የጀርመን የልማት እርዳታ መጠንና የእርዳታ ድርጅቶች አስተያየት፣ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 11.11.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የጀርመን የልማት እርዳታ መጠንና የእርዳታ ድርጅቶች አስተያየት፣

የጀርመን የልማት እርዳታ ጉዳይ ድርጅቶች፣ የነጻ ዴሞክራቱ ፓርቲ (FDP) ባልደረባ የሆኑት ዲርክ ኒበል፣ የኤኮኖሚና የልማት ተራድኦ ሚንስትር ከሆኑ ወዲህ፣ የልማት እርዳታ ፖለቲካ አዲስ አቅጣጫ ይዟል በማለት ሲወቅሱ ይሰማል።

default

የልማት እርዳታው በጀት ሳይጨምር ባለበት እንዲረጋ ከመደረጉም፣ ለብዙ ፕሮክቶች ይሰጥ የነበረው ገንዘብ ይቀነሣል፣ ድሆችን ከመርዳት ይልቅ ለኤኮኖሚ ትብብር ነው የላቀ ግምት የሚሰጠው የሚለውን ነቀፌታ፣ የሆነው ሆኖ ፣ ሚንስትሩ አልተቀበሉትም። የጀርመን የልማት እርዳታ በቂ አይደለም መባሉንና የልማት እርዳታም አላግባብ ይውላል መባሉን በማያያዝ

በዚህ ነጥብ ዙሪያ ፣ ረሃብን ከዓለም ዙሪያ ለማስወገድ የሚታገለውን Welthungerhilfe የተሰኘውን የጀርመን ዓለም አቀፍ ድርጅት እንዲሁም «ቴር ዴዝ ዖም » የጀርመን ቅርንጫፍ፣ የሁለቱንም ድርጅቶች ተጠሪዎች አነጋጋሬ ነበር።

የልማት እርዳታ፣ በመሠረቱ ፣ በገፍ ቢሰጥና ፣ ገንዘቡ፣ የብዙ አዳጊ አገሮችን ህዝብ ፣ የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የሚበጅ ሆኖ ቢገኝ ፣ እሰየው እንጂ ሌላ ባላስባለ ነበር። ይሁን እንጂ፣ እርዳታውን ፣ ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት( HRW) እንዳለው፣ ገዥዎች፣ ህዝብን ለመጨቆን በፖለቲካ መሣሪያነት ሆኗል የሚጠቀሙበት። ታዲያ፣ የልማት እርዳታ አላግባብ መዋሉ በሚነገርበት ሰዓት ፣ መጠኑ ዝቅ አለ ብሎ መውቀሱ እስከምን ድረስ አግባብነት አለው? በጀርመን ፣ የ Welthungerhilfe የፖለቲካ ጉዳዮች አማካሪ ወ/ሮ Birgit Dederichs-Bain ---

«የልማት እርዳታ፣ አላግባብ መዋሉ፣ በሰሜን ንፍቀ-ክበብ የሚገኙ፣ የተሻለ ኑሮ ያላቸው በደቡብ ለሚገኙመሰሎቻቸው ፣ ትብብር ማሳየት ከጎናቸው መቆም ያለባቸው የመሆኑን የጠቃሚ መርኅ ጉዳይ አይለውጥወም። ይህ የመጀመሪያው ነጥብ ነው። ሁለተኛ፣ ጀርመንን የመሰለ ከጠንካሮቹ የኤኮኖሚ ሞተሮች አንዷ የሆነች (ከአውሮፓ አገሮች ጋር ስትነጻጸር ማለት ነው)ከብሔራዊው ያልተጣራ ገቢዋ 0,35 ከመቶ ብቻ ለልማት እርዳታ ማዋሏ፣ አያስወቅስም ማለት አይቻልም። ሌሎች ፣ ያን ያህል አቅም የሌላቸው ተጣጥረው የበለጠ ሲሰጡ፣ እንዲህ ዓይነቱ፣ ተመጣጣኝ አይደለምና ፣ መሆን የለበትም።»

የቴር ዴዝ ዖም ቃል አቀባይ ሄር ክርስቲያን ራም በበኩላቸው---

«የልማት እርዳታ መጨመሩ አግባብነት ያለው ነው ምክንያቱም ሁለት በጥሞና የሚታዩ ጉዳዮች አሉና! እርግጥ ነው በየትኛውም የልማት እርዳታ በሚቀርብበት ገንዘብ በሚሰጥበት አካባቢ፣ እርዳታው አላግባብ የሚውልበት አደጋ ይኖራል። ስለሆነም፣ የእርዳታውን መጠን ከፍ ስለማድረግ ብቻ አይደለም የምንናገረው፤ ስለገንዘቡ መጠን አይደለም፤ ሁለት ዋና ጉዳዮች አሉ።»

የፖለቲካ ተዓማኒነት ሌላው ፤ ጉዳይ መሆኑን የጠቀሱት የ«ዌልትሁንገር ሂልፈ» የፖለቲካ ጉዳዮች አማካሪ ፣ አንድ መንግሥት ፣ አንድ አገር፣ ለረጅም ጊዜ በፖለቲካ መግለጫው ላይ ቃል እየገባ ፤ በመጨረሻ ግን ቃሉን ጠብቆ ካልተገኘ ተዓማኒነቱን አጠያያቂ ያደርገዋል ነው ያሉት። ታዲያ የልማት እርዳታ ውጤታማ እንዲሆን ፣ ረዳት መንግሥታትና በኢትዮጵያም የተሠማሩ «ዌልትሁንገርሂልፈ» ን የመሳሰሉ ድርጅቶች ማን ማድረግ ይሆን የሚጠብቅባቸው?!

«የጀርመን ዓለም አቀፍ የረሃብ አስወጋጅ ድርጅት (ዌልትሁንገርሂልፈ)ኢትዮጵያ ውስጥ ለሥራ ከተሠማራ ብዙ ዓመታትን አስቆጥሯል። አስፈላጊ በሆኑ ዘርፎች ፣ በገጠር ልማት ፣ በውሃ አቅርቦት መለስ ብለው ካዩት በአነዚህ ጊዜያት ውስጥአንዳንድ የተከናወኑ ጠቃሚ ጉዳዮች አሉ።»

«ዌልትሁንገር ሂልፈ»፤ የልማት እርዳታን ውጤታማ ለማድረግ በዋናነት ያተኮረበት መርኅ የሲቭል ማኅበረሰብ መደራጀት ነው። ሥራ ማንቀሳቀስ የሚችል የተደራጀ የሲቭል ማኅበረሰብ መኖር አለበት ብሎ የሚያምነው ይኸው ድርጅት፤ የኢትዮጵያ ተባባሪ ሆኖ ሥራውን በ1970ኛዎቹ ዐመታት ሲጀምር ከነበረው በላቀ ሁኔታ አሁን የተደራጀ የሲቭል ማኅበረሰብ አለ ነው የሚለው።ይህ ደግሞ ድርጅቱ እንደሚለው ለተሳካና ውጤታማ ትብብር አንድ ወሳኝ ቅድመ-ግዴታ ሆኖ የሚታይ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ትኩረት ስለሰጣቸው ተግባራትም ፤ Birgit Dedrichs-Bain ሲያብራሩ---

«አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ወንዶችና ሴቶች አርሶ አደሮችን ማጠናከር፣ ምርታቸውን እንዲያሳድጉ ማገዝ፣ እንዲያውም በተሻለ ሁኔታ ለሽያጭ ገበያ ማቅረብ እንዲችሉ መርዳት ነው። ለምሳሌ ያህክል የሥራ ማኅበር መዋቅር እንዲኖራቸው ማብቃት ተገቢ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ባለአነስተኛ ይዞታ አርሶ አደሮች የሚጠናከሩበት ሁኔታ እየተስፋፋ ከመጣ፣ ከሰፋፊ የመሬት ቅርምት፣ አንጻር ጠቃሚ ነው። በመጨረሻም፤ አንድ ሌላ ቅድመ-ግዴታ ልጥቀስ--ከሲቭል ማኅበረሰብ ከባለአነስተኛ ይዞታ አርሶ-አደሮች መጠናከር ባሻገር እንደሚመስለኝ፤ አስተማማኝ ህጋዊ አፈጻጸም ሊኖር ይገባል። ህግ መኖሩ ብቻ ሳይሆን ለህዝብ ጥቅም ተግባራዊ መሆን ይኖርበታል። በገጠር ማለቴ ነው። ይህ ሊደረግ የሚገባው፣ ቅድመ ግዴታ ነው።»

ተክሌ የኋላ

ሒሩት መለሰ