የጀርመን የልማት ተራድኦ | ኤኮኖሚ | DW | 12.09.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የጀርመን የልማት ተራድኦ

የጀርመን መንግሥትና ዓብያተ-ክርስቲያን የልማት ዕርዳታ ትብብር ከተጀመረ 50 ዓመታት አለፉት።

የጀርመን መንግሥትና ዓብያተ-ክርስቲያን የልማት ዕርዳታ ትብብር ከተጀመረ 50 ዓመታት አለፉት። የአገሪቱ ካቶሊክና ወንጌላዊት ዓብያተ-ክርስቲያን ከመንግሥት ጋር ሲያካሂዱት የቆየው ይሄው ትብብር በእርስበርስ መተማመን ላይ የተመሠረተና ታሪኩም የስኬት ታሪክ ሆኖ ነው የሚታየው። እናም የትብብሩ 50ኛ ዓመት በዚህ በቦን የአገሪቱ ፕሬዚደንት፤ እንዲሁም 500 ገደማ የሚጠጉ የፖለቲካና የዓብያተ ክርስቲያን ተጠሪዎች በተገኙበት በደመቀ ስነ ስርዓት ተከብሯል።

ፕሬዚደንት ዮአሂም ጋውክ ሁለቱን ታላላቅ የጀርመን ዓብያተ-ክርስቲያን በዓለምአቀፍ ደረጃ ድህነትንና ፍትህ-ዓልባነትን በመታገል ላደረጉት አስተዋጽኦ ሲያመሰግኑ የልማት ሠራተኞቹ የሕብረተሰቡ ድጋፍ እንዳይለያቸውም ለሕብረተሰባቸው ጥሪያቸውን ሰንዝረዋል። የልማት ሠራተኞቹ ድልድይ መሆናቸው ነው የተጠቀሰው።

« ባሕር ማዶ ርቆ የሚሠራ በዚህ በቤቱ ብዙ ድጋፍ ያስፈልገዋል። ዓብያተ-ክርስቲያኑ በማስተማር ተግባራቸው በዚህ በጀርመንም ተቀባይነት ለማግኘት ይጥራሉ። በሌሎች ሃገራት ሰዎች እንዴት እንደሚኖሩና የተሻለ ዕድል እንዲኖራቸው፤ እንዲሁም በዚህ በጀርመን ምን መደረግ እንደሚገባው ማሳወቅም ተግባራቸው ሆኖ ነው የቆየው»

የጀርመን ካቶሊክና ወንጌላዊት ዓብያተ-ክርስቲያን ከመንግሥት ጋር ትብብር ከጀመሩ ከጎርጎሮሳውያኑ 1962 ዓመተ-ምሕረት ወዲህ እስካሁን ከፌደራሉ የልማት ሚኒስትር መሥሪያ ቤት ያገኙት ድጎማ 6,2 ሚሊያርድ ኤውሮ ገደማ ይጠጋል። በዕርዳታ ድርጅቶቻቸው በካቶሊኩ ሚዜሪዮርና በወንጌላዊቱ ቤተ-ክርስቲያን የልማት አገልግሎት ድርጅት eed በኩል የራሳቸውን ገንዘብ ጨምረው ባለፉት ሃምሣ ዓመታት በእሢያ፣ ላቲን አሜሪካና አፍሪቃ ሃያ ሺህ የሚደርሱ ፕሮዢዎችን አራምደዋል።

Flash-Galerie Stasi-Unterlagenbehörde Gauk

ፕሬዚደንት ዮአሂም ጋውክ ልማት የፖለቲካና የሕብረተሰብ፤ የመንግሥትና የዓብያተ-ክርስቲያን የጋራ ተግባር መሆኑን ሲያስገነዝቡ የአገሪቱ የልማት ተራድኦ ሚኒስትር ዲርክ ኒብልም ይህንኑ በማጠናከር ዓብያተ-ክርስቲያኑ በዚህ ረገድ ያደረጉትን አስተዋጽኦ ከፍ አድርገው ነው ያወደሱት። ተግባሩም ስኬታማ የሚሆነው በጋራ ሲራመድ ብቻ መሆኑን አመልክተዋል።

««ፍቱን የሆነ የልማት ዕርዳታ ፖሊሲ የመላውን ሕብረተሰብ ክፍላት ተሳትፎ ይጠይቃል። ሲቪሉን ሕብረተሰብና የኤኮኖሚውን ዘርፍ በአጠቃላይ ማለት ነው። ይህ ደግሞ እዚህ እኛ ዘንድ ብቻ ሣይሆን በምንተባበራቸው ሃገራትም መኖሩን እናውቃለን። እናም ዓብያተ-ክርስቲያኑ በሕብረተሰብ ውስጥ ጥልቅ መሠረት እንዳላቸው በመረዳት የተለየ ክበደት ሰጥተናቸው ነው የቆየነው»

የዓብያተ-ክርስቲያኑ አስተዋጽኦ ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ በተለይም መንግሥታዊው የልማት ትብብር በፖለቲካ ችግር የተነሣ ሊራመድ በማይችልባቸው ሁኔታዎች ከአንዴም ብዙ ጊዜ በጉልህ የታየ ነገር ነው። መንግሥት በማይችልበት ጊዜ ዓብያተ-ክርስቲያኑ ከውስጥ አበሮቻቸው ጋር በመሆን ለድሃው ሕዝብ በቀጥታ ዕርዳታ ማቅረብ ይቻላቸዋል። የጀርመኑ የልማት ተራድኦ ሚኒስትር ዲርክ ኒብል ለዚህ ጥሩ ምሳሌም አላቸው።

«በርማ ማዕቀብ ተጥሎባት በነበረ ጊዜ በዚያ ተገኝተን መሥራት አንችልም ነበር። ዓብያተ-ክርስቲያኑ በአንጻሩ በተግባር መሰማራቱ አላዳገታቸውም። መንግሥት ከዚህ በተጨማሪ ከሰሜን ኮሪያም የመተባበር ሃሣብ አልመጣለትም። ዓብያተ-ክርስቲያኑ ግን በዚያም የዕርዳታ ፕሮዤዎችን ያራምዳሉ»

እንግዲህ አንዱ የሌላውን ጉድለት እየሸፈነ የልማት ዕርዳታውን ለማራመድ ሲጣር ቆይቷል ማለት ነው። እርግጥ ይህ መንግሥት ገንዘብ አቅራቢ በመሆኑ የፖሊሲ ተጽዕኖ ያደርጋል ማለት አይደለም። የወንጌላዊቱ ቤተ-ክርስቲያን የልማት አገልግሎት ድርጅት የአመራር ዓባል ክላውዲያ ቫርኒንግ እንደሚያስረዱት ተግባራቸውን የሚያራምዱት ከማንኛውም የመንግሥት ተጽዕኖ ነጻ ሆነው ነው።

«ዓብያተ-ክርስቲያኑ በየትኛው አገር፣ ከማን ወይም በምን ዓይነት ፕሮዤ ላይ እንደሚሰማሩ የሚወስኑት ራሳቸው ናቸው። መንግሥት በበኩሉ ድህነትን ለመታገል ገንዘብ በሚያቀርብልን ጊዜ ይህንኑ በአግባብ እንደምንጠቀም ያውቃል። በተለይም ተባባሪያችን ከሆኑት ዓብያተ ክርስቲያንና የዓብያተ-ክርስቲያን የልማት ድርጅቶች ጋር በምንሰራበት ጊዜ!»

የጀርመን የልማት ተራድኦ ሚኒስትር መሥሪያ ቤት በዚህ ዓመትም የዓብያተ-ክርስቲያኑን ድርጅቶች ተግባር በ 216 ሚሊዮን ኤውሮ ይደግፋል። ታዲያ ቀደም ሲል እንተጠቀሰውና የፌደራሉ የልማት ትብብር ሚኒስቴር ተቋም መርህም እንደሚያመለክተው ከገንዘብ አቅርቦቱ ጋር የተያያዘ አንዳች የፖለቲካ ቅድመ-ግዴታ የለም። እንዲያው አንድ ግዴታ ቢኖር ገንዘቡ ከልማት ውጭ ለሰበካ ተግባር ስራ ላይ መዋል እንደሌለበት ብቻ ነው።

የሁለቱ የጀርመን ዓብያተ-ክርስቲያን የልማት ዕርዳታ ተግባር ማዕከላዊ ተቋማት ገንዘቡን ለበጎ አድራጎት ድርጅቶቻቸው አከፋፍለው በስራ ላይ የሚያውሉ ሲሆን ስለዚሁም መረጃ የማቅረብ ግዴታ አለባቸው። የካቶሊኳ ቤተ-ክርስቲያን የዕርዳታ ድርጅት የሚዜሪዮር ባልደረባ ማርቲን ብሩክልማን-ሲሞን እንደሚያስረዱት እርግጥ ፕሮዤዎቹን ራሳቸው አያራምዱም። የዚህ ሃላፊነት ያለው 2,500 ገደማ በሚጠጉት በየቦታው የሚገኙ ተባባሪዎቻቸው ዕጅ ነው።

«እነዚሁ ለምሳሌ በኪርጊዚያ መንገድ አዳሪ ሕጻናትን ወይም በፊሊፒን ለአቅመ-አዳም ያልደረሱ እስረኞችን ይንከባከባሉ። ከዚሁ ሌላ በፔሩ የማዕድን ሠራተኞችን ወይም በኬንያ በደሳሳ ጎጆ የሚኖሩ ድሆችን ይረዳሉ»

ብሮክልማን-ሲሞን ጨምረው እንደሚያስረዱት በዓብያተ-ክርስቲያኑ የልማት ስራ መጀመሪያ ላይ ፕሮዤዎቹ የሚያተኩሩት ለምሳሌ አንድ የቤተ-ክርስቲያን የጤና ጥበቃ ይዞታ፣ ትምሕርትቤቶችና የዕጅ ሥራ ማሰልጠኛዎችን በማነጽ ነበር። ግን ከጊዜ ጋር ሁኔታው እየተለወጠ ነው የመጣው። በዛሬው ዘመን ዋናው ነገር መንግሥታት መብትና ግዴታቸውን ማወቃቸው፤ በራሳቸው መሠረታዊ ማሕበራዊ አገልግሎቶችን መስጠታቸውም ነው። በሌላ አነጋገር ዛሬ በአፍሪቃ፣ በእሢያም ሆነ በላቲን አሜሪካ የራስን የጤና ጥበቃ ወይም የትምሕርት ስርዓት ማነጽ የዓብያተ-ክርስቲያኑ ተግባር አይደለም።

ሁኔታው እንዴት ይቀጥላል? የዓብያተ-ክርስቲያኑ የልማት ትብብር ዛሬ በደቡቡ ዓለም ላይ ብቻ ማተኮሩ አብቅቷል። የዓለም ኤኮኖሚ ትስስር ግሎባላይዜሺን አዳዲስ የመፍትሄ መንገዶችን እየጠየቀ ነው የሚገኘው። እና ይህም በውል ሊጤን የሚገባው ነገር ነው። በዛሬው ጊዜ ሰዎችን አሣ ከመስጠት አሣ ማጥመድ ማስተማሩ የተሻለ ነው የሚለው መሠረተ-ዓላማ ብዙም ስር ሰዶ አይገኝም። በሌላ በኩል አሣን ማጥመድ የቻለ ሁሉስ ውሃ ያገኛል ወይ? ባዕድ ጀልባ ከጠረፉ ላይ መጥቶ አሣውን የሚወስድበትስ ምን ማድረግ ይችላል? በዘመነ ግሎባላይዜሺን የልማት ዕርዳታ ተግባርም ይበልጥ ፖለቲካዊ እየሆነ ነው የሄደው።

EED Logo

የሆነው ሆኖ ግን የልማት ዕርዳታው ተግባር ወደፊት መቀጠል ይኖርበታል። የወንጌላዊቱ ቤተ-ክርስቲያን የልማት ተቋም ባልደረባ ክላውዲያ ቫርኒንግ እንደሚሉት ታዲያ ያለፉት ሃምሣ ዓመታት ተግባር በስኬት እንዲቀጥል የሕብረተሰቡ ድጋፍ በጣሙን ወሣኝ ነው የሚሆነው።

«በምናደርገው ነገር ሁሉ ለመቀጠል የሕብረተሰቡን ድጋፍ እንፈልጋለን። በወቅቱ ካለው የኤኮኖሚ ቀውስና ችግር አንጻር አንዳንዴ ትኩረቱ በራስ ላይ ሲሆን ይታያል። በውጭ ሶሥት ሚሊያርድ ሕዝብ በቂ ካሎሪ አግኝቶ በአግባብ ራሱን መቀለብ በማይችልበት ሁኔታ ላይ እንዳለ እየታወቀ የራስን ችግር ለመቋቋሙ ቅድሚያ የሚሰጥ ነው የሚመስለው። ስለዚህም በኛ የአኗኗር ሁኔታና በድህነቱ መካከል ያለውን ልዩነት መረዳትና ግንዛቤ መስጠት ይኖርብናል»

በዚህ በጀርመን በመንግሥትና በዓብያተ-ክርስቲያን መካከል ለአምሥት አሠርተ-ዓመታት ሲካሄድ የቆየው የልማት ዕርዳታ ትብብር ፍቱንነቱን አሳይቷል። ይሁን እንጂ የወደፊት ጉዞው ቀላል ይሆናል ማለት አይደለም። በዓለምአቀፉ የፊናንስና የኤኮኖሚ ቀውስ የተነሣ አንዳንድ ለጋሽ ሃገራት የልማት ዕርዳታቸውን ቀንሰዋል። ታዲያ ድህነትን በመታገሉ ረገድ ስኬት ሊገኝ የሚችለው በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸገው ሰሜኑ ዓለም ቅንጡ የፍጆታ ዘይቤውን አጥብቆ ሲያስብበትና ሲለውጠው ነው።

በወቅቱ የኢንዱስትሪውን ዓለም የቤንዚን ፍላጎት ለማርካት የተያዘው የባዮ-ዲዝል እርሻና የምግብ ምርቶች ዋጋ መናር ያስከተለው ክርክር የሁኔታውን ክብደት በግልጽ ያመለክታል።

መሥፍን መኮንን

ሒሩት መለሰ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 12.09.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/166sv
 • ቀን 12.09.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/166sv