የጀርመን የእሥራኤል ምክክር በበርሊን | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 05.12.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የጀርመን የእሥራኤል ምክክር በበርሊን

የጀርመን እና የእሥራኤል ካቢኔዎች አባላት ዛሬ ማምሻቸውን በበርሊን ምክክር ያካሂዳሉ። ሁለቱ ሀገራት ሁለት ቀናት በሚቆየው እና አሁኑ ለአራተኛ ጊዜ በሚያካሂዱት ምክክር ላይ የሚወያዩት በትምህርት፡ በፈጠራ ክሂሎትና እና በዘላቂ

ልማት በተሰኙት ጉዳዮች ላይ ቢሆንም፡ ይኸው ምክክራቸው እሥራኤል በያዘችው የፍልሥጤማውያን ግዛት፡ ማለትም፡ በምዕራባዊው ዳርቻ እና በምሥራቅ ኢየሩሳሌም 3000 አዳዲስ መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት ባወጣችው ዕቅዷ የተነሳ ጥላ አጥሎበታል። በመካከለኛ ምሥራቅ ሰላም ለማውረድ የሚደረገውን ጥረት አዳጋች ያደርገዋል የሚባለው ይኸው ዕቅድ ጀርመንን እንዳሳሰባት ተመልክቶዋል።

የጀርመናውያን የውጭ ፖሊሲ መሠረታዊ ምሰሶ ከእሥራኤል ጋ መልካሙን ግንኙነት መፍጠር ነው። የእሥራኤል እና የጀርመን ግንኙነት በተለይ ባለፉት ዓመታት ይበልጡን ተጠናክሮ፡ እአአ ከ 2008 ዓም ወዲህ በያመቱ የበርሊንና የኢየሩሳሌም የካቢኔ አባላት ምክክር ያደርጋሉ።

የእሥራኤል ደህንነት የማረጋገጥ ጽኑ ፍላጎት ያላት ጀርመን እሥራኤል ያወጣችው አዲሱ የሠፈራ ግንባት እንዳሳሰባት በጀርመን ፌዴራዊ ምክር ቤት፡ ቡንድስታክ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ሊቀመንበር የሆኑት የክርስትያን ዴሞክራቶች ህብረት እንደራሴ ሩፐርት ፖለንስ ከዶይቸ ቬለ ጋ ባደረጉት ቃለ ምልልስ አስታውቀዋል። በዚህም የተነሳ ፣ ይላሉ ፖለንስ፣ የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ጀርመናውያን በሠፈራው ግንባታ አንፃር ያደረባቸውን ስጋት ግልጽ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
« የጀርመን ዓላማ እሥራኤል እንደ አንድ ዴሞክራሲያዊ የአይሁዳውያን መንግሥት ከጎረቤቶችዋ ጋ በሰላም መኖር እንድትችል ማድረግ ነው። ይህ ግን የሁለት መንግሥታት ምሥረታው መፍትሔ በተግባር ሲተረጎም ብቻ ነው እውን የሚሆነው። እና አሁን እሥራኤል E - 1 በሚል መጠሪያ በሚታወቀው የሠፈራ ዕቅዷ ይህንኑ ሂደት ካሰናከለች ይህ ዓላማ ግቡን ሊመታ አይችልም። »


የጀርመናውያን እሥራኤላውያን የምክር ቤት ቡድን ሊቀ መንበር ጄሪ ሞንታግም ተመሣሣይ አስተያየት ነው የሰነዘሩት።
« ትልቁ ምኞቴ መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል በጀርመንና በእሥራኤል መካከል ያለውን እና ታሪክ ጭምር ያጠናከረውን የጠበቀ ትሥሥር ሳይበጥሱ በሠፈራው ግንባታ ዕቅድ አንፃር ግልፁን መልዕክት እንዲያስተላልፉ ነው። በእሥራኤል ጎን መቆማችንን እንቀጥላለን። በእሥራኤል አኳያ ልዩ ኃላፊነት አለብን። በዚህም የተነሳ ጀርመን የሁለት መንግሥታት ምሥረታ ወደ ሰላም የሚያመራ መንገድ አድርጋ እንደምትመለከተው ለእሥራኤል ግልፅ ማድረግ ይኖርባታል። »
በዛሬው የሁለቱ ሀገራት የካቢኔ ምክክር ላይ ከጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጎን ይሳተፋሉ ተብለው ሲጠበቁ የነበሩት የእሥራኤል መከላከያ ፡ የውጭ ጉዳይ እና የምጣኔ ሀብት ሚንስትሮች፡ እንዲሁም፡ የሌሎች ዘርፎች ተወካዮች ቢሆኑም፡ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አቪግዶር ሊበርማን ተሳትፎአቸውን ከጥቂት ጊዜ በፊት መሰረዛቸው ተሰምቶዋል። የቀኝ አክራሪው ፖለቲከኛ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁን አጅበው ወደ በርሊን ለምን እንደማይመጡ ምክንያቱ በውል አልታወቀም። በዚያም ሆነ በዚህ ግን በምክክሩ የሚካፈሉት እሥራኤላውያኑ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በአዲሱ የሀገራቸው የሠፈራ ዕቅድ ላይ ከጀርመናውያኑ አቻዎቻቸው ብርቱ ሂስ ሊቀርብባቸው እንደሚገባ ሞንታግ ከማሳሰባቸው ጎን፡ ጀርመን ባለፈው ሣምንት በኒው ዮርክ የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ የፍልሥጤማውያንን አቋም ወደ መንግሥታዊ ያልሆነ የታዛቢነት ደረጃ ከፍ ባደረገበት የድምፅ አሰጣጥ ላይ ድምፀ ተዓቅቦ ያደረገችው ጀርመን ርምጃውን ያልተቃወመችበትን ምክንያት እንድታስረዳ ማወቅ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል። እንደሚታወሰው፡ የተመድ የፍልሥጤማውያኑን ማመልከቻ በከፍተኛ የድምፅ ብልጫ ነበር ያፀደቀው። ማመልከቻውን የተቃወመችው እሥራኤል ድምፅ አሰጣጡ ከተጠናቀቀ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ነበር በያዘችው የፍልሥጤማውያን ግዛት E1 የተባለው የሠፈራ ግንባት እንዲካሄድ ፈቃድ የሰጠችው። ሞንታግ ይህንኑ የእሥራኤል ርምጃ የተሳሳተ ነው ብለውታል።


« የእሥራኤል አቋም፡ ለራስዋ ለእሥራኤል ጥቅም ሲባል፡ ውይይት እና ለውጥ ይደረግባት ባይ ነኝ። እሥራኤል መረዳት ያለባት፡ የድምፅ አሰጣጡ ዓለም በጠቅላላ ያህሉ የፍልሥጤማውያንን አቋም በተመድ ለማሳደግ፡ ማለትም፡ በመካከለኛው ምሥራቅ ለሁለት መንግሥታቱ ምሥረታ የራሱን ተጨባጭ ድርሻ ለማበርከት መወሰኑን ነው። እና የእሥራኤል መንግሥት፡ ለእሥራኤል ጥቅም ሲል ይህንኑ የሁለት መንግሥታት ምሥረታን መንገድ ከማክሸፍ ይልቅ፡ ገንቢ በሆነ ዘዴ ቢከተለው ያዋጣዋል። »
ቡንድስታግ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ሊቀ መንበር ሩፐርት ፖለንስ የተመድ ውሳኔን የሰላሙን መፍትሔ የሚያጎላ አድርገው ተመልክተውታል።
« የውሳኔውን አንቀጽ ጽሑፍ ስንመለከት፡ ፍልሥጤማውያን የእሥራኤልን ኅልውና እንደሚያውቁና ከእሥራኤል ጎን ለጎንም የፍልሥጤማውያን መንግሥት እአአ በ 1967 ዓም ድንበር ውስጥ ሊመሠረት እንደሚገባ እና በድንበሩ አከላለል ላይ ለውጥ ሊኖር እንደሚችል ሊታሰብ እንደሚገባ ይነበባል። ይኸው ነጥብ እስካሁን ሁሌ ለድርድር የቀረበው መፍትሔ ነበር። የውሳኔው አንቀጽ ዓላማም ይህ ነው። እና የጀርመን መንግሥትም ይህን ዓይነቱን የውሳኔ ጽሑፍን አልቀበልም ለማለት እንደማይቻል አሳማኝ መከራከሪያ ሀሳብ ልሊያቀርብ ይችላል። »
ከኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ ይገንባ የሚባለው ሠፈራ ምዕራባዊውን ዳርቻ ለሁለት የሚከፍል ከመሆኑም ሌላ፡ ዐረባዊውን ምሥራቅ ኢየሩሳሌምንም ከተቀረው የፍልሥጤማውያን ግዛት በጠቅላላ ይለያያል። ይህም የሰላሙን ጥረት ይበልቱን አዳጋች ስለሚያደርገው ነው ጀርመን እና ሌሎች ምዕራባውያን መንግሥታት ዕቅዷን እንድትሰርዝ ያሳሰቡት። ይሁን እንጂ፡ በርሊን እና ኢየሩሳሌም፡ ምንም እንኳን በዚሁ ጉዳይ ላይ የአመለካከት ልዩነት ቢኖራቸውም፡ በፀጥታ ጥበቃው ዘርፍ በቅርብ ተባብረው መሥራታቸውን ቀጥለዋል።
የእሥራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁን የበርሊን ጉዞ በመቃወም ለነገ ጥዋት ግዙፍ የተቃውሞ ሰልፍ ለማካሄድ ዕቅድ መያዙ ተሰምቶዋል።

አንድሪያስ ጎርሴቭስኪ/ አርያም ተክሌ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic