የጀርመን የምርጫ ስርዓት | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 14.09.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የጀርመን የምርጫ ስርዓት

ከጀርመን መራጮች ከአንድ ሦስተኛው በላይ እድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ ነው። እድሜያቸው የገፋው እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች በምርጫው ውጤት ላይ የሚያሳድሩት ተጽእኖ ከፍተኛ ነው። አቶ ክፍለማርያም እንደሚሉት በአንጻሩ ወጣቶች ደግሞ ለምርጫ እምብዛም ትኩረት አለመስጠታቸው ከጀርመን የምርጫ ተግዳሮቶች አንዱ ነው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 12:47

የጀርመን የምርጫ ስርዓት

ጀርመናውያን በጎርጎሮሳዊው መስከረም 26 ቀን 2021 ዓም የምክር ቤት ተወካዮቻቸውን ይመርጣሉ። ጥቂት ቀናት ለቀረው ለዚህ ምርጫ እጩ ተወዳዳሪዎች በተለያዪ ቦታዎች ቅስቀሳዎችና የምርጫ ዘመቻዎች እያካሄዱ ነው። የእጩ ተወዳዳሪዎች ምስሎችና ዓላማዎቻቸው የሰፈሩባቸው ፓስተሮችም በተለያዩ ስፍራዎች ተለጥፈዋል።በምርጫው የሚወዳደሩ ፓርቲዎች  ቢመረጡ ሊያከናውኑ ያቀዷቸውን ተግባራት የሚጠቁሙ መረጃዎችን ህዝብ በብዛት በሚገኝባቸው የከተማ ክፍሎች ፣እየሰጡ ነው። የሦስት ዋና ዋና ፓርቲዎች  እጩ መራሄ መንግስቶችም ሁለት ጊዜ የቴሌቪዥን ክርክሮችን አካሂደዋል።የዛሬው አውሮጳና ጀርመን ዝግጅታችን በጀርመን ምርጫ በተለይም በሀገሪቱ የምርጫ ስርዓት ላይ ያተኩራል። 

የጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት በጀርመንኛው መጠሪያው ቡንደስታግ ምርጫ በየአራት ዓመቱ ነው የሚካሄደው።በዚህ አገር አቀፍ  ምርጫም  ጀርመናውያን ሁለት ድምጽ ነው

የሚሰጡት። አንደኛው ድምጽ መራጮች ከየአካባቢያቸው በጀርመን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፣ለሚወክሏቸው እንደራሴዎቻቸው የሚሰጡት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የሚፈልጉትን ፓርቲ የሚመርጡበት ድምጽ ነው።በጀርመን 299 የምርጫ ክልሎች ይገኛሉ። እያንዳንዱ የምርጫ ክልል 250 ሺህ ነዋሪዎችን ያካትታል። በምርጫ ክልሎቹ አብላጫ ድምጽ ያገኙት አሸናፊዎች በምክር ቤቱ ወንበር ይይዛሉ።የህዝባቸው ቁጥር ከፍተኛ የሆነ የጀርመን ፌደራል ክፍለተ ሃገር የምርጫ ክልሎች ቁጥር ፣ አነስተኛ ህዝብ ካላቸው ጋር ሲነጻጸር ከፍ ይላል። እነዚህ ግዛቶች ወደ ቡንደስታግ የሚልኳቸው ተወካዮች ቁጥርም አነስተኛ የምርጫ ክልል ካላቸው የበዛ ነው የሚሆነው። ግለሰቦችም ቢያንስ የ200 ደጋፊዎችን ፊርማ ካሰባሰቡ በምርጫው መወዳደር ይችላሉ። አቶ ክፍለ ማርያም ገብረ ወልድ 50 ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ ጀርመን ኖረዋል። ከፍተኛ ትምህርታቸውን እዚሁ ጀርመን ነው የተከታተሉት። የፖለቲካ ሳይንስና የልማት ምሁር እንዲሁም ጋዜጠኛ ናቸው።ርሳቸው እንደሚሉት ቀጥተኛ በሚባለው የጀርመን የምርጫ ስርዓት ህዝቡ ሁለት ድምጽ እንዲሰጥ የተደረገው ካለፈው የጀርመን አስከፊ ታሪክ ትምህርት በመውሰድ ነው።

የጀርመን ምክር ቤት 598 መደበኛ መቀመጫዎች አሉት ከነዚህ መቀመጫዎች ግማሹ የሚሞላው ህዝቡ በሚሰጠው ሁለተኛ ድምጽ ውጤት መሰረት ነው።ለእጩ ተወዳዳሪዎች ሳይሆን ለፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሰጠው ይህ ድምጽ እያንዳንዱ የፖለቲካ ፓርቲ በቡንደስታግ የሚያገኘውን የወንበር ብዛት ይወስናል።በምርጫው የሚወዳደሩ ፓርቲዎችም በሚያካሂዱት ጉባኤ የእያንዳንዱን ፌደራል ክፍለ ሀገር እጩ ዝርዝር አቅርበው መቀመጫዎቹን ይይዛሉ። ሆኖም መራጮች በምክር ቤቱ ፣ማን የመረጡትን ፓርቲ ወክሎ መቀመጫ እንደሚያገኝ ግን አስቀድመው ማወቅ አይችሉም ። የጀርመንን ምርጫ ልዩ ከሚያደርጉት ጉዳዮች አንዱ በአንደኛው ድምጽ ለሚፈልጉት ፓርቲ እጩ ተወዳዳሪ ድምጻቸውን የሚሰጡት መራጮች በሁለተኛው ድምጽ ደግሞ ሌላ ፓርቲ እንዲመርጡ እድል መስጠቱ ነው።ለምሳሌ በአካባቢው ለሚወዳደር የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲ እጩ የመጀመሪያውን ድምጹን የሰጠ መራጭ ፣ሁለተኛውን

ድምጽን  ከዚህ ፓርቲ ጋር ተጣምሮ ሊመራ ለሚችለው ለነጻ ዴሞክራቶች ፓርቲ  የመስጠት እድል ይኖረዋል።

የጀርመን ፌደራል ስታትስቲክስ ጽህፈት ቤት እንዳስታወቀው በመስከረም አጋማሹ የጀርመን ሀገር አቀፍ ምርጫ እድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆነ 60.4 ሚሊዮን ዜጎች መምረጥ ይችላሉ።ከመካከላቸው 31.2 ሚሊዮኑ ሴቶች 29.2 ሚሊዮኑ ደግሞ ወንዶች ናቸው።ከነዚህ ውስጥ 2.8 ሚሊዮኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ድምጽ የሚሰጡት። ከጀርመን መራጮች ከአንድ ሦስተኛው በላይ እድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ ነው። በቁጥር የሚያመዝኑትና በምርጫም በንቃት የሚሳተፉት እድሜያቸው የገፋው እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች በምርጫው ውጤት ላይ የሚያሳድሩት ተጽእኖ ከፍተኛ ነው። አቶ ክፍለማርያም እንደሚሉት በአንጻሩ ወጣቶች ደግሞ ለምርጫ እምብዛም ትኩረት አለመስጠታቸው ከጀርመን የምርጫ ተግዳሮቶች አንዱ ነው።

የጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት መቀመጫ 598 ቢሆንም በየአራት ዓመቱ በሚካሄድ ምርጫ ቁጥሩ ሊጨምር ይችላል።ለምሳሌ የተሰናባቹ  ምክር ቤት መቀመጫ ብዛት 709 ነው። የጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት መቀመጫ ቁጥር በየምርጫው ለምን ይለያያል? አቶ ክፍለ ማርያም መልስ አላቸው። በጀርመን የምርጫ ስርዓት ፣ተወካዮቻቸውን በቀጥታ የሚመርጡት ጀርመናውያን መሪያቸውን ግን በቀጥታ አይመርጡም። የጀርመን መራሄ መንግሥት የሚመረጠው የህዝብ እንደራሴዎች በሚስጥር በሚሰጡት ድምጽ ነው። ከ12 ቀናት በኋላ በሚካሄደው የጀርመን ምርጫ ለ16 ዓመታት ጀርመንን የመሩት አንጌላ ሜርክል አይወዳደሩም። ምርጫው እርሳቸውን የሚተካውን መሪ ይወሰናል። ሦስት ዋና ዋና የጀርመን የፖለቲካ ፓርቲዎች ማለትም የሜርክል ፓርቲ የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት በጀርመንኛው ምህጻር ሴ ዴ ኡ መሪ  አርሚን ላሼት፣ የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ በምህጻሩ ኤስ ፔ ዴ መሪ ኦላፍ ሾልትስ፣ እንዲሁም የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ ሊቀ መንበር አነሌነ ቤርቦክ በእጩ መራሄ መንግሥትነት ይወዳደራሉ።የትኛው ፓርቲ አሸንፎ ከማንኛው ፓርቲ ጋር ተጣምሮ የሚመሰርተው መንግሥት መስከረም 16 ቀን 2014 ዓመት በሚካሄደው ምርጫ ውጤት ይወሰናል።

ኂሩት መለሰ

እሸቴ በቀለ 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች