የጀርመን የስለላ ድርጅት ኃላፊ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 03.07.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የጀርመን የስለላ ድርጅት ኃላፊ

የጀርመን የሀገር ዉስጥ የስለላ ድርጅት ኃላፊ ሃይንስ ፍሮም በህቡዕ የሚንቀሳቀስ አፍቃሬ ናዚ ቡድንን ማንነት ለማጣራት የሚደረገዉን የስለላ ክትትልን ለማድበስበስ ተፈፀመ በተባለ ስህተት ጫና ተገፍተዉ ከሥራ ለመሰናበት ጠየቁ። መሥሪያ ቤታቸዉ

default

ሃይንስ ፍሮም

የአፍቃሪ ናዚዎችን ህዋስ በመከታተል ሂደት ተፈፀመ የተባለዉ «ቅሌት» ባለስልጣኑ በጀርመን ህግ መሠረት የጡረታ እድሜያቸዉ ሳይደርስ፤ ጡረተኛ ለመሆን ማመልከቻ እንዲያስገቡ ግድ ብሏቸዋል። ባለፈዉ ህዳር ወር ማንነቱ የተጋጠዉ አፍቃሬ ናዚ ቡድን የአስር ሰዎችን ህይወት እስኪያጠፋ ሲንቀሳቀስ የጀርመን የስለላ ሠራተኞች፤ በተለይ የሀገር ዉስጡ የስለላ መሥሪያ ቤት ባልደረቦች ሳይደርሱበት ወይም እንደሚጠረጠረዉ አንዳንዶች ሆን ብለዉ ደብቀዉት ዓመታት ተቆጥረዋል። በሶስት ሰዎች ይመራ የነበረዉ ይህ አፍቃሬ ናዚ የሽብር ቡድን አንዲት ጀርመናዊት ፖሊስን እና ዘጠኝ የዉጭ ዝርያ ያላቸዉን ሰዎች በተለያየ ጊዜ መግደሉ ይፋ ሆኗል። ቡድን ሌሎች 20 ሰዎች ላይም ጉዳት ማድረሱ ተዘግቧል። ምስላቸዉ ይፋ ከሆነዉ ከቡድኑ አባላት ከሶስቱ ሁለቱ ወንዶች ሲሆኑ ራሳቸዉን አጥፍተዋል፤ ሴቷ ግን አሁንም በህይወት መኖሯ ይታመናል።

ባለፈዉ ሳምንት ረቡዕ የፍሮም መሥሪያ ቤት የዚህን ቡድን ምንነት ያጋልጣል የተባለ ሰነድን ነዉ ማጥፋቱ የተሰማዉ። ይህም ላለፉት 12 ዓመታት በኃላፊነት በተሰማሩበት ከፍተኛ ልምድ ማካበታቸዉ የተገለፀዉን የ63ዓመቱን ሃይስ ፍሮም፤ ሥራቸዉን እንዲለቁ አስገደደ። ዘገባዎች እንደሚሉት የጠፋዉ ሰነድ የፍሮም መሥሪያ ቤት ባልደረቦች ቱሪንገን ከሚገኘዉ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤት ጋ በመሆን ከአፍቃሪ ናዚዉ ቡድን ጋ ሳይተባበሩ እንዳልቀሩ የሚያጋልጥ ነዉ ተብሎ ይታመናል።

NSU Trio

ሶስቱ የቡድኑ አባላት

ዋናዉ ጥያቄ ላለፉት አስር ዓመታት በህቡዕ እየተንቀሳቀሰ በመላ ጀርመን ግድያና ዝርፊያ ሲፈፅም የቆየዉ የሶስቱ ሰዎች ቡድን እንዴት ከጀርመን የስለላ መሥሪያ ቤት ባለሙያዎች ሊሰወር ቻለ የሚለዉ ነዉ።የአዲሱ የጀርመን ምክር ቤት የአፍቃሪ ናዚ ምርመራ ኮሚቴ ሊቀመንበር ሶሻል ዴሞክራቱ ሴባስቲያን ኤዳቲ ያነሱትም ይህኑ ጥያቄ ነዉ፤

«ማዕከላዊዉ ጥያቄ የሶስት ሰዎች ጥምረት የሆነዉ አሸባሪ ቡድን ለአስር ዓመታት ያህል በህቡዕ በጀርመን ሪፑብሊክ እየተዟዟረ ሲገድልና ሲዘርፍ ከስለላ ሰዎች እንዴት መሠወር ቻለ የሚለዉ ነዉ። የፌደራል የስለላ ባለሙያዎችና የፀጥታ ኃይላት የእነዚህን ሶስት ሰዎች ፈለግ ተከታትለዉ ያልደረሱበት ምክንያት ምድነዉ ነዉ? ስለዚህ ጉዳይ የፌደራሉ የሀገር ዉስጥ የስለላ መሥሪያ ቤት የሚያዉቀዉ ካለ እኔም ማወቅ እፈልጋለሁ።»

የስለላ መሥሪያ ቤቱ ለጠፋዉ ህይወትና ለተፈፀመዉ ዝርፊያ ምክንያት የሆነዉ ቡድን ማንነትና ከነማን ጋ ግንኙነት እንዳለዉ በቀጣይ መረጃ ያቀርባል ተብሎ ሲጠበቅ መረጃ ማጥፋቱ አንዳንዶች እንደሚሉት ብዙም አላስገረማቸዉም። ይህ ደግሞ የሀገሪቱን የስለላ መሥሪያ ቤት ተዓማኒነት የሚያሳጣ ነዉ። የዶቼ ቬለ የጀርመንኛዉ ቋንቋ ባልደረባ ያስፐር ባረንበርግ ስለሁኔታዉ ያነጋገራቸዉ የጀርመን የሀገር ዉስጥ ሚኒስትር ሃንስ ፔተር ፍሪደሪሽ ያንን ተዓማኒነት መመለስ እንደሚገባ ገልፀዋል፤

Deutschland Innenminister Hans-Peter Friedrich

ሃንስ ፔተር ፍሪደሪሽ

«አዎ ይሄ በትክክል በመገናኛ ዘዴዎች መገለጡ ነዉ ነገር ግን ከሁሉም በላይ የምክር ቤት እንደራሴዎችም በመጀመሪያ ዘገባቸዉ ላይ ገልፀዉታል። ከሀገር ዉስጥ የስለላ ድርጅት መረጃዎች ፈልገን ነበር፤ በዚያ ምትክ ግን ሰነዶች ጠፍተዋል። ይህ በርግጥ ተዓማኒነትን የሚጥስ ነዉ። ስለዚህ ይህን ተዓማኒነት መልሰን መገንባት ይኖርብናል።»

የስለላ መሥሪያ ቤቱ ኃላፊ በዚህ ወር መጨረሻ ከሥራቸዉ በጡረታ ለመሰናበት ይዘጋጁ እንጂ ጉዳዩ በእሳቸዉ መልቀቅ ብቻ እንደማያከትምና የሚያነካካዉም እንደሚበዛ ነዉ የተገመተዉ። ይህን ጉዳይ የሚከታተሉ አካላት ፖሊስን ጨምሮ የምርመራ ጥረታቸዉን የሚያደናቅፍ ርምጃ እንደገጠማቸዉ ይፋ አድርገዋል። ለወራት ከተሰነዘረ ትችት በኋላ ሃይንዝ ፍሮም ሥራቸዉን ለመልቀቅ የተዘጋጁ ከፍተኛ ባለስልጣን ሲሆኑ፤ ባለፈዉ ጥር ወር በስለላ ተቋሙ የቀኝ አክራሪዎችን የሚከታተለዉ ዘርፍ ሃላፊ አርቱር ኸርትቪግ በሌላ ሰዉ ተተክተዋል። ይህንና መሠል ሁኔታዎችን በመመርመርም የጀርመን የሀገር ዉስጥ ሚኒስቴር ከነገ በስተያ ሐሙስ ዝርዝር ዘገባ እንደሚያቀርብ ይጠበቃል።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic