የጀርመን የኤቦላ ሕክምና ማዕከል | ጤና እና አካባቢ | DW | 14.11.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

የጀርመን የኤቦላ ሕክምና ማዕከል

ኤቦላ ተሐዋሲ መስፋፋትን ለመግታት የሚደረገዉ ጥረት በተጠናከረበት በዚህ ወቅት ላይቤሪያ ዉስጥ በጀርመን የሕክምና እርዳታ ድርጅት አክሽን ሜዲዮር የተገነባዉ የኤቦላ ታማሚዎች ማዕከል ግንባታ ተጠናቆ ሙሉ ሥራዉን ጀመረ።

የሕክምና ማዕከሉ የላይቤሪያ መንግሥት ካዘጋጀዉ የኤቦላ ታማሚዎች መታከሚያ ዘርፍ ጋ የተገናኘ በመሆኑም የኤቦላ ተሐዋሲን መዛመት ለመቀነስ በበሽታዉ የተያዙ ወገኖች ተገልለዉ የሚቆዩባቸዉ ክፍሎች ቁጥር እንዲጨምር ያደርጋል።

«አሁን ኤሌዋ ክሊኒክ ዉስጥ እገኛለሁ።» በታችኛዉ ኤለዋ ሃኪም ቤት ቅጽር ግቢ ስለሚገኝም፤ በመሠረቱ ኤለዋ የኤቦላ ማዕከል ቁጥር ሁለት ነዉ የተባለዉ። እኔ ከቆምኩበት ፊት ለፊት ሁለት ትላልቅ ድንኳኖች አሉ። የጀርመን የሕክምና እርዳታ ድርጅት አክሽን ሜዲዮር ነዉ ያስገነባዉ። ከላይቤሪያዋ ዋና ከተማ ሞኖሮቪያ ወጣ ብሎ የተዘጋጁት እነዚህ አዲስ የኤቦላ ታማሚዎች አግልሎ ማቆያ ስፍራ በጀርመናዊቱ የጤና ባለሙያ ማርግሬት ጊራቲስ ኒማነ ትብብር ነዉ የተሠራዉ። ጀርመናዊቱ የጤና ባለሙያ ሞኖሮቪያ ዉስጥ የህክምና የእርዳታ ድርጅት ያቋቋሙ ሲሆን አሁን ኤቦላን ለማጥፋት በሚደረገዉ ጥረት የበኩላቸዉን እያደረጉ ነዉ።

ሁለቱ አዳዲስ የኤቦላ ታማሚዎች ለይቶ ማቆያ ስፍራዎች ግንባታ ባለፈዉ ሳምንት መጀመሪያ ሲጠናቀቅም ኤቦላን ለማጥፋት በሚደረገዉ ዘመቻ ለመርዳት የጀርመን ጦር ሠራዊትና የህክምና አባላትያካተተ ቡድን እዚያ በመድረሱ ግራቲስ ኒማነ በጣም ተደስተዋል።

«ይህ ድንኳን በጣም ልዩ ነዉ። ሌላኛዉ ድንኳን ደግሞ የሚቀት መቆጣጠሪያ የለዉም። በየትኛዉም ቦታ የሚገኝ የተለመደዉን ድንኳን ነዉ የምንጠቀመዉ እናም ለታማሚዎቹም በጣም ጥሩ ይሆናል።»

ግራቲስ ኒማነ ለጀርመኑ ወታደራዊና የህክምና ቡድን አዲሱን የህክምና ማዕከል ሲያስጎበኙ ከእሳቸዉ ባልደረቦች አንዱ ደግሞ ገለጻዉን ያደርግ ነበር።

«ሳምሶን ካዋና እባላለሁ መዝጋቢ ነርስ ነኝ። ሕሙማንን በመቀበል አስተናግዳለሁ። ለሕሙማኑ መድሃኒት፤ ምግብና አስፈላጊዉን ክብካቤ እሰጣለሁ፤ ልብሶቻቸዉን መለወጥን ጨምሮ ማለት ነዉ። እነዚህ ድንኳኖች ለታማሚዎቹ ማግኘታችን በጣም ጥሩ ነዉ። ድንኳኖቹ ሙሉ በሙሉ አየር ማናፈሻና ማቀዝቀዣ ያላቸዉ በመሆናቸዉ ምቹ ናቸዉ።»

አዲስ በተዘጋጀዉ የኤቦላ ታካሚዎች ማዕከል ዉስጥ የተዘጋጁት ሁለቱ ድንኳኖች እያንዳንዳቸዉ 22 አልጋዎች ማዘርጋት ይችላሉ። አንደኛዉ ሴቶችና ልጆች የሚስተናገዱበት ሲሆን አንደኛዉ ደግሞ ለወንዶች ነዉ። አንደኛዉ ድንኳን አፍሪቃ ሌላኛዉ ጀርመን ተብለዉ ተሰይመዋል። ከዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ በዚሁ ኤቦላን ለመቆጣጠር በሚካሄደዉ ዘመቻ ለመራዳት የመጡት ዶክተር ጆርጅ ኦሌንኮ ከሕህመማቸዉ ያገገሙት የኤቦላ ሰለባዎች ጀርመን ወደተባለዉ ድንኳን እንዲዛወሩ ይደረጋል። የጸናባቸዉ ደግሞ በአፍሪቃ ድንኳን ይቆያሉ።

«አሁን ከታማሚዎች ጋ ትልቅ ችግር አለብን። ሁኔታቸዉ የተሻሻለዉን ጀርመን ድንኳን ዉስጥ የጠናባቸዉን ደግሞ ወደአፍሪቃ ድንኳን ለማዛወር ወስነናል። ይህም ማለት በጣም የታመመና የደከመዉ እንዲሁም አቅም ያጣ አፍሪቃ ድንኳን ዉስጥ ይቆያል ማለት።»

ግራቲስ ኒማነ ተጨማሪ ሁለት በሽተኞች ተገልለዉ የሚቆዩባቸዉ ስፍራዎች መገንባታቸዉ የኤቦላ ተሐዋሲ እንዳይስፋፋ የሚደረገዉን ዘመቻ ያጠናክራል ይላሉ።

«እርግጥ ነዉ ይህ አስደስቶኛል ምክንያቱም ጤናማ ለመሆን በተለይ ደግሞ በኤቦላ የተጎዳህ ከሆነ ጥሩ አካባቢ ያስፈልጋል። ምክንያቱም መገለል ይገጥምሃል። አሁን ግን ሕመምተኞቹ የሚያስታምማቸዉ የማግኘት እድል አላቸዉ። አስታዉሳለሁ ሐምሌና ነሐሴ አካባቢ እንዲህ ያሉ ማዕከላት አልነበሩም። ባዶ የሐኪም ቤት አልጋም አልነበረም። አሁን በቂ ቦታ አለ፤ ያ ደግሞ ግሩም ነዉ።»።

Mitarbeiter der action medeor packt in Toenisvorst Notfallpakete für Birma

በአክሽን ሜንዲዩር የተገነባዉን የጀርመን ላይቤሪያ የኤቦላ ታማሚዎችን ማቆያ ማዕከል ከተመለከቱ በኋላ ጀርመን ላይቤሪያ ዉስጥ ኤቦላን ለማጥፋት እንዲሳተፍ የላከችዉ ወታደራዊ ኃይልን የሚመሩት የጀርመን ቀይ መስቀል ቡድን መሪ ክላዉስ ሙሾቭ ባዩት ዝግጅት መደሰታቸዉን ገልጸዋል።

«ማርጋሬት በሰራችዉ በጣም ተደስቻለሁ። እዚህ ለታማሚዎች አስፈላጊዎቹ ነገሮች በመኖራቸዉ ከእንግዲህ አይሰቃዩም።»

ላይቤሪያ ዉስጥ በኤቦላ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ በመሄዱ የጀርመን የሕክምና የእርዳታ ድርጅት አክሽን ሜዲዮርበሚያደርገዉ አስተዋፅኦ ኦቦላን ከሀገሪቱ ጨርሶ የማጥፋቱ ተስፋ አለ።

ጁሊየስ ካኑባ/ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic