የጀርመን የመ/ሚኒስትር የማሊ ጉብኝት | አፍሪቃ | DW | 05.04.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የጀርመን የመ/ሚኒስትር የማሊ ጉብኝት

የጀርመን የመከላከያ ሚኒስትር ለጉብኝት ማሊ ገብተዋል። ጀርመን ከ200 የሚበልጡ ወታደሮች ማሊ ዉስጥ አሏት። የመከላከያ ሚኒስትር ዑርዙላ ፎን ደር ላይን በተመድ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ሥር የተሠማሩት የጀርመን ወታደሮች የሚገኙባት ሰሜን ማሊ የምትገኘዉ ጋኦ ዛሬ ገብተዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:51

ፎን ደር ላየን እና ኩሊባሊ

የጀርመን ወታደሮች ከሁለት ወራት በፊት ማሊ መግባት ጀምረዋል። እስከመጪዉ ሰኔም ቁጥራቸዉ በእጥፍ ይጨምራል።

የጀርመን የመከላከያ ሚኒስትር ዑርዙላ ፎንደር ላይን የጀርመን ወታደሮች ለሰላም ማስከበር ተልዕኮ በሰፈሩበት የሰሜን ማሊ ግዛት ሲደርሱ ከተደረገላቸዉ ወታደራዊ አቀባበል በተጨማሪ ኒሻንም ተሸልመዋል። ሽልማቱን የማሊዉ አቻቸዉ ቲማን ኩሊባሊ ራሳቸዉ ናቸዉ በአካል ተገኝተዉ ያበረከቱላቸዉ። ኩሊባሊ በዚሁ አጋጣሚ ባደረጉት ንግግርም ጀርመን ለምታደርገዉ ተሳትፎ ምሥጋና አቅርበዋል። የማሊ ወታደሮችም በሚያገኙት ወታደራዊ ስልጠና መሻሻል እንዳሳዩ አመልክተዋል።

«ከ2013 ዓ,ም ጀምሮ የማሊ ጦር ሠራዊት ከፍተኛ መሻሻሎችን አሳይቷል።»

ቀደም ሲል የማሊን ሰሜናዊ ክፍል ቅጥር ታጣቂ ተዋጊዎች፤ ፅንፈኛ ሙስሊሞች፤ እንዲሁም የቱዋሬግ አማጽያን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረዉት ነበር። ፈረንሳይ በወቅቱ የከፋ አደጋ እንዳይደርስ ወታደሮቿን ወደ ስፍራዉ አዘመተች። የተመድ በበኩሉ የማሊ የሰላም አስከማሪ ተልዕኮ በምህፃሩ ሚኑስማንን አዋቅሯል።

የአዉሮጳ ኅብረት እራሱን እንዲከላከል የማሊ መንግሥት ወታደሮችን ያሰለጥናል። እስካሁንም 8000 የሚሆኑትን አሰልጥኗል። ጀርመንም ለመንግሥታቱ ድርጅት የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ሚኑስማን 200 ወታደሮቿን ልካለች። የጀርመን ምክር ቤት ቡንደስታኽ እስከ 650 ወታደሮችን በሰላም ማስከበሩ ተልዕኮ ለማሰማራት ፈቃድ ሰጥቷል። የሚኑስማን ተልዕኮ መጠናከር ለማሊ ብቻ ሳይሆን ለአዉሮጳ ሃገራትም አስፈላጊ እንደሆነ ነዉ ፎን ደር ላይን ያመለከቱት፤

« ይኸው የምዕራብ አፍሪቃ አካባቢ የሚረጋጋበት ሁኔታ ለአውሮጳ እጅግ አስፈላጊ ነዉ ፣ ምክንያቱም፣ በዚህ አካባቢ የሚኖረዉ መረጋጋ ለሕገወጥ ስደት ምክንያት የሚሆነዉን ሁሉ በጋራ ማስወገድ ያስችላል ። ለዚህ ግብም ነዉ በጋራ የምንሠራዉ።»

የጀርመን ወታደሮች በሰሜን ማሊ በተለይም ጋኦ አካባቢ ነዉ የሚንቀሳቀሱት። ወራደሮቹ በተጠቀሰዉ ስፍራ መሣሪያ በተጠመደባቸዉ ተሽከርካሪዎች በሚያደርጉት ክትትል እና ቅኝት የአሸባሪዎች፤ የጦር መሣሪያ እና አደንዛዥ እፅ አዘዋዋሪዎች እንዲሁም ሰዎችን በሕገወጥ መንገድ የሚያሸጋግሩ ወንጀለኞችን እንቅስቃሴ ይከታተላሉ። በያዝነዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት መጨረሻ ገደማም ወታደሮቹ ከፍተኛ ቴክኒዎሎጂ በተገጠመላቸዉ አብራሪ አልባ አዉሮፕላኖችም እገዛ እንደሚደረግላቸዉ ተገልጿል። ከዚህ የሚገኘዉ መረጃም ማሊ ዉስጥ 12,000 ገደማ ወታደሮችን ለሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላሰማሩ 52 መንግሥታት ግልጽ ይሆናል።

Mali Deutschland Ursula von der Leyen besucht Bundeswehr Soldaten in Gao

ፎንደር ላየን ከጀርመን ሠራዊት ጋር

የጀርመን ወታደሮች የማሊ ተልዕኮ አደገኛ እንደሆነ ነዉ የሚገለፀዉ። ባለፉት ሦስት ዓመታት ማሊ ዉስጥ ለሰላም ማስከበር ከተሰማሩ ባለ ሰማያዊ ቆብ ወታደሮች 70 የሚሆኑት በተጣለ ጥቃትና እና ፍንዳታ ሕይወታቸዉን አጥተዋል። በዚያም ላይ የመንግሥታቱ ድርጅት የሰላም አስከባሪ ኃይል የመዋጋት ስልጣን አልተሰጠዉም። እንዲያም ሆኖ የመከላከያ ሚኒስትሯ ደጋግመዉ ተልዕኮዉ የተራዘመ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል። ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ተንታኞች ማሊ ዉስጥ ከሁለት ሺህ እስከ ሦስት አምስት መቶ የሚሆኑ የተለያዩ የፅንፈኛ ቡድኖች ታጣቂዎች እንደሚንቀሳቀሱ ይገምታሉ። የማሊ የመከላከያ ሚኒስትር ሀገሪቱን ለማረጋጋት የኤኮኖሚ ይዞታዉን ማሻሻል ይበጃል ይላሉ። ፎን ደር ላይየን ማሊ ሁለተኛዋ አፍጋኒስታን ትሆናለች የሚል ግምት የላቸዉም። የማሊ ተልዕኮ ተግባራዊ የሆነዉ ከሰፊ የፖለቲካ ሂደት በኋላ ሲሆን ግቡም ሰላም የሚሰፍንበትም መንገድ ማመቻቸት ነዉ። ባለፈዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት የማሊ መንግሥት እና አማፅያን ቡድኖች አንድ የሰላም ስምምነት ተፈራርመዋል። ፎን ደር ላይየን የሚኒሱማ ተዕልኮ ይህ ተግባራዊ እንዲሆን እንደሚረዳ አመልክተዋል።

«የሚኑሱማ ተዕልኮ ለማሊ የተመቻቸ ጊዜ ይሰጣታ። በዚህም ማሊ ዉስጥ በተቀናቃኞቹ ኃይሎች መካከል የተጀመረዉ ሂደትን ተጠቅሞ ሀገሪቱን ወደ ሰላምና መረጋጋት ለመምራት የሚቻልበትን አጋጣሚ ያመቻቻል።»

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic