የጀርመን ዕጩ ፕሬዚዳንት | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 20.02.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የጀርመን ዕጩ ፕሬዚዳንት

የጀርመን ፕሬዚዳንት ስልጣን ከለቀቁ ከ2 ቀናት በኋላ አዲስ ፕሬዚዳንት ዕሁድ የካቲት 11 ቀን 2004 ዓ. ም. በእጩነት ቀርበዋል። መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርኬልን ጨምሮ በሐገሪቱ የዋነኛ ፖለቲከኞች ይሁንታን ከወዲሁ ያገኙት ዕጩ የ72 ዓመቱ

የጀርመን ፕሬዚዳንት ስልጣን ከለቀቁ ከ2 ቀናት በኋላ አዲስ ፕሬዚዳንት ዕሁድ የካቲት 11 ቀን 2004 ዓ. ም. በእጩነት ቀርበዋል። መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርኬልን ጨምሮ በሐገሪቱ የዋነኛ ፖለቲከኞች ይሁንታን ከወዲሁ ያገኙት ዕጩ የ72 ዓመቱ የምስራቅ ጀርመኑ ዮአሂም ጋውክ ናቸው።

ጀርመን ለሁለት ተከፍላ በነበረበት ዘመን በኮሚኒስቶቹ የምስራቅ ጀርመን ነው ተወልደው ያደጉት። ዮአሂም ጋውክ ይባላሉ። የ72 ዓመት አባወራ ሲሆኑ፤ የአራት ልጆች አባት ናቸው። በግራጫማ ፀጉራቸውና ረጋ ባለው አንደበታቸው ይታወቃሉ። የበርሊን ግንብ ተደርምሶ ሁለቱ ጀርመኖች አንድ እንዲሆኑ ያስቻለውን ሠላማዊ ዓብዮት ከመሩት ዋነኛ ፖለቲከኞች መካከልም ይመደባሉ። በዛው ተወልደው ባደጉበት የምስራቅ ጀርመን የሉተራን ፓስተር እና የሠብዓዊ መብት ተሟጋችም ነበሩ። ቀደም ሲል ለፕሬዚዳንትነትነት በዕጩነት ቀርበው ያኔ መራሂተ-መንግስቷ በጠቆሟቸው ሌላው ዕጩ ክርስቲያን ቩልፍ ቦታውን ሊያገኙ አልቻሉም ነበር። እሁድ ከአውሮፕላን ወርደው ይጓዙበት በነበረው ታክሲ እንደተቀመጡ ነው መራሂተ-መንግስቷ ደውለው የጠሯቸው። አሁን ቦታውን ለሌላ ሊሰጡ ሳይሆን ለእሳቸው ለማስረከብ ይመስላል። ዕጩ ፕሬዚዳንቱ ዮአሂም ጋውክ በበኩላቸው ግራ ሳይጋቡ አልቀረም።

ዮአሂም ጋውክ እና ክሪስቲያን ቩልፍ

ዮአሂም ጋውክ እና ክሪስቲያን ቩልፍ

«አሁን ግራ በተጋባሁበት ሁኔታ መሰረታዊ፣ የፖሊሲ ጉዳዮችን ላቀርብላችሁ አልችልም። ያ የማይቻል ነገር ነው። መራሂተ-መንግስቷ ሲደውሉልኝ ከአውሮፕላን ወርጄ ታክሲ ውስጥ ነበርኩኝ። ገና እንኳን አልታጠብኩም። መደነቄን፣ ትንሽ ግራ መጋባቴን ብትመለከቱም ምንም አይደለም። አንድ ነገር ግን አውቃለሁ። ሰዎች ሃላፊነትን ለመሸከም ያላቸው ፍላጎት በመላው ሀገራችን ያለ ነው፤ በፖለቲከኞች ብቻ የተወሰነ አይደለም። የእኔም ዋና ተግባር ይህን ልምድ ማስቀጠል ነው።»

ጋውክ ከሁለት ዓመት ቀደም ብሎ ለፕሬዚዳንትነት ዕጩ ሆነው በቀረቡበት እና በክሪስቲያን ቩልፍ በተሸነፉበት ወቅት የመገናኛ ብዙኃንን ከፍተኛ ትኩረት ስበው እንደነበር የሚታወቅ ነው። ያኔ በጀርመን ከፍተኛ ተነባቢነት ያላቸው፤ ሳምንታዊዎቹ ደር ሽፒግል እና ቢልድ መፅሄት ጋውክን «የተሻለው ፕሬዚዳንት» እና «ተወዳጁ ፕሬዚዳንት» በሚል አሞካሽተዋቸው ነበር። ክሪስቲያን ቩልፍ በሙስና ተጠርጥረው ስልጣናቸውን እንዲለቁ ሲገደዱ ለፕሬዚዳንትነቱ በዕጩነት የብዙዎችን ቀልብ የሳቡት እኚሁ ጋውክ ናቸው። እሁድ ምሽት የዋነኞቹ ፓርቲ መሪዎች በተገኙበት ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት መራሂተ-መንግስት አንጌላ ሜርክል ተቃውሞዋቸውን በማንሳት ለጋውክ ያላቸውን ድጋፍ አሳይተዋል።

«ክቡራት እና ክቡራን ይህ ሰው ከፊታችን ለተጋረጠው ፈተና እና ለወደፊቱ ጠቃሚ መነቃቃት ሊሆነን እንደሚችል እርግጠኛ ነኝ።»

በ ሶሻል ዲሞክራት ፓርቲ SPD እና አረንጓዴዎቹ የቀረቡት የዮአሂም ጋውክ ለፕሬዚዳንትነት መታጨትን መራሂተ-መንግስቷ ሲቃወሙ ነበር። ይሁንና ከእሳቸው ፓርቲ ማለትም ከክርስቲያን ዲሞክራቶች ጋር በጥምር ስልጣን የያዘው የነፃ ዴሞክራቶቹ ፓርቲ FDP ትናንት ከSPD እና ከአረንጓዴዎቹ ጋር በመሆን ለጋውክ ድጋፍ በመስጠቱ አንጌላ ሜርኬከል በስተመጨረሻ ቢሆንም ድጋፋቸውን ለጋውክ ሰጥተዋል። ሜርክል የሁሉም ፓርቲዎች ድጋፍ ያለው ዕጩ ያስፈልጋል በማለት ነበር ሲከራከሩ የቆዩት። ዕጩው ፕሬዚዳን ዮአሂም ጋውክ፥

«መራሂተ መንግስት፣ በዕጩነት የመራጣችሁኝ ክቡራት እና ክቡራን፤ በህይወት ዘመኔ ካጋጠሙኝ በርካታ ልዩ ቀናት ሁሉ ይህ ለኔ በእርግጥም ልዩ ቀን ነው።»

የጀርመን ፖለቲከኞች

የጀርመን ፖለቲከኞች

መራሂተ-መንግስት አንጌላ ሜርክል የዮአሂም ጋውክን መታጨት እስከ የካቲት 12 ቀን 2004ዓ. ም ምሽት ድረስ ቢቃወሙም ሁለቱንም የሚያመሳስላቸው ነገሮች ግን አሉ። ሁለቱም በእምነታቸው ሉተራኖች ሲሆኑ፤ ከምስራቅ ጀርመን ነው የመጡት። ጋውክ የቀድሞ ፓስተር፤ ሜርክል ደግሞ የፓስተር ልጅ ናቸው። ጋውክ ራሳቸውን ወግ አጥባቂ አድርገው ነው የሚገልፁት፤ እንዲያም ሆኖ ከሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ድጋፍ አግኝተው እዚህ ደርሰዋል። መጠይቅ ከተደረገላቸው ጀርመኖች መካከል ከግማሽ በላዪ ጋውክን በፕሬዚዳንትነት ማየት ይፈልጋል። ጋውክ ከሳምንታት በኋላ ይፋዊ በሆነ መልኩ በዓለ ሲመት እንደሚደረግላቸው ይጠበቃል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic