የጀርመን የስለላ ቅሌት | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 19.08.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የጀርመን የስለላ ቅሌት

የጀርመን ፊደራል የስለላ መሥሪያ ቤት ቱርክን ሲሰልል ቆይቷል የቀድሞዋንና የአሁኑን የአሜሪካን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስልኮች ጠልፏል መባሉ ማነጋገሩን ቀጥሏል ። የጀርመን ፖለቲከኞች እስካሁን በጉዳዩ ላይ ምንም ያልተናገረው የሐገሪቱ መንግስት ማብራሪያ እንዲሰጥ ግፊት እያደረጉ ነው ።

የአሜሪካን ብሄራዊ የሥለላ መሥሪያ ቤት በምህፃሩ NSA የጀርመን መራሂተ መንግስት የአንጌላ ሜርክልን ስልክ መጥለፍን ጨምሮ በጀርመን ዜጎች ላይ አካሂዷል የተባለው ስለላ ለብዙ ወራት ጀርመናውያንን ሲያነጋግር የቆየ ጉዳይ ነበር ። ከዚያ በኋላም ጀርመን ውስጥ በጀርመን የስለላ ድርጅት ባልደረባ በአሜሪካን ባለሥልጣናት ትዕዛዝ ተፈፀመ በተባለው ስለላ ሰበብ ጀርመን ከአንድ ወር በፊት ከበርሊን የአሜሪካን ኤምባሲ አንድ ከፍተኛ የአሜሪካን የስለላ ድርጅት CIA ሃላፊን ከሃገርዋ እስከማባረር ደርሳለች ። አነዚህ አሜሪካን ፈጸመቻቸው የተባሉት ስለላዎች የቅርብ ወዳጅ በሆኑት በሁለቱ ሃገራት መካከል ለጊዜውም ቢሆን ያለመተማመን መንፈስ አሳድሮ ነበር ። የጀርመን ፖለቲከኞች በወቅቱ ወዳጅ ከምትባለው ከአሜሪካን የማይጠበቅ ያሉትን ስለላ ኮንነው አሜሪካን አሻፈረኝ ያለችውን ያለመሰለል ውል እንድትፈርም ሲወተውቱ ቆይተዋል ። የስለላው ቅሌት ይፋ እንደሆነም የጀርመን መራሂተ መንግሥት መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል በሰጡት አስተያየት ድርጊቱን ነቅፈውት ነበር ።

«በወዳጆች መካከል የሚካሄድ ስለላ ፍፁም ተቀባይነት አይኖረውም »

በወዳጅ አሜሪካን ተሰለልኩ ስትል የከረመችው ጀርመን አሁን ደግሞ በተራዋ የሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ቃል ኪዳን ድርጅት በምህፃሩ NATO አባል የሆነችውን ቱርክን እንደምትሰልል እንዲሁም የአሜሪካን ከፍተኛ ባለስልጣናትን ስልክ እንደጠለፈች 3 የጀርመን መገናኛብዙሃን በጋራ ያካሄዱት ምርመራዊ ዘገባ አጋልጧል ።ዙድ ዶቸ ትሳይቱንግ የተባለው ጋዜጣ እንዲሁም NDR WDR የተባሉት ሁለት የጀርመን የራድዮና የቴሌቪዥን ድርጅቶች በጋራ ካካሄዱት ምርመራ በኋላ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ያወጡት ዘገባ የጀርመን የሥለላ መስሪያ ቤት የቀድሞዋን የአሜሪካን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሂላሪ ክሊንተንን ቢያንስ አንድ የስልክ ንግግር እጎአ በ2012 መቅረፁን አጋልጧል ። የተቀረፀው የክሊንተን ንግግር ክሊንተን በአሜሪካን መንግስት አውሮፕላን ውስጥ ሆነው ከቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ ኮፊ አናን ጋር ያካሄዱት የስልክ ንግግር መሆኑ ተገልጿል ።የጀርመን መንግስት ምንጮች የስልክ ንግግሩ በመካከለኛው ምሥራቅ ላይ ያተኮረ የስለላ መረጃ ስብሰባ ወቅት በስህተት የተቀረፀ እንጂ በዋሽንግተንዋ ከፍተኛ ዲፕሎማት ላይ ስለላ ለማካሄድ ታቅዶ የተከናወነ አለመሆኑን ማስታወቃቸው በዘገባው ተመልክቷል።

እነዚሁ ምንጮች የጀርመን መንግሥት የተቀረፀው ንግግር ወዲያውኑ እንዲሰረዝ አለማደረጉ ግን ትልቁ ስህተት መሆኑንን መጠቆማቸው ተሰምቷል ።ስለ ጉዳዩ የጀርመን መንግስትም ሆነ የዋይት ሃውስ ብሄራዊ የፀጥታ ምክር ቤት ቃል አቀባይ ምንም ዓይነት አስተያየት ከመስጠት እንደተቆጠቡ ነው ። የተቀረፀው የክሊንተን የስልክ ንግግር ለአሜሪካን ብሄራዊ የስለላ ድርጅትም ይሠራል ተብሎ በመጠርጠሩ ባለፈው ወር የተያዘው ማርኩስ(R)አር የተባለው የጀርመን የስለላ ድርጅት ባልደረባ ለዋሽንግተን አሳልፎ ከሰጣቸው መረጃዎች መካከል አንዱ መሆኑን መገናኛ ብዙሃኑ ዘግበዋል ። በዚሁ ዘገባ ማርኩስ R ለአሜሪካውያን ከሰጣቸው ሰነዶች ውስጥ የጀርመን መንግሥት ፣ ስም ሳይጠቅስ አንድ የሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ቃል ኪዳን ድርጅት አባል አገርን እንዲሰልል ለጀርመን የስለላ መሥሪያ ቤት ያስተላለፈው ትዕዛዝ ይገኝበታል ። በዘገባው የመረጃው ምንጭ ግን አልተጠቀሰም ።ሌላው ታዋቂ የጀርመን መፅሄት ዴር ሽፒግል ደግሞ የአሁኑ የአሜሪካን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የጆን ኬሪ የስልክ ንግግርም እጎአ በ2013 መቀረፁን የሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ቃል ኪዳን ድርጅት NATO አባል በሆነችው በቱርክ ላይ ጀርመን ለዓመታት ስለላ ስታካሂድ መቆየቷን አጋልጧል ። በአሁኑ ጊዜ የጀርመን የስለላ መሥሪያ ቤት ፣ዩናይትድ ስቴትስ ታከናውናለች በሚባለው ደረጃ ስልታዊ የስለላ ዘዴ ተግባራዊ ማድረግ አለማድረጉ እንዲሁም የወዳጅ አገሮችን ፖለቲከኞች መሰለል አለመሰለሉ ማነጋገሩ እንደቀጠለ ነው ። የጀርመን ፖለቲከኞች ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ይፋ በሆኑት በነዚህ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ አስተያየቶችን እየሰነዘሩ ነው ። ይህ እውነት ሆኖ ከተገኘ አሜሪካን ስትሰልለን ቆይታለች በማለት ሲወነጅል የነበረውን የጀርመንን መንግሥት አንገት የሚያስደፋ መሆኑ እንደማይቀር የጀርመን ፖለቲከኞች እየተናገሩ ነው ። በጀርመን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሃገር ውስጥ ጉዳዮች ኮሚቴ ሊቀ መንበር የክርስቲያን ዴሞክራቶች ህብረት ፓርቲ በምህፃሩ CDU አባል ቮልፍጋንግ ቦስባህ ድርጊቱ ተፈፅሞ ከሆነ ለአሜሪካውያን ትልቅ ስጦታ ይሆናል ይላሉ ።

«የቀድሞዋ የአሜሪካን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክሊንተንም ሆነ በኋላም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ በስልክ ያደረጓቸው ንግግሮች ተጠልፈው ከሆነ በርግጥ ይህ ስለላን በሚመለከት ከአሜሪካን ብሄራዊ የስለላ ድርጅት NSA ጋር ከተደረገው መደበኛ ስምምነት የፍፁም የተለየ ነው ለነገሩ ይህ ዜና ለአሜሪካውያን ከሰማይ እንደወረደ መና የሚቆጠር ነው ። የጀርመን ፌደራል ሪፐብሊክ አሜሪካ ሰለለች ወይም በሚስጥር አዳመጠችን እያለ ሲከስ ቆይቶ ራሱ እያደረገው ነው ለማለት ይመቻቸዋል ።»

ከሁሉም አስተያየት ለመስጠት የፈጠኑት ተቃዋሚዎች የመንግሥትን ተግባር ነቅፈዋል ። የተቃዋሚው የጀርመን የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ ፖለቲከኛ ኮንስታንቲን ፎን ኖትስ መንግሥትራሱ የሚኮንነውን መልሶ ራሱ በማድረጉ ወቅሰዋል ።

« ፍፁም የማይናወጥ አቋም ያለው መስሎ የያዘው ግን መንታ አቋም ነው ።»

ጀርመንን የሚመራው የጥምሩ መንግሥት አባላት ግን ይህን ወቀሳ አይቀበሉም ። የአሜሪካን ብሄራዊ የስለላ ድርጅት NSA በጀርመናውያን ላይ አካሂዷል የተባለውን ስለላ ለማጣራት በጀርመን ምክር ቤት ስር የተቋቋመው ኮሚቴ ሊቀ መንበር የክርስቲያን ዴሞክራት ህብረት ፓርቲ አባል ፓትሪክ ዜንስቡርግ ጀርመን በተለይ በውጭ ፖለቲከኞች ላይ ያነጣጠረ ስለላ እንደማታካሂድ፣ ሆኖም ስለላ አስፈላጊ የሚሆኑባቸው ሁኔታዎች መኖራቸውን አስረድተዋል ።በርሳቸው አስተያየት ለምሳሌ ቱርክ ላይ ስለላ መካሄዱ ጠቃሚ ነው ።

«እጅግ አሳሳቢና አስቸጋሪ በሆኑ ሃገራት ፣ ግጭት በሚከሰትባቸውም አካባቢዎች የስለላ ሥራዎችን ማከናወን ትክክለኛ ተግባር ነው ። እንደሚመስለኝ በአሁኑ ጊዜ በግልጽ እንደሚታየው በቱርክና በኢራቅ አካባቢ ስለላ ማካሄድ አስፈላጊ ነው ።»

በጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የክርስቲያን ዲሞክራቶች ህብረት ፓርቲ CDU ተወካዮች ምክትል ሊቀ መንበር አንድሪያስ ሾክንሆፍም ቱርክ ላይ ይካሄዳል የተባለው ስለላ ጠቃሚ መሆኑን ነው የሚናገሩት ። ሾክንሆፍ ጀርመን

ውስጥ 3 ሚሊዮን ቱርኮች እንዳሉ አስታውሰው አሸባሪ ተብለው የተፈረጁ አንዳንድ የቱርክ ድርጅቶች እንዳሉና እነዚህ ድርጅቶችም ከቱርክ በኩል ምን ዓይነት ድጋፍ እንደሚደርግላቸው በተቻለ አቅም ለማጣራት ይሞከራል ብለዋል ። በጀርመን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተቃዋሚው የግራዎቹ ፓርቲ የህዝብ ተወካዮች ተጠሪ ግሬጎር ጊዚ በቱርክ ላይ ስለላ መካሄዱ አግባብ አይደለም ይላሉ

«ቱርክ የNATO አባል መሆኗ የታወቀ ነው ።ቱርክ እርግጥ ነው የIS አሸባሪዎች ኢራቅ ውስጥ እንደፈለጉ ሲዘምቱ ን ዝም ብላ በመመልከቷ ከፍተኛ ተቃውሞ አለኝ ።ነገር ግን ይህ ርስ በርስ ለመሰላለል ምክንያት አይደለም ። ይህን መረዳት ያዳግተኛል ።እኔ እንደሚመስለኝ በዓለም ዙሪያ የስለላ ድርጅቶች ተግባር ቅጥ አጥቷል ።»

እጎአ ከ2009 ዓም አንስቶ የጀርመን ዋነኛ የስለላ ዒላማ ሆና መቆየቷ የተነገረው ቱርክ ትናንት በአንካራ የጀርመን አምባሳደርን ጠርታ ስለ ጉዳዩ ማብራሪያ ጠይቃለች ። የቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በጀርመን መገናኛ ብዙሃን የወጣው ዘገባ ፍፁም ተቀባይነት እንደሌለው አስታውቆ ስለዚሁ ዘገባ የጀርመን ባለሥልጣናት ይፋና አጥጋቢ ማብራሪያ እንዲሰጡ ጠይቀዋል ።ቱርክ በዘገባው የጀርመን መንግሥት ያካሂዳል የተባለው ስለላ በርግጥ የሚፈፀም ከሆነ በአስቿኳይ እንዲቆምም ጠይቃለች ። የጀርመን መንግሥት አሁንም ቱርክ ላይ ስለላ ያካሂዳል ፣ የአሜሪካን የቀድሞዋንም ሆነ የአሁኑን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስልክ ጠልፏል ስለመባሉ ምንም ዓይነት አስተያየት አልሰጠም ።የ CDU ውቦስባህ ግን የጀርመን መንግሥት ሁሉንም ነገር በግልጽ ቢያሳውቅ ጥሩ ነው ይላሉ ።

«የጀርመን ፌደራል መንግሥት እጎአ ከ2009 አንስቶ ከስምምነት ውጭ ሲያካሂድ የቆየውን ስለላ አሳማኝ በሆነ ምክንያት በምን ያህል መጠን ሲያካሂድ እንደቆየ ቢገልፅ ምንኛ ጥሩ ነበር ። ምነው ቢሉ ተደጋግሞ የቃል ኪዳን ተጓዳኞች እርስ በርስ መሳለል የለባቸውም ይባላልና ።»

መንግሥት ስለ ጉዳዩ አጠቃላይ መግለጫ ባይሰጥም የጀርመን ጥምር መንግስት አካል የሆነው ጀርመን ሶሻል ዲሞክራቶች ፓርቲ ዋና ፀሃፊያስሚን ፋሂሚ በጎረቤት ሶሪያና ኢራቅ በሚካሄዱ ግጭቶችና የአሸባሪዎች እንቅስቃሴ ሳቢያ ቱርክ ውስጥም የኔቶ የጦር አባላት እንደመስፈራቸው የጀርመን የስለላ ድርጅት በቱርክ መረጃዎችን ቢሰበስብ አያስገርምም ሲሉ ትናንት በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል ።

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic