የጀርመን የስደተኞች ወጪ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 04.09.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የጀርመን የስደተኞች ወጪ

ጀርመን የሚገቡት ስደተኞች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ነው ። በዚያው መጠንም ሃገሪቱ ለስደተኞች የምታወጣው ገንዘብም እያደገ ነው ። ይህም ሊያስከትል ይችላል የተባለው ችግር እያነጋገረ ነው ። ይሁንና ወጪው ከጀርመን አጠቃላይ በጀት ጋር ሲነፃጸር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:21
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:21 ደቂቃ

የጀርመን የስደተኞች ወጪ

በዚህ ርዕስ ላይ የሚካሄደው ውይይትም ትርጉም አልባ ሆኗል ሲል የዶቼቬለው ክላውስ ኡልሪሽ ዘግቧል ። በሌላ በኩል ምዕራብ ጀርመን ሄፐንሃይም በተባለችው ከተማ በአንድ የስደተኞች መጠለያ በተነሳ ቃጠሎ 5 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል ። የቃጠሎው መንስኤ እስካሁን በትክክል አልታወቀም ።
ዙድ ዶይቸ ትሳይቱንግ የተባለው ታዋቂ የጀርመን እለታዊ ጋዜጣ ፣ጀርመን ወደ ሃገርዋ በሚገቡ ስደተኞች ምክንያት ባለፉት ዓመታት ያወጣችውንና ዘንድሮ ታወጣለች የሚባለውን ገንዘብ መጠን ያነፃፀረበትን ዘገባ በዚህ ሳምንት አውጥቶ ነበር ። በዚሁ ዘገባ መሠረት የጀርመን ፌደራል መንግሥት ከ2 ዓመት በፊት ማለትም በጎርጎሮሳዊው 2013 ለተገን ጠያቂዎች ወጪ ያደረገው ገንዘብ 1.5 ቢሊዪን ዩሮ ይጠጋል ። የጀርመን ፌደራል ግዛቶች ደግሞ እያንዳንዳቸው በየዓመቱ ለስደተኞች 12,500 ዩሮ እንደሚያወጡ ተዘግቧል ። ይህ ገንዘብ ፣ሊገባደድ አራት ወራት ገደማ በቀሩት በ2015 ወደ 10 ቢሊዮን ዩሮ ከፍ ሊል እንደሚችል ይገመታል ። ይሁንና ይህ ገንዘብ ከ301 ቢሊዮን ዩሮ በላይ ከሆነው የጀርመን ዓመታዊ በጀት ጋር ሲነፃጸር ብዙ ሊባል የሚችል አይደለም ። በመቶኛ ሲሰላ ከአጠቃላዩ በጀት 3.31 በመቶ ነው ።ያም ሆኖ የፌደራል ጀርመን የማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስትር አንድሪያ ኔህልስ ፣ ለስደተኞች መሠረታዊ ፍላጎቶች ለቋንቋ ትምህርትና ለሌችም ስለጠናዎች በመጪው ዓመት ከ 1.8 እስከ 3.3 ቢሊዮን ዩሮ የሚደርስ ተጨማሪ ገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል ። ሶሻል ዲሞክራትዋ

ፖለቲከኛ ኔልስ ባለፈው ማክሰኞ በርሊን ውስጥ እንደተናገሩት እነዚህ ወጪዎች ከ4 ዓመት በኋላ በጎርጎሮሳውያኑ 2019 ወደ 7 ቢሊዮን ዩሮ ከፍ ማለታቸው አይቀርም ።አሁን ወደ ጀርመን የሚገቡት ስደተኞች በሚቀጥሉት ዓመታት ሠራተኞች ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል ።ጀርመን ውስጥ መንግሥት ማህበራዊ ድጎማ የሚሰጣቸው ሰዎች ቁጥር በጎርጎሮሳዊው 2016 ፣ ከ240 ሺህ እስከ 460 ሺህ ይደርሳል ተብሎ ይገመታል ። አነዚህሥራ ያላገኙ ወይም መሥራት የማይችሉ ናቸው ። ከመካከላቸው ከ175 ሺህ እስከ 335 ሺህ የሚሆኑት መሥራት ይችላሉ ተብሎ ይገመታል ።ሚኒስትር ኔልስ በ2019 ከመንግስት ማህበራዊ ድጎማ የሚጠብቁ ሰዎች ቁጥር ወደ አንድ ሚሊዮን ከፍ እንደሚል ተናግረዋል ። ትንበያው ሃገሪቱ ይገባሉ ተብሎ የሚጠበቀውን 800 ሺህ ስደተኞች ግምት ውስጥ ያስገባ ነው ።የፌደራል ጀርመን የሠራተኛ ጉዳይ መስሪያ ቤት በሚቀጥሉት ዓመታት ሥራ ፈላጊ ስደተኞች ስለ ሥራ ምክር የሚሰጡ ድርጅቶችን ያጨናንቃሉ ብሎ ይጠበቃል ።ሚኒስትር ኔልስ ስደተኞች ወደ ሥራው ዓለም እንዲቀላቀሉ የሚያግዝ ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ አስፈላጊ ነው ይላሉ ። በርሳቸው አስተያየት ተገን ጠያቂዎች ጀርመን ውስጥ በሥራው ዓለም ተፈላጊ እንዲሆኑ ፣የጀርመንኛ ቋንቋ ችሎታ ቁልፍ መሣሪያ ነው ።ዙድ ዶይቸ ትሳይቱንግ የጠቀሰው አንድ የአውሮፓ ኤኮኖሚ ምርምር ማዕከል በጎርጎሮሳዊው በ2012 ባካሄደው ጥናት መሠረት ወደ 6.6 ሚሊዮን ለሚሆኑ የጀርመን ዜግነት ለሌላቸው የሃገሪቱ ነዋሪዎች በአጠቃላይ 22 ቢሊዮን ዩሮ ወጪ ተደርጓል ።ከ50 ዓመት በላይ የጀርመን መንግሥትና የኤኮኖሚ አማካሪ የሆኑት ሽቴፈን አንገነንድት ለለስደተኞች የሚወጣው ገንዘብ ከነርሱም የሚገኘው ጥቅም ጉዳይ የሚነሳበት ሁኔታ ግልፅ አይደለም ይላሉ ።በርሳቸው አስተያየት ወጪውንም ሆነ ጥቅሙን በትክክል ለማወቅ ያስቸግራል ።

Deutschland Brandanschlag an Asylbewerberheim in Heppenheim

ቃጠሎ የደረሰበት የሄፐንሃይም የስደተኞች መጠለያ

«ለምሳሌ ስደተኛ በዓመት 2000 ዩሮ የሚያስገባልን ከሆነ እንቀበለው አለበለዚያ እንተወው ማለት አለብን ? ለኔ በዚህ ጉዳይ በሚካሄደው ክርክር ላይ ጥርጣሬ አለኝ ። ከዚህ በተጨማሪም ለስደተኞች የምናወጣው ገንዘብና በስራው ዓለም የሚያበረክቱትን አስተዋፅኦ ለይቶ ማወቁ እጅግ አስቸጋሪ ነው ። »
አንገነንድት ወደ ዚህ ሃገር የሚመጡ ስደተኞች በተቻለ ፍጥነት በሥራ እንዲሰማሩ ለማድረግ ጥረት መደርግ እንዳለበት ይስማማሉ ።ግን ይላሉ ጀርመን ስደተኞቹን የምትቀበልበት ዋናው ምክንያትይህ እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል ።
«ሆኖም ሰዎቹን የተቀበልነው ሠራተኛ ስለምንፈልግ ሳይሆን ከለላ ሊሰጣቸው የሚገባ በመሆኑ እንደሆነ ማወቅ አለብን ። እናም ከሁሉም በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ይህ መሆን አለበት»
በሌላ በኩል በጀርመንዋ የሄሰን ፌደራዊ ክፍለ ሃገር በሄፐንሃይም ከተማ ስደተኞች የተጠለሉበት ህንፃ ዛሬ የእሳት አደጋ እንደደረሰበት ተዘግቧል ። በአደጋው 5 ሰዎች መቁሰላቸው ተነግሯል ። በዚሁ በባለ ሶስት ፎቅ ህንጻ ውስጥ ከ60 በላይ የሚሆኑ ከሶሪያ ከኢራቅ ከሶማሊያና ከኢትዮጵያ የመጡ ስደተኞች ይኖሩበታል ። የአደጋው መንስኤ ለጊዜው አልታወቀም ።

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሀመድ

Audios and videos on the topic