የጀርመን የስደተኞች ጉዳይ ረቂቅ ህግ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 19.04.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የጀርመን የስደተኞች ጉዳይ ረቂቅ ህግ

የጀርመን ጥምር መንግሥት ጀርመን ተገን የተሰጣቸው ስደተኞች ከህብረተሰቡ ጋር ተዋህደው የሚኖሩበትን መንገድ ያፋጥናል በተባለ አዲስ እቅድ ላይ ባለፈው ሳምንት ተስማምቷል ። በረቂቅ ህግ ደረጃ በቀረበው በዚህ እቅድ ከዚህ ቀደም በተገን ጠያቂዎች ላይ ገደብ የሚጥሉ አንዳንድ ደንቦች ይሻሻላሉ ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:57

የጀርመን የስደተኞች ጉዳይ ረቂቅ ህግ

ጀርመንን ተጣምረው የሚመሩት የክርስቲያን ዴሞክራት ህብረት ፣የክርስቲያን ሶሻል ህብረትና የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲዎች ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ላይ የተስማሙበት አዲስ የውህደት ጉዳይ ረቂቅ ህግ በሃገሪቱ የረዥም ጊዜ ታሪክ ውስጥ ልዩ ስፍራ የሚሰጠው እርምጃ ተደርጎ ተወስዷል ። የእስከ ዛሬዎቹን የተናጠል እርምጃዎች በማዕከላዊ አሰራር ይተካል የተባለው ረቂቁ ህግ ከዚህ ቀደም ለተገን ጠያቂዎች የተዘጉ አንዳንድ እድሎችን በመክፈት ከቀደሙት ደንቦች ይለያል ። ከቀድሞው በተሻለ ተገን ጠያቂዎች ከህብረተሰቡ ጋር ፈጥነው እንዲዋሃዱ ያግዛሉ የተባሉ እርምጃዎችንም አካቷል ። በጀርመን ፌደራል ሪፐብሊክ መንግሥት ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ ይህ የውህደት ህግ መቅረቡ ፣ የጀርመን ሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ ሊቀመንበርና ምክትል መራሄ መንግሥት ዚግማር ገብርየል እንዳሉት ለተገን ጠያቂዎች የተሻሉ እድሎችን የሚፈጥር ታሪካዊ እርምጃ ነው ።
«በርግጥ የውህደት ህግን ማውጣት እጅግ በጣም አስፈላጊ ከሆኑት ውሳኔዎች አንዱ ነው ። በጀርመን ፌደራል ሪፐብሊክ ታሪክ ጀርመን ለመጀመሪያ ጊዜ የውህደት ህግ ይኖራታል ።ይህ ታሪካዊ እርምጃ ነው ።ከኛ ጋር መኖር የሚፈልጉ ከአሁን በኋላ ለህብረተሰቡ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት የተሻሉ እድሎች ይኖሩዋቸዋል ። በዚህ ውስጥ የሚካፈሉ እውቅና ፣ብልፅግናና እና ነፃነት ያገኛሉ ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላም እንደ ዜጋ መብትና ግዴታዎች ይኖሯቸዋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ

።እንደ SPD መሪ እርግጠኛ ነኝ፣ ይህ ህግ በጥቂት በጥቂት ዓመታት ውስጥ ለዘመናዊ የኢሚግሬሽን ህግ እንደ አንድ ትልቅ እርምጃ ሊታይ ይችላል ።»
በጎርጎሮሳውያኑ 2015 ዓም ጀርመን የገቡ ተገን ጠያቂዎች ቁጥር 1.1 ሚሊዮን ይገመታል ። አዲሱ ህግ እነዚህ ተገን ጠያቂዎች በተቻለ ፍጥነት ከህብረተሰቡ ጋር ተዋህደው እንዲኖሩና የተሻለ የሥራ እድል እንዲያገኙ ይረዳል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል ። በሌላ በኩል ረቂቁ በተገን ጠያቂዎች ላይ ገደቦችን የሚጥሉ እቅዶችንም ይጨምራል ። ከፍተኛ ትምህርታቸውን እዚህ ጀርመን የተከታተሉት የህግ ባለሞያና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ዶክተር ለማ ይፍራ ሸዋ እንደሚሉት ህጉ ስደተኞች በትላላቅ ከተሞች እንዳይከማቹ ለማድረግ የሚኖሩበትን ስፍራ ይገድባል ።
ስደተኞችን በተመደቡበት ቦታ ብቻ እንዲቆዩ የሚያስገድደው አዲሱ ህግ በብዛት በከተሞች መስፈራቸውን ቢከላከልም ዶክተር ለማ እንደሚሉት በአንዳንድ ሁኔታዎች የተገን ጠያቂዎችን ህይወት አስቸጋሪ ሊይደርግ ይችላል።
መንግሥት ጦርነትና ክትትልን እንዲሁም ግድያን ሸሽተው ጀርመን የመጡ ስደተኞች የተገን ማመልከቻዎች ቶሎ መልስ እንዲያገኝ ይፈልጋል ። በሌላ በኩል የተገን ጥያቄአቸው ተቀባይነት ሳያገኝ የቀረ በጥቅሉ የኤኮኖሚ ስደተኞች የሚላቸው ደግሞ በአፋጣኝ ወደ መጡበት እንዲመለሱ አቅዷል ። ጀርመን እንዲኖሩ ለተፈቀደላቸው ደግሞ አዲሱ ህግ እንደ ከዚህ ቀደሙ

Afrikaner in Deutschland Ausbildung von afrikanischen Arbeitern bei Dornier

ሳይሠሩ የሃገሪቱ የማህበራዊ ድጎማ ተቀባይ ብቻ እንዳይሆኑ ይከላከላል ።
በእቅዱ መሠረት የጀርመን ፌደራል መንግሥት ፣ ድጎማ ለሚሰጣቸው ተገን ጠያቂዎች ፣ 100 ሺህ ያህል ሥራዎችን ለመፍጠር የሚያስችል ገንዘብ ይመድባል ። ከዚህ ሌላ ህጉ ታሪካዊ ሊባል የሚችል ለውጥም አካቷል ።
በአዲሱ ህግ ስደተኞች የተገን ማመልከቻቸው ተቀባይነት ባገኘ በ 6 ሳምንት ውስጥ የቋንቋ ትምህርት መጀመር ይፈቀድላቸዋል ። በህጉ ተገን ጠያቂዎች ቋንቋ የመማር ግዴታ አለባቸው ። ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ የማይሆኑ ስደተኞች ግን ከመንግስት የሚሰጣቸው ድጎማ ይቀነስባቸዋል ። የውጭ ዜጎች የጀርመንኛ ቋንቋን ጨምሮ ስለ ህዝቡ ባህልና ስለ ሃገሪቱ የፖለቲካ ስርዓት የሚማሩበት የውህደት ትምህርት የሚያስተምሩት ዶክተር ለማ ከልምድ እንደሚናገሩት ግን ቋንቋ መማር የማይፈልጉ ስደተኞች አላጋጠሟቸውም ።
ጀርመን ተገን የሚሰጣቸውን ስደተኞች መብትና ግዴታዎችን የሚመለከተው አዲሱ ህግ ያስቀመጣቸው ገደቦች እና ያሻሻላቸው ደንቦች ዋነኛ ዓላማ አንድ ነው እንደ ዶክተር ለማ ። በርሳቸው አስተያየት ጥምሩ መንግሥት በአዲሱ ህግ ሃገሪቱ ለስደተኞች በምትሰጠው ማህበራዊ ድጎማ ብቻ ተስበው የሚመጡ ስደተኞችን የማስቀረት ዓላማ ይዞ የተቀረፀ ነው ።
ረቂቅ ህጉ በዚህ ሳምንት ከጀርመን ፌደራዊ ክፍለተ ሃገራት መሪዎች ጋር ውይይት ይደረግበታል ። ከዚያም በሃገሪቱ ፓርላማ ቀጥሎም በጀርመን ፌደራል ምክር ቤት ከፀደቀ በኋላ ሥራ ላይ ይውላል ። ህጉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል ።

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሀመድ

Audios and videos on the topic