የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የኢራቅ ጉብኝት | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 16.08.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የኢራቅ ጉብኝት

የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ዛሬ ባግዳድ ተገኝተው ለኢራቅ መንግሥት ድጋፋቸውን ገለፁ። ሀገሪቱ በአማፂ ቡድኑ ላይ የምታደርገው ትግል ትክክል መሆኑን ለኢራቁ የፖለቲካ አቻቸው ሁሴን አል ሻሪስታኒ በመግለፅ ለሀገሪቱ በአሁኑ ሰዓት ከምንም በላይ ሰብዓዊ ርዳታ ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።

ለዚህም ጀርመን አስቀድማ 24 ሚሊዮን ዩሮ መመደቧን አስታውቃለች። የጀርመኑ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሽታይን ማየር ከባግዳድ ቆይታቸው በኃላ ወደ ኢራቅ ኩርድ ራስ- ገዝ መስተዳድር ዋና ከተማ ወደ አርቢል ተጉዘው አንድ የስደተኛ ጣቢያን ጎብኝተዋል። የጀርመኑ አየር ኃይል ዛሬ ጠዋት የመጀመሪያዎቹን የሰብዓዊ ርዳታዎች መዲና አርቢል ይዞ ገብቷል። ጀርመን ለኢራቅ የምታቀርበዉ ርዳታ እስካሁን በምግብ፣ በብርድ ልብስ እና በመድሃኒት እንደተወሰ ነው።

ትናንት ዓርብ ጀርመን ወደ ሰሜናዊ ኢራቅ ሰብዓዊ እርዳታ መላክ መጀመርዋ ይታወቃል። 5 የጀርመን አየር ኃይል አውሮፕላኖች ትናንት ማለዳ ለሰላማዊ ሰዎች እርዳታ የሚውል 36 ቶን ክብደት ያለው ሰብዓዊ እርዳታ ይዘው ወደ ሰሜን ኢራቅ ማቅናታቸዉ ይታወቃል።

መድሐኒቶች ምግብና ብርድ ልብስ የጫኑት እነዚሁ አውሮፕላኖች ወደ ኢራቅ ኩርድ ራስ- ገዝ መስተዳድር ዋና ከተማ አርቢል ማቅናታቸው ነበር የተገለፀዉ። ሌሎች እርዳታዎችን ወደ ኢራቅ መላኩ እንደሚቀጥልም የጀርመን መከላከያ ሚኒስትር ዑርዙላ ፎን ዴር ላየን ተናግረዋል።

«እርግጥ ነው ይህ የመጀመሪያው ነው። አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ተጨማሪ እርዳታዎችን ለመላክ ጠንክረን እየሠራን ነው። ተጨማሪ እርዳታዎችን የማጓጓዙ አስፈላጊነት የማይቀርና የሚታይ ነው። ለመከላከያ የሚውሉ ቁሳቁሶች አስፈላጊ ስለ መሆን አለመሆናቸው የሚቀርቡ ጥያቄዎችንም እያጠናን ነው። የብረት ቆቦች የጥይት መከላከያ ሰደርያዎች ና ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች በሚቀጥሉት ቀናት በተጨባጭ እንዲቀርብ ይደረጋል። እነዚህ አሁን በመከናወን ላይ ያሉ ቀጣይ እርምጃዎች ናቸው።»

አዜብ ታደሰ
ልደት አበበ