የጀርመን የአካባቢ ጥበቃ መርሀ ግብር | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 24.08.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የጀርመን የአካባቢ ጥበቃ መርሀ ግብር

ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቅ የካርቦን ዳይኦክሳይድ ጋዝ መጠን መቀነስ በአሁኑ ሰዓት ከፍተኛ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች ውስጥ አብዩ ነው ።

የጀርመን ካቢኔ

የጀርመን ካቢኔ

ለዓለማችን ሙቀት መጨመርና ለልዩ ልዩ የአካባቢ ጥበቃ ችግሮች መንስኤ የሆነውን ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቅ የካርቦን ዳይኦክሳይድ ጋዝ መጠን መቀነስ በአሁኑ ሰዓት ከፍተኛ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች ውስጥ አብዩ ነው ። በተለይ የአየር ፀባይ ለውጥ በየአገሩ ያስከተለው አደጋ እንደ ጥሩ ምሳሌ ሊታዩ በሚችልበት በአሁኑ ወቅት አገራት ትኩረታቸውን ወደዚሁ አቅጣጫ አድርገዋል ። ቀደም ሲልም የችግሩን አሳሳቢነት የተረዱት ሰላሳ ስድስት ባለ ኢንዱስትሪ ሀገራት ለዓየር ፀባይ ለውጥ መንስኤ የሆነውን የካርቦን ዳይኦክሳይድ ጋዝ መጠን ለመቀነስ የክዮቶውን ውል ፈርመዋል ። በውሉ መሰረትም እስከ ዛሬ አምስት ዓመት ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቀውን የዚህን ጋዝ መጠን በአምስት በመቶ ዝቅ ለማድረግ ነው የተስማሙት ። የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራትም በበኩላቸው ለአጣዳፊው ችግር የቅርብ መፍትሄ ለመሻት የጋራ ስምምነት ላይ ደርሰዋል ። በኢንዱስትሪ ከበለፀጉት አገራት ውስጥ አንዷ የሆነችው የአውሮፓ ህብረት አባል ጀርመንም በዚህ አቅጣጫ የበኩልዋን ዕርምጃ ለመውሰድ የሚያስችላትን ዕቅድ አውጣለች ። የጀርመን ካቢኔ የሁለት ቀናት ስብሰባውን ትናንት ሜሰቤርግ ውስጥ በጀመረበት ወቅት ዋነኛው የመወያያ ርዕስ ባለ ሰላሳ ነጥቡ የአካባቢ ጥበቃ መርሀግብር ነበር ። የጀርመን የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር ሲግማር ጋብርየል በጀርመን እስካሁን አካባቢን ለመጠበቅ ብዙ ተሰርቷል ይላሉ ።
« በዕርግጥም ሁሌም ቢሆን ራስን ማሞገስ አስቸጋሪ ነገር ነው ። ሆኖም በአካባቢ ጥበቃ ፖለቲካ ረገድ ትልቅ ዕመርታ ታይቷል ብዮ ነው የማስበው ። ቀደም ባለው ጊዜ በየዓመቱ ሁለት ሚሊዮን ቶን መጠን ያለው የካርቦን ዳይኦክሳይድ ጋዝ ነበር ወደ ከባቢ አየር እንዳይገባ የሚደረገው ። አሁን ግን ትልቅ ማስተካከያ አድርገናል ። ሁለት መቶ ሚሊዮን ቶን መጠን ያለው የካርቦን ዳይኦክሳይድ ጋዝ ነው በየዓመቱ ከባቢ አየርን እንዳይበክል የምንይዘው ። »

የአካባቢ ጥበቃ መርሀ ግብሩ አከራክሯል

የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትሩ ገብርየል የአካባቢ ጥበቃ መርሀ ግብራቸው ተቀባይነት እንዲያገኝ ከክርስቲያን ዲሞክራቱ የኢኮኖሚ ሚኒስትር ሚሻኤል ግሎስ ጋር ብዙ ተሟግተዋል ። ክርክሩም መርሀ ግብሩ በአንዳንድ ተቋማት ላይ የሚያሳድረው ጫና ከፍተኛ ይሆናል የሚለው ነበር ። የኢኪኖሚ ሚኒስትሩ መርሀ ግብሩ ብዙ ያስወጣንል ሲሉም ነው የሚከራከሩት ። እርሳቸው ሂሳቡን እንዳሰሉት ለመርሀ ግብሩ ማስፈፀሚያ ሰባ ቢሊዮን ዩሮ ያስፈልጋል ። ጋብርየል ደግሞ ይህ እጅግ ተጋኗል ሱሉ ነበር የተቃወሙት ። በዚህ ክርክርም በመጨረሻ ላይ ድሉ የገብሬል ሆኗል ። መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክልም የአካባቢ ጥበቃ መርሀ ግብሩ ደጋፊ ነበሩ ። ሜርክል ጉዱዩን ሰፋ አድርገው በማየት አውሮፓ ብቻውን ለአካባቢ ጥበቃ ትኩረት ቢሰጥ የትም እንደማይደረስ ነበር ያስረዱት ።
« የቡድን ስምንት ፕሬዝዳንትነታችንን አውሮፓ ብቻ የመሪነቱን ቦታ መያዝ እንደሌለባት ይልቁንም ዩናይትድ ስቴትስም በመልማት ላይ ያሉት አገራትም አንድ ነገር እንዲያደርጉ እንጠቀምበታለን ። » ምክንያቱም አውሮፓ ለብቻዋ የአየር ፀባይ ለውጥን ልትከላከል አትችልም ። »
የጀርመን መንግስት እስከ ዛሬ አስራ ሶስት ዓመት ድረስ ወደ ከባቢ አየር የሚገባውን በካይ ጋዝ መጠን አሁን ከሚለቀቀው በአርባ በመቶ ለመቀነስ ነው ያቀደው ። በዕቅዱ መሰረት የቤት ውስጥ የኃይል አጠቃቀም ልዩ ትኩረት ይሰጠዋል ። በሀገሪቱ ጥቅም ላይ ከሚውለው የኃይል መጠን አንድ ሶስተኛው ለቤት ውስጥ አገልግሎት ነው የሚውለው ። ጥምሩ መንግስት ስልጣን ከያዘ ወዲህ ከፀሀይና ከንፋስ የሚገኝን ኃይል በመጠቀም የኃይል ቁጠባን ተግባራዊ አድርጓል ። ይሁንና እንደ አንዳንድ የአካባቢ ጥበቃ ባለሞያዎች መርሀግብሩ የሚጎለው ነገር አላጣም ። ለምሳሌ አሽከርካሪዎች ከባቢ አየር እንዳይበከል መውሰድ ያለባቸው ዕርምጃ በሰነዱ ውስጥ የለም ።