመን ወታደሮች በሰፈሩበት ከዋና ከተማ ባማኮ ወጣ ብሎ በሚገኘው ሁለተኛው የጦር ሰፈር ላይ ከባድ ጥቃት መድረሱ ተዘግቧል። በወቅቱ መኪና ላይ በተጠመደ ቦምብ እና ተኩስ ሦስት የማሊ ወታደሮች መጎዳታቸውም ተመልክቷል። ስለማሊ የፀጥታ ይዞታ እና ስለጀርመን ወታደሮች ቆይታ «DW» ያነጋገራቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃይኮ ማስ ሁኔታውን እንዲህ ገልፀዋል፤
«አስተማማኝ እንደሚሆን እርግጠኛ ነኝ ነገር ግን ትንሽ ፋታ ያስፈልገናል። ምክንያቱም እዚህ የሚታየው የፀጥታ ሁኔታ እኛ እንደምንገምተው አይደለም። የከፋ ነገር ከመጣ ልናደርገው የምንችለው ወታደሮቻችንን ማስወጣት ነው። ግን ደግሞ እስከዛሬ የተገነባው መዋቅር ሁሉ ወዲያው ይፈርሳል። አሸባሪዎች እና የተደራጁ ወንጀለኞችም በሀገሪቱ ላይ ዳግም የበላይነት ያገኛሉ።» ለአራት ቀን የተለያዩ የአፍሪቃ ሃገራትን የሚጎበኙት ሃይኮ ማስ ዛሬ ማሊ እንደሚገኙ የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አመልክቷል። ቀደም ባሉት ቀናትም ሴራሊዮን እና ቡርኪናፋሶን ጎብኝተዋል። 

 

ሸዋዬ ለገሰ

አዜብ ታደሰ