የጀርመን የውጭ ንግድ፤ የአውሮፓ ሕብረትና እሢያ | ኤኮኖሚ | DW | 17.02.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የጀርመን የውጭ ንግድ፤ የአውሮፓ ሕብረትና እሢያ

የጀርመን የውጭ ንግድ ማየሉን ባለፈው ሣምንት ያመለከተው የአገሪቱ ፌደራል የሰንጠረዥ ቢሮ ያወጣው አንድ መረጃ ነው። ዕድገቱ ቀጣይ ነው ወይ? በወቅቱ 5 ሚሊዮን ገደማ የደረሰውን የሥራ-አጥ ቁጥር ለመቀነስስ አስተዋጽኦው እስከምን ነው?
ለጀርመን የውጭ ንግድ 2004 ጥሩ ዓመት መሆኑ ገና ባለፈው ታሕሳስ ወር የተገመተ ነገር ነበር። ይህን የጀርመንን ምርቶች በውጭ ገበዮች ላይ ውድ ያደረገው የኤውሮ ተመን መናር እንኳ ሊገታው አልቻለም። ጀርመን ባለፈው 2004 ዓ.ም. ከ 730 ሚሊያርድ ኤውሮ በላይ ያወጣ ምርት ወደ ውጭ ለመሸጥ ችላለች። ይህም ቀደም ካለው ዓመት ሲነጻጸር የአሥር በመቶ ዕድገት መሆኑ ነው። በዚሁ ጊዜ ወደ አገር የገባውም የውጭ ምርት 7.4 በመቶ በማደግ ወደ 574 ሚሊያርድ ኤውሮ ከፍ ብሏል። በውጭ ንግዱ የተገኘው ትርፍ እንግዲህ 156.7 ሚሊያርድ ኤውሮ መሆኑ ነው።

ጀርመን በ 2004 ዓ.ም. በውጭ ንግዱ ረገድ ለምን ከዓለም ክብረ-ወሰን ለመድረስ እንደቻለች የአገሪቱ የንግድ ማሕበራት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሃንስ-ዩርገን ሙለር ሲያስረዱ- ”በውጭ ንግድ ላይ ያተኮረው የጀርመን የኤኮኖሚ ዘርፍ በዓለም አዳጊ ገበዮች ላይ፤ በተለይ በቻይናና በተቀሩት የደቡብ-ምሥራቅ እሢያ አገሮች ላይ ማተኮሩ እጅግ ጠቅሟል። የምሥራቅ አውሮፓ አገሮች፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ የአውሮፓውን ሕብረት የተቀላቀሉት መንግሥታትም ንግዱ ያለመባቸው ነበሩ። እነዚህ አገሮች ከፍተኛ ዓመታዊ ዕድገት የሚያደርጉ ሲሆን የውጭ ንግዳችን የናረውም በነዚሁ አካባቢዎች ነው።”

ከጀርመን ምርቶች፤ እነዚህም ከታላላቅ የምርት መኪናዎች አንስቶ እስከ አውቶሞቢል ብዙዎችን ያዳርሳሉ፤ ሁለት-ሶስተኛው የተሸጡት በአውሮፓው ሕብረት ውስጥ ነበር። በዚህ ንግድ አብዛኛውን ድርሻ የሚይዙትም የኤውሮው ምንዛሪ ተገልጋይ አገሮች ናቸው። በመሆኑም የኤውሮ ዋጋ መወደድ ንግዱን የሚያሰናክል አንዳች ተጽዕኖ አላሳየም። በዚህ በኤውሮ-ዞን ውስጥ ዋነኛዋ የጀርመን ምርት ተቀባይ ፈረንሣይ ነበረች። ከሕብረቱ ውጭ የተሸጠው ምርት ደግሞ በጠቅላላው በ 265 ሚሊያርድ ኤውሮ ይገመታል።

ለጀርመን የውጭ ንግድ ማየል ባለፈው ታሕሳስ ወር በሶሥተኛ አገሮች የታየው የሃያ በመቶ ዕድገት ድርሻ ቢኖረውም የምጣኔ-ሐብት ጠበብት የሚናገሩት የዓለም ኤኮኖሚ ማገገምና በአገር ውስጥ የደሞዝና የኑሮ ዋጋ ዕድገት ዝቅተኛ ሆኖ መገኘቱ ወሣኝ እንደነበር ነው። ይሁንና የነጋዴው ማሕበር ሥራ አስኪያጅ ሃንስ-ዩርገን ሙለር የጀርመን የውጭ ንግድ በያዝነው ዓመትም በዚህ መጠን ማደጉን ይጠራጠራሉ። “እንደዚህ ግሩም ሆኖ ይቀጥላል ብለን አንጠብቅም። ምክንያቱም በተለይ ቀደም ሲል የጠቀስኳቸው ሁለት ታላላቅ የዕድገት አካባቢዎች፤ ማለት ሩቅ ምሥራቅና በቀደምትነት ቻይና እንዲሁም የምሥራቅ አውሮፓ አገሮች ልማት ዝግ የሚል መሆኑ ነው። በተመሳሳይ ጊዜ በአውሮፓው ሕብረት ገበያና በጀርመንም ታላቅ የኤኮኖሚ ዕድገት ስለማይጠበቅ የውጭ ንግዱ በአማካይ ከአምሥት በመቶ በላይ ያድጋል ብለን አንጠብቅም። እርግጥ መጨረሻ ምን ውጤት ላይ እንደምንደርስ የዶላር ሂደትም ወሣኝ ይሆናል።”

የጀርመን የውጭ ንግድ ላለፈው ዓመት የአገሪቱ 1.7 በመቶ የኤኮኖሚ ዕድገትም ታላቅ አስተዋጽኦ አድርጓል። ሆኖም አሥር በመቶ በሆነው ጥሩ የውጭ ንግድ ዕድገት እንኳ የሚጎተተውን የውስጥ ገበያ እንቅስቃሴ ለማነቃቃት አልተቻለም። ስለዚህም በዓለምአቀፍ ደረጃ የውጭ ንግድ ክብረ-ወሰን ያስመዘገበችው ጀርመን በኤኮኖሚ ዕድገቷ አኳያ ደካማ ሆና ትቀጥላለች ማለት ነው። ይህ የውጭ ንግድ ዕርምጃ አስቸጋሪውን የሥራ ገበያ ሁኔታ ለመለወጥ የሚያስችል ተጽዕኖም አይኖረውም።

የአውሮፓው ሕብረት ዓባል መንግሥታት የልማት ተራድኦ ሚኒስትሮች በፊታችን ሰኞና ማክሰኞ ሉክሰምቡርግ ውስጥ በየግማሽ ዓመቱ የተለመደ ስብሰባቸውን ያካሂዳሉ። የሚነጋገሩባቸው ዓበይት ነጥቦች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በዓለም ላይ ያለውን ድህነት እስከ 2015 በከፊል ለመቀነስ ከአምሥት ዓመታት በፊት አውጥቶት የነበረው የሚሌኒየም ዕቅድና ደቡብ እሢያን የቃኘው የማዕበል ቁጣ ናቸው።

በሕንድ ውቂያኖስ ጠረፍ አስከፊው የማዕበል ቁጣ ታላቅ ጥፋት ካደረሰ ከሁለት ወራት በኋላ ሚኒስትሮቹ እስካሁን በተወሰዱት የዕርዳታ ዕርምጃዎች መርካታቸው አልቀረም። ዓባል ሃገራቱና የሕብረቱ ኮሚሢዮን ከወዲሁ የ 323 ሚሊዮን ኤውሮ አስቸካይ ሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርበዋል። በወቅቱ የአውሮፓውን ሕብረት በርዕስነት የምትመራው የሉክሰምቡርግ ባለሥልጣናት የሚናገሩት መላው ዓባል መንግሥታት ቃላቸውን አክብረው በዕርዳታው ተግባር እንደቀጠሉና ሁኔታው እንደማይለወጥም ነው።

የሕብረቱ የልማት ዕርዳታ ኮሜሣር ሉዊስ ሚሼል የገንዘብ አቅራቢዎቹን ሃገራት የክፍያ ሞራል ለማጠንከር በየስድሥት ወሩ የተሰጠውን ዕርዳታ የሚያመለክት ዝርዝር በይፋ ለማውጣት ያስባሉ። ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ከአንድ አማካሪ ኩባንያ ጋር በመሆን መቆጣጠሪያ ዘዴ ለመፍጠርም ታቅዷል። ቁርጠኛ ጥረት ነው እየተደረገ ያለው። በጉባዔው ላይ የሚሳተፉት የጀርመኗ የልማት ተራድኦ ሚኒስትር ሃይደማሪ ቪቾሬክ ሶይል ለተባበሩት መንግሥታት የተገባው ቃል ሳይዛነፍ ገቢር መሆን እንዳለበት ያስገነዝባሉ። ቪቾሬክ ሶይል እንዳስረዱት ጀርመን የመጀመሪያውን ሰብዓዊ ዕርዳታ ከማስተላለፏም በላይ በሶሥት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ሥራ ላይ የሚውል 500 ሚሊዮን ኤውሮ ለማቅረብ የገባችውን ቃል ገቢር ለማድረግ እየጣረች ነው።

የጀርመኗ ባለሥልጣን ይሄው ገንዘብ፤ በአጠቃላይም የአውሮፓው ሕብረት ዓባል መንግሥታት ለመንገድ ሥራ፣ ለወደቦች፣ ለት/ቤቶችና ለመኖሪያ ቤቶች መልሶ ግንባታ ቃል የገቡት 1.5 ሚሊያርድ ኤውሮ ተግባር ላይ የሚውልበትን ሁኔታ በተጨባጭ ለመታዘብ በሣምንቱ መጨረሻ ወደ ስሪላንካ ይጓዛሉ።

የአውሮፓው ሕብረት ኮሚሢዮንም ወደፊት የእሢያውን ትሱናሚ መሰል ቀውሶችን በፍጥነት ለመቋቋም ECHO በሚል አሕጽሮት የሚታወቀውን የራሱን የዕርዳታ ተቋም ለማስፋፋትም ያስባል። ዓባል መንግሥታት በቀውስ ጊዜ በፍጥነት ሊቀርቡ የሚችሉ የዕርዳታ ቡድኖችን እንዲመዘግቡም ተጠይቀዋል። ተግባሩን ብራስልስ ላይ ተቀማጭ በሆነ አንድ አመራር ለማቀናጀት ነው የተወጠነው። በሉክሰምቡርግ ባለሥልጣናት ዕምነት ቅንጅቱ እስካሁን የታዩ አንዳንድ ድክመቶችን ካስወገደ ከቃል ወደ ተግባር መሸጋገሩ የሚያዳግት ነገር አይሆንም።

የሕብረቱ የርዳታ ጉዳይ ኮሜሣር ሉዊስ ሚሼል እንዳስረዱት የማዕበሉ ቁጣ ከደረሰባቸው አገሮች አንዳንዶቹ ለምሳሌ ስሪላንካ የመልሶ-ግንባታ ፕሮዤዎችን በተመለከተ ጭብጥ የሆነ የራሳቸው ጽንሰ-ሃሣብ አላቸው። ማዕበሉ ያደረሰው ጥፋትና ያስከተለው መከራም ምናልባት በስሪላንካ መንግሥትና በታሚሉ ዓማጺያን፤ በኢንዶኔዚያም በጃካርታና በአቼህ የነጻነት እንቅስቃሴ መካከል ዕርቅን ሊያወርድ እንደሚችል የኮሜሣሩ ተሥፋ ነው። “ምናልባት እነዚህ ውዝግብ ያለባቸው አገሮች ሁኔታውን ተጠቅመው ችግሩን እንዲፈቱ ለማሳመን መሞከሩ ተገቢ ነው። ግን ጣልቃ መግባትም ሆነ ችግሮቹን ለማደባለቅ መከጀል የለብንም። አንድ የፖለቲካ ውዝግብ ትሱናሚ ካስከተለው ቁጣ የተለየ ነውና”

ለማንኛውም የአውሮፓው ሕብረት ለመልሶ-ግንባታው ተግባር ጭብጥ ዓላማ ለመቀየስ ካለፈው ሰኞ ወዲህ በስሪላንካና በኢንዶኔዚያ ሁኔታውን መታዘብ ጀምሮ ሰንብቷል። የሕብረቱ ኮሚሢዮን ለኢንዶኔዚያ፣ ታይላንድ፣ ስሪላንካና ሌሎች ጉዳት የደረሰባቸው ታዳጊ አገሮች ቀደም ሲል ታቅዶ የነበረው የንግድ ማቃለያ ዕርምጃ በፊታችን ሐምሌ መሆኑ ቀርቶ በቅርቡ በሚያዝያ ወር እንዲጸናም ሃሣብ አቅርቧል። ይህ የጊዜ ሽግሽግ በአራት ሚሊያርድ ኤውሮ የሚገመት የንግድ ልውውጥን የሚያስከትል ነው። እርግጥ ይህን ሃሣብ ከሶሥት ሣምንታት በፊት ብራስልስ ላይ ተካሂዶ የነበረው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ አልተቀበለውም ነበር። ቢሳካ መልሶ-ግንባታውን ለማጠናከር የሚረዳ እንደሚሆን አንድና ሁለት የለውም።