የጀርመን የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ማሕበርና ኢትዮጵያ | ኢትዮጵያ | DW | 08.05.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የጀርመን የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ማሕበርና ኢትዮጵያ

ዋና ጽ/ቤቱ በሰሜን ጀርመን በገኧቲንገን ከተማ የሚገኘው በዓለም ዙሪያ በጭንቅ ላይ ለሚገኙ ሕዝቦች ተቆርቋሪ መሆኑ የሚነገርለት ማሕበር(GFBF) በኢትዮጵያ ያለውን ወቅታዊ የሰብአዊ መብት ይዞታ አስመልክቶ ትናንት ጋዜጣዊ መግለጫ አወጣ።

default

ማሕበሩ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም በኦሮሚያ መስተዳድር በተለያዩ ዩንቨርስቲዎችና ት/ቤቶች ከመጋቢት ወር ማለቂያ ገደማ አንስቶ ተቃውሞ በማቅረባቸው በአጠቃላይ ፤ ቢያንስ 80 ያህል ተገድለዋል። ባለፈው ሳምንት ብቻ፤ ከ 50 በላይ ሲገደሉ 300 ያህል ሰዎች ቆስለዋል። ከ 2,000 በላይ ታፍሰው ታሥረዋል ሲል ገልጿል። ዑልሪኽ ዴሊየስ ነገም በርሊን ውስጥ ከመራኄ መንግሥት ጽ/ቤት ፊት ለፊት ሰልፍ ይደረጋል ብለዋል።

የማሕበሩ የአፍሪቃ ጉዳዮች ሄር ዑልሪኽ ዴልዬስ፣ «የተዛመተው የኃይል እርምጃ ባስቸኳይ ሊቆምና የታሠሩት ወጣቶችም ያለምንም ማመንታት በቶሎ ሊፈቱ ይገባል ነው ያሉት። ማሕበራቸው ፣ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ያቀረበው መልእክት ለማን እንደሆነ ፣ ማንን ቤት እንደተማጸነ ጠይቄአቸው ሲመልሱ--

«በዚያ ሰብአዊ መብት ጥሰት የተፈጸመው ዓለም አቀፍ ትኩረት ሳይሰጠው ነው። በአርግጥ ምን እንደተካሄደ ጭብጡን ማወቅ ይኖርብናል። የዐይን ምሥክሮችን ቃል መነሻ በማድረግ በማድረግም ነው ማሕበራችን መግለጫ ያወጣው።በጀኔቭ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን አጣሪ ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ይልክ ዘንድ ጠይቀናል። የዚህን የኃይል እርምጃ መነሻ ምክንያት በግልጽ መርምሮ ማሳወቅ ያሻል። በደረሰን መረጃ መሠረት ፤ ተይዘው የታሠሩት ፤ በአመዛኙ የኦሮሚያ ዩንቨርስቲዎችና ሌሎችም ት/ቤት ተማሪዎች 2,000 ገደማ እንደሚሆኑ ነው የተገመተው።ሁሉም ባስቸኳይ እንዲፈቱ ያደርግ ዘንድ ጠይቀናል። ተማሪዎችቹ ያደረጉት ቢኖር፤ አከራካሪ የሆነው፤ ያዲስ አበባ ከተማ የመስፋፋት እቅድ በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞ ማሳየት ነበረ። ለምን በዚህ ምክንያት ይታሠራሉ?»

ወደ አውሮፓ የሚላክ አበባ ለማማረት ሲባል ከዚህ ቀደም ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች ፤ ባለፉት ዓመታት፤ ከአዲስ አበባ ዙሪያ ተፈናቅለዋል ያሉት ዑልሪኽ ዴልዬስ፣ ለሃገራቸው የጀርመን መንግሥትና ፤ ለአውሮፓ ሕብረት ያላቸውን መልእክት ሲያስረዱ--

«ይህ የሰብአዊ መብet ጥያቄ በግልጽ እንዲነገር ነው የምንፈልገው። ኢትዮጵያ ላካባቢው አገሮች ባላት «የማረጋጋት ሚና» ሳቢያ ችላ ሊባል አይገባም ነው የምንለው። የአውሮፓ ሕብረት መንግሥታትም አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙ አምባሳደሮቻቸው በኩል ፣ የታሠሩት እንዲፈቱ ጥያቄ ያቀርቡ ዘንድ ነው የምንጠይቀው።»

በዓለም ዙሪያ በተለያዩ አገሮች ፣በጭንቅ ላይ ለሚገኝ ማንኛውም ሕዝብም ሆነ ጎሳ ተቆርቋሪ መሆኑን የሚገልጸው የዚህ ማሕበር፤ የአፍሪቃ ጉዳዮች ተመራማሪና ተጠሪ ዑልሪኽ ዴልዬስ፣ አዲስ አበባ አሁን ካላት 54,000 ሄክታር መጠን፤ በ 1,1 ሚሊዮን ሄክታር ሰፋ ለማለት ማቀዷ፣ ተማሪዎችን ብቻ ስለማይመለከት ዑደታዊ የኃይል እርምጃ እንዳያስከትል ሥጋት አለን ይላሉ። የከተማ የማስፋፋት እቅዱን ዴልየስ እንዳሉት ፤ የኦሮሞ ፓርቲዎችና ድርጅቶች ብቻ ሳይሆኑ ፣አዲስ በሆነ ክሥተት የመንግሥት አካላት የሆኑ የኦሮሞ ድርጅቶችም አልተቀበሉትም።

የዩናይትድ ስቴትስ ው ጉ ሚ ጆን ኬሪ፤ አዲስ አበባ በቆዩበት ጊዜ፤ ስለጋዜጠኞችና የደረ ገጽ ጸሐፍት እንዲሁም የታቃውሞ ፓርቲዎች ፖለቲከኞች ስለመታሠራቸው ፤ ስለኦሮሞ ተማሪዎች ተቃውሞም ከቅርብ መረጃ ሳያገኙ እንዳልቀሩ ይታሰባል። በአንድ በኩል ለሰብአዊ መብት መቆርቆር ስለመኖሩ ሲነገር እንደማለን፤ በሌላም በኩል ለኤኮኖሚና ለስልታዊ አካባቢያዊ ጥቅም ማሰብ ማሰላሰሉ አለ፤ ሁለት የተለያዩ ጉዳዮችን እንዴት ማስታረቅ ይቻላል?

«በግልጽ መታወቅ ያለበት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ በኃይል ርምጃ በሚታረቅ ፀጥታ መመካት ካለ ለአካባቢው ሃገራት መረጋጋት አይበጅም። ኢትዮጵያ የሚመጥን ዴሞክራቲክ ለውጥን ፣ መሠረታዊ የሰብአዊ መብትን አከባበር የሲቭሎችን መብት፤ የተቃውሞ ሰልፍ የማድረግን መብት ጭምር መቀበል ይኖርባታል። የሰላ ሒስ ወይም አስተያየት በመሠንዘ,ራቸው ባቻ ሰዎች ሊታሠሩ አይገባም። ይህን ለኢትዮጵያ መንግሥት ማሳወቅ ያሻል። አለበለዚያ ከኢትዮጵያ ጋር የሚደረግ ትብብር ፋይዳቢስ ነው የሚመስለኝ። ሰብአዊ መብትን በቦታ ለያይቶ መመዘን አይቻልም። ሱዳንንና ደቡብ ሱዳንን እያስጠነቀቁ፣ ኢትዮጵያን የአካባቢው አረጋጊ ኃይል ናት በሚል ማወደስ የማይሆን ጉዳይ ነው።ሰብአዊ መብት በእጅጉ እየተጣሰ ሊቀጥል የሚገባው አይደለም። ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ፤ ለራሱ ጥቅም ሲል በኢትዮጵያ ለሰዎች ሰብአዊ መብት፤ መቆም ይጠበቅበታል። ከዚህም በመነሣት፣ ነገ ከጀርመን መራኂተ-መንግሥት ጽ/ቤት ፊት ለፊት ከኢትዮጵያውያን ጋር ስልፍ እናደርጋለን። ይህ ሰብአዊ መብትን ዐቢይ ርእስ ያደረገ የኢትዮጵያዊ ጉዳይ ችላ ሊባል አይገባምና!»

ተክሌ የኋላ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic