የጀርመን ውኅደት ያከሰራት ከተማ-ቢሾፌሮደ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 11.11.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የጀርመን ውኅደት ያከሰራት ከተማ-ቢሾፌሮደ

በጀርመን ውኅደት ማግሥት በቱሪንጊያ ግዛት ቢሾፌሮደ በተባለች አነስተኛ ከተማ ይገኝ የነበረ የፓታሽ ማውጪያ ተዘግቶ የተበተኑ የቀድሞ ማዕድን ቆፋሪዎች ዛሬም በደል ይሰማቸዋል። በውኅደቱ ማግሥት ከግማሽ በላይ የምሥራቅ ጀርመን የመንግሥት ተቋማት ለምዕራብ ጀርመን ተሸጠዋል።በዚህም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የምሥራቅ ጀርመን ሰዎች ስራቸውን አጥተዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 05:48

በቢሾፌሮደ የነበረው የፖታሽ ማውጫ ከተዘጋ 30 አመታት ሆኖታል

በጀርመን ቱሪያንጊያ ግዛት ከቢሾፌሮደ በስተ-ሰሜን ከሚገኘው ቤተ-መዘክር ስንደርስ የተቀበሉን ቢንደር በትንሿ ከተማ በነበረ የፖታሽ ማዕድን ማውጫ ለረዥም አመታት ሰርተዋል። ከምድር ከርስ ዘልቀው ማዕድን ይቆፍሩ የነበሩት ሰው ዕድሜ ተጫጭኗቸዋል። ትከሻቸው ጎብጧል፣ አይኖቻቸው ደካክመዋል፣ እጆቻቸው ይንቀጠቀጣሉ። የለበሱት ጥቁር እና ነጭ ሸሚዝ፣ ጅንስ ሱሪ እና የተጫሙት የቆዳ ጫማ በዕድሜያቸው ማምሻ ኑሮ እንዳልደላቸው ያሳብቃሉ።

ይኸ ቤተ-መዘክር ከ30 አመታት ገደማ በፊት የተዘጋ የፓታሽ ማምረቻን ለመዘከር የተቋቋመ ነው። በሕንጻው አንደኛ ፎቅ የቀድሞ ማዕድን ቆፋሪዎች ከምድር ከርስ ዘልቀው ያወጧቸው አንጸባራቂ የድንጋይ አይነቶች በመልክ በመልክ ተሰድረዋል። የቀድሞ ማዕድን ቆፋሪዎች የሚጫሟቸው፣ የሚለብሷቸው፣ ራሳቸውን ከአደጋ የሚከላከሉባቸው ሁሉ ይገኛሉ።

Bischofferode Kalibergbau (DW/E. Bekele Tekle)

ዊሊባልድ ኔበል የፖታሽ ማውጫውን ከመዘጋት ለመታደግ ለ80 ቀናት ገደማ የረሐብ አድማ ካደረጉ መካከል አንዱ ናቸው

ከምድር በታች ያለው የሕንጻው ክፍል የቀድሞው ማዕድን ማውጫ ነው። ጥቂት ማሽኖች እና ሰራተኞች ደረታቸው ላይ የሚያንጠለጥሏቸው መብራቶች በዚህ አሉ። የሰራተኞች ምሳ መቋጠሪያ ቦርሳዎች ሻግተው ከግድግዳ ተሰቅለዋል። 

የቢሾፌሮደ ማዕድን ማውጫ በይፋ የተዘጋው ጀርመን ከተዋሀደች ከጥቂት አመታት በኋላ በጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር ታኅሳስ 22 ቀን 1993 ዓ.ም. ነበር። ይኸ ለቤተ-መዘክሩ ኃላፊ እና የቀድሞ ማዕድን ቆፋሪኛ ዊሊባልድ ኔበል እና ለባልደረቦቻቸው ዛሬም ድረስ ልብ ሰባሪ ሆኖ ዘልቋል።

ዊሊባልድ ኔበል "የማዕድን ማውጫው መዘጋት እጅግ አሳዛኝ ነው። ለረዥም አመታት ማዕድናት ይወጡ በነበረበት ቦታ ሥራ ቆሟል። ለምን ካልከኝ ከ1993 በኋላ ቢሾፌሮደ በድንገት ጠፋች። ሰራተኞች ማዕድን ማውጫው እንዳይዘጋ በመታገላቸው የመንግሥት ጠላት ተደረጉ" ሲሉ ይናገራሉ።

Bischofferode Kalibergbau (DW/E. Bekele Tekle)

በቢሾፌሮደ የሚገኘው ቤተ-መዘክርና የቀድሞ ማዕድን አውጪዎች ማኅበር የሚገኝበት ሕንጻ

በቦታው የማዕድን ቁፋሮ የተጀመረው ከአንድ አመቶ አመታት በፊት ገደማ ነው። ማዕድን ማውጫው ካሊቬርክ ቶማስ ሙንትዘር ወይም የቶማስ ሙንትዘር የፖታሽ ስራዎች በሚል መጠሪያ ይታወቅ ነበር።

ምሥራቅ እና ምዕራብ ተብለው የተለዩት ጀርመኖች ከተዋሐዱ በኋላ በጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር 1992 ዓ.ም. ማዕድን ማውጫው እንዲዘጋ መንግሥት ወሰነ። መነሾው በጀርመን ከበቂ በላይ የፓታሽ ምርት ይገኛል የሚል ነበር። የምሥራቅ ጀርመን ኩባንያዎችን ወደ ግል ለማዘዋወር የተቋቋመው ድርጅት (The Treuhand agency) በበኩሉ የምሥራቆቹ ፖታሽ አምራቾች ከምዕራቡ መሰሎቻቸው እንዲቀላቀሉ ሐሳብ አቀረበ። ውሳኔው ማዕድን ቆፋሪዎችን ከሥራ ገበታቸው እንደሚያፈናቅል የገባቸው ሰራተኞች ተቃውሞ ጀመሩ። 

ወደ 700 ገደማ ሰራተኞችን እጣ ፈንታ ለመታደግ የተደረገው ተቃውሞ እና የረሐብ አድማ ከጀርመን ተሻግሮ ዓለም አቀፍ ተሰሚነት አገኘ። ከአውስትራሊያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና አሜሪካ የአጋርነት መልዕክቶች እና ስጦታዎች ጎረፉ። ነገር ግን የጀርመን መንግሥትን ውሳኔ መቀልበስ አልቻሉም። የማዕድን ማውጫው መዘጋት ያስከተለው ኤኮኖሚያዊ ምስቅልቅል በቢንደር እና በባልደረቦቻቸው ላይ የበረታ ነበር።

Deutschland Der ehemalige Bergmann Binder (DW/S. Mnette )

የቀድሞው የቢሾፌሮደ ፖታሺየም ማውጫ ሰራተኛ ቢንደር

"በወቅቱ ሁለት ልጆች ነበሩኝ። አንዲት ሴት እና አንድ ወንድ። ትዳር ከመሰረትኩ 20 አመታት አልፈዋል። ባለቤቴ ሥራ አልነበራትም። እኔም ከስራ ስባረር ችግር ላይ ወደቅን። ከዚያ በኋላ ባለቤቴ በመንግሥት የግብር ሰብሳቢ መስሪያ ቤት ጸሀፊ ሆና ለመስራት ተገደደች" ይላሉ ቢንደር

በወቅቱ የጀርመን ኩባንያዎችን ወደ ግል ለማዛወር በተቋቋመው ድርጅት በርካታ የምስራቅ ጀርመን ሰዎች ዛሬም ቂም እንደቋጠሩ ናቸው። ብዙዎች የምሥራቅ ጀርመን ምጣኔ ሐብት ከምዕራቡ አኳያ ላለበት መዛነፍ ይኸንንው ተቋም ተጠያቂ ያደርጋሉ። ዊሊባልድ ነባል እንደሚሉት ካሳ እንኳ በአግባቡ አልተከፈላቸውም።

"በርካታ የምሥራቅ ሰዎች ይሰሩበት የነበረው የትሮይሃንድ ኤጀንሲ አስቀያሚ ድርጊት ፈጽሟል። ተቋሙ የቆመው ለእኛ ለተራዎቹ ሰዎች ሳይሆን ለግዙፎቹ ኩባንያዎች ነበር። ካሳ ሲከፈል እንኳ እኛ የቢሾፌሮደ ሰዎች ትዝ ያልናቸው በመጨረሻ ነው። ለእኛ ምንም አይነት የካሳ ገንዘብ አልተዘጋጀም። እድለኛ ሆነን ‘የይሁዳ ገንዘብ’ ብለን ለምንጠራው ካሳ አንድ ተሟጋች ጥብቅና ቆመልን። በሌሎች ግዛቶች ተመሳሳይ በደል የደረሰባቸው አርባ ሺህ፣ አምሳ ሺህ እና ሰባ ሺህ ሲከፈላቸው ለእኛ የሰጡን ግን 7, 500 የዶች ማርክ (በወቅቱ የጀርመን መገበያያ ገንዘብ) ብቻ ነበር። ይኸን 7,500 ማርክ ለመቀበል መንግሥትን አንከስም ብለን እንድንፈርም አስገድደውናል" ሲሉ ይናገራሉ። 

Bischofferode Kalibergbau (DW/E. Bekele Tekle)

ዊሊባልድ ኔበል

በጎርጎሮሳዊው 1990 ዓ.ም.  የተቋቋመው የትሮይሃንድ ኤጀንሲ ከ8,000 በላይ የመንግሥት ድርጅቶችን እና ከአራት ሚሊዮን በላይ ሰራተኞቻቸውን እጣ ፈንታ የመወሰን ኃላፊነት ተጥሎበት ነበር። በጉዳዩ ላይ የተሰሩ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ከግማሽ በላይ የምሥራቅ ጀርመን የመንግሥት ተቋማት ለምዕራብ ጀርመን ተሸጠዋል። ከጀርመን ውኅደት በኋላ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የምሥራቅ ጀርመን ሰዎች ስራቸውን አጥተዋል። ከእነዚህ መካከል ቢንደር አንዱ ናቸው።

"መጀመሪያ ለአጭር ጊዜ የኮንትራት ስራዎች አገኘን። በቋሚነት ይቀጥሩናል ብለን ነበር። ስራችን ለስድስት ወይም ለስምንት ወራት ብቻ ነበር። ከዚያ ዓለቆቻችን እየጠሩ የስራ ውላችን መቋረጡን ነገሩን። ምን እናድርግ? ምንም። አዳዲስ ስራ ማፈላለግ ጀመርን። የተወሰኑ ስራ አገኙ፣ የተወሰኑ ሳያገኙ ቀሩ"

ጀርመን ባትዋሀድ ኖሮ የቢሾፌሮደ ፖታሽ ማምረቻ ሳይዘጋ ይቀር ነበር? በቀጥታ ጥያቄውን መመለስ ከባድ ይመስላል። "እስከ ዛሬ ድረስ ለሚቀጥሉት አስር አመታትም ማምረት እንችል ነበር። አስፈላጊ የቴክኒክ ቁሳቁሶች ነበሩ፣ ማዕድናቱ አሉ" የሚሉት ዊሊባልድ ነባል ግን ማምረቻው ለረዥም አመታት ይሰራ ነበር የሚል አቋም አላቸው።

"የቴክኒክ ሰራተኞቹ እና ማዕድን ማውጫው ምልክታቸው እንዳይገኝ፣ ማንም እንዳያስታውሳቸው ተደርገው ጠፍተዋል። የቀረው ከተረፈ ምርት የተፈጠረው ተራራ ብቻ ነው። እሱም ለበርካታ መቶ አመታት እዚሁ ይቆያል" ሲሉ ነባል ነባራዊውን ሁኔታ ይገልጹታል።

Bischofferode Kalibergbau (DW/E. Bekele Tekle)

ከማዕድን ማውጫው 34 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ተረፈ ምርት የተፈጠረው ተራራ

ከ34 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ተረፈ ምርት የተፈጠረው ተራራ በቦታው የማዕድን ማውጫ እንደነበር ይመሰክራል። የቱሪንጊያ ግዛት መንግሥት ይኸው ተረፈ ምርት በአካባቢው ነዋሪዎች ጤና ላይ እክል እንዳያሳድር በየአመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዩሮ ያወጣል። ጀርመን ከተዋሀደች ከ30 አመታት በኋላ የቀድሞ ማዕድን ቆፋሪዎች አቤቱታ መልስ ለማግኘቱ ግን ማንም እርግጠኛ አይደለም።

እሸቴ በቀለ

ልደት አበበ


 

Audios and videos on the topic