የጀርመን ውሕደትና የምሥራቁ ግንባታ | ኤኮኖሚ | DW | 29.09.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የጀርመን ውሕደትና የምሥራቁ ግንባታ

የጀርመን መልሶ ውሕደት ከሰፈነ ወዲህ በፊታችን ዕሑድ ሃያ ዓመት ይሞላዋል። በነዚህ ዓመታት በተለይ የምሥራቁን ኤኮኖሚ በመገንባቱ ረገድም ታላቅ ጥረት ነው የተደረገው።

default

ምሥራቅ በርሊን

ተንኮታኩቶ ወድቆ የነበረውን የቀድሞውን የምሥራቁን ክፍል ኤኮኖሚ ለመገንባት እስካሁን የወጣው ገንዘብ ከቢሊዮን ኤውሮ ይበልጣል። እርግጥ ተግባሩ ገና ዛሬም አላበቃም። ይሁንና በምዕራቡ ክፍል ግብር ከፋይ ድጋፍና የኤኮኖሚ ብልጽግና በቀድሞይቱ ሶሻሊስት ግዛት አምሥት ፌደራል ክፍለ-ሐገራት ውስጥ የተካሄደው መዋቅራዊ ግንባታና ጥገና አድናቆት የሚሰጠው ነው።

አርአያም ሆነ የተዘጋጀ ንድፈ-ሃሣብ አልነበረም። የሶሻሊስት ምሥራቅ ጀርመንን ማዕከላዊ የፕላን ኤኮኖሚ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ገበያ ኤኮኖሚ የመቀየሩ ግብ ብቻ እንጂ! ውሕደቱ እንዲህ ባለ ሁኔታ ሲጀምር ይህን ተግባር እንዲያራምር የተሰየመው ባለ አደራ ተቋምም ፋታ በሌለበት ሁኔታ ስራውን ይጀምራል። በጊዜው አራት ሚሊዮን ተቀጣሪዎች የሚሰሩባቸው 12 ሺህ ፋብሪካዎች በውድቀት አፋፍ ላይ ሲገኙ የምሥራቅ ጀርመን ዕዳም 300 ሚሊያርድ ዴ-ማርክ ደርሶ ነበር። ችግሩ ጨርሶ ጊዜ የሚሰጥ አልነበረም። የተቋሙ ሃላፊ ቢርጊት ብሮይል ዛሬ መለስ ብለው ሲያስታውሱ እንዲህ ይላሉ።

“የግል ይዞታን ማስፈኑ ኤኮኖሚውን ለመጠገን የተሻለው መንገድ ነው ብለን በማመናችን ይህንኑ በፍጥነት ማራመድ የመጀመሪያው ተግባራችን ነበር። ሁለተኛው መርሆ በቁርጠኝነት መጠገን የሚል ነበር። እና የወደፊት ተሥፋ በሚታይበት ቦታ ሁሉ ጥገናውን ማካሄድና የሰዉንም ተሥፋ ማጠናከር ይታመንበታል። ሶሥተኛው ደግሞ የፋብሪካዎች አዘጋግ የሕዝቡን ስሜት እንዳይጎዳ ሆኖ መካሄድ ነበር”

የሁለቱ የጀርመን ግዛቶች ከአራት አሠርተ-ዓመታት መነጣጠል በኋላ መልሶ ለመዋሃድ መብቃት በጊዜው ማንም ያልጠበቀውና ችግሩ ቀላል ባይሆንም ለሕዝቡም አዲስ ምዕራፍን የከፈተ ነበር። ለፌደራል ሬፑብሊክ ጀርመን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ከተከተለው ተዓምር ያሰኘ ፈጣን የኤኮኖሚ ዕድገት ቀጥሎም ይሄው የምሥራቁ ግንቢያ ሁለተኛው ታላቅ ብሄራዊ ፕሮዤ መሆኑ ነው። ከምዕራቡ ወደ ምሥራቁ ክፍል የፈሰሰው ገንዘብ እጅግ ከፍተኛ ሲሆን ለግንባታው አስተዋጽኦ መደረጉ ደግሞ ከሃያ ዓመታት በኋላም አልተቋረጠም።

ባለፉት ሃያ ዓመታት ታዲያ ሁሉም ነገር ተሟልቷል አይባል እንጂ የምሥራቁ ክፍል ገጽታ በጣሙን ነው የተቀየረው። ዛሬ የምሥራቁን ክፍል የሚጎበኙ የምዕራቡ ወገን ነዋሪዎች በየከተማው ቤቶች ተጠግነውና ተውበው፤ እንዲሁም መንገዶች አምረው ሲያዩ ዘመናዊ በሆነው መዋቅራዊ ግንባታ በጣሙን ነው የሚገረሙት። ዕውነትም ዛሬ ለሁለት ተከፍላ በኖረችው በርሊን እንኳ ቢቀር ከግንቢያው አንጻር የምዕራቡና የምሥራቁ ልዩነት በሰፊው ነው የተወገደው። የቀድሞው ልዩነት ብዙም ጎልቶ አይታይም።

የጀርመን ውሕደት በትክክል ምን ያህል ወጪን እንደፈጀ እርግጥ መገመት ብቻ ነው የሚቻለው። ግን ምሥራቃዊቱ ከተማ ሃለ ላይ ተቀማጭ እንደሆነው የጀርመን የምጣኔ-ሐብት ምርምር ኢንስቲቲዩት ከሆነ እ.ጎ.አ. በ 1991 እና በ 2009 መካከል የወጣው ገንዘብ 1,3 ቢሊዮን ኤውሮ ይደርሳል። ለማነጻጸር ያህል ያለፉት 50 ዓመታት ዓለምአቀፍ የልማት ዕርዳታ በአጠቃላይ 1,5 ቢሊዮን ኤውሮ ቢጠጋ ነው። ለምሥራቁ ግንቢያ የሚወጣው ገንዘብ በአብዛኛው ወደ አዳዲሶቹ ምሥራቃዊ ክፍለ-ሐገራት በቀጥታ ሲፈስ ቆይቷል። በአንጻሩ ፌደራላዊው መንግሥት ራሱ በቀጥታ መዋዕለ-ነዋይ የሚያደርገው በመገናኛ ፕሮዤዎች፤ ማለትም በመንገዶችና ፈጣን አውራ ጎዳናዎች፤ እንዲሁም የውሃ መስመሮች ላይ ነው።

ወደ ውሕደቱ አፍላ ዘመን መለስ እንበልና ለጀርመን ከባድ ፈተናን የደቀነው ኋላ ቀር የነበረውን መዋቅራዊ ይዞታ ለማቅናትና አምራች ከፋብሪካዎች ለመደገፍ ገንዘብ ማውጣቱ አልነበረም። ታላቁ ፈተና የጊዜይቱ ምሥራቅ ጀርመን ኤኮኖሚ እንዳለ ተንኮታኮቶ መውደቁ ነበር። ይህ ደግሞ በምሥራቁ ክፍል የሥራ አጡ ብዛት ራስ ከማዞር ደረጃ እንዲደርስ ነው ያደረገው። ሁኔታው እያደር ታዲያ ብዙ መስዋዕትን መጠየቁም አልቀረም። እናም ወደ ምሥራቅ ከፈሰሰው 1,3 ቢሊዮን ኤውሮ ሁለት-ሶሥተኛው ለማሕበራዊ ድጎማ መውጣቱ ግድ ይሆናል። ዛሬም ቢሆን የምሥራቁ ሥራ አጥ ቁጥር ከምዕራቡ እጅግ የላቀ ነው።

እርግጥ በ 1990 የኤኮኖሚ፣ የምንዛሪና ማሕበራዊው ውሕደት ሲሰፍንና የቀድሞው ዶቼ-ማርክም የምሥራቁ ምንዛሪ ሲሆን ሂደቱ የተጠቀሰውን መልክ ይዞ መቀጠሉን ያቀደው አልነበረም። በጊዜው የምሥራቁ ነዋሪ ዕርምጃውን ሆ ብሎ ቢቀበለውም ለውጡ ግን ወዲያው በኤኮኖሚው ላይ ከባድ ተጽዕኖ ይኖረዋል። ሕዝቡ የጡረታና የቁጠባ ገንዘቡን እስከ ስድሥት ሺህ የምሥራቅ ማርክ ድረስ ብቻ በዴ-ማርክ አንድ-ለአንድ እንዲለውጥ ይደረጋል። ኩባንያዎች ደግሞ የሠራተኛውን ደሞዝ በዴ-ማርክ መክፈል ይገደዳሉ።

ይህም የምሥራቁን አምራቾች በአንድ ሌሊት ከምዕራቡ የኤኮኖሚ ፉክክር እንዲጋፈጡ ነው ያጋለጠው። እናም በዚህ ሁኔታ ተጎጂ እንጂ ተጠቃሚ አልተገኘም። ራሳቸው የምሥራቁ ነዋሪዎች በአዲሱ ምንዛሪ የውስጥ ምርቶችን ለመግዛት አለመፈለጋቸውም ለሁኔታው መባባስ ተጨማሪ ምክንያት ይሆናል። በጊዜው ነዋሪው ምግብ ይሁን መጠጥ ወይም ቴክኒካዊ ምርቶችና ተሽከርካሪዎች የምዕራቡ ምርት እስካልሆኑ ሊያያቸውም አልፈለገም።

የምንዛሪው ውሕደት የቀድሞይቱን ሶሻሊስት ምሥራቅ ጀርመን ኤኮኖሚ ለውድቀት እንደሚዳርግ በጊዜው ጠበብት ቀደም ብለው ማስጠንቀቃቸው አልቀረም። ሆኖም የጊዜው የፌደራል ጀርመን የፊናንስ ሚኒስትር ቴዎ ቫይግል ዛሬ ሲናገሩ ያኔ “ዴ-ማርክ ወደኛ ካልመጣ እኛ ወደሱ እንሄዳለን” ሲል በምሥራቅ ከተነሣው መፈክር አንጻር ሌላ ምርጫ አልነበረም ባይ ናቸው። ምናልባት እንደገና ወሰን ከመከለል የተለየ! የቀድሞው ባለሥልጣን እንደሚሉት ችግሩ በዚህ ብቻም አያበቃም።

“ሌላም በቁጥጥር ሥር መዋል የነበረበት ተጨማሪ ችግር አልጠፋም። ይሄውም በጊዜው ለምሥራቅ ጀርመን የሶቪየቱ ገበያ መቅረት ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ ፉክክር በበዛበት በዓለም ገበያ ላይ መቆናጠጡ ቀላል ነገር አልሆነም”

ለማንኛውም በተዋሃደች ጀርመን ዛሬም ቢሆን የኤኮኖሚው አቅም እኩል የተከፋፈለ ሣይሆን እንደቀጠለ ነው። የምዕራቡ ወገድ ኩባንያዎች እርግጥ ምርቶቻቸውን በምሥራቁ ክፍል ይሸጣሉ። የሚያመርቱት ግን በምዕራቡ ክፍል ነው። በምሥራቃዊው ጀርመን ክፍለ-ሐገራት የኢንዱስትሪ የሥራ መስኮች የሚከፈቱት እንግዲህ በቀስታ ነው። በምሥራቅ የኤኮኖሚው አቅም ዛሬም ቢሆን በነፍስ-ወከፍ ከምዕራቡ ሲነጻጸር 71 በመቶውን ያህል ድርሻ ቢይዝ ነው።
ነጻው የኤኮኖሚ ዘርፍ ከሚያወጣው አጠቃላይ ብሄራዊ ምርት አኳያም አማካዩ አቅም ከምዕራቡ ሲነጻጸር በ 66 ከመቶ ብቻ የተወሰነ ነው። በሌላ በኩል የምሥራቁ ማሕበራዊ ወጪ ግን ከምዕራቡ ሃያ ከመቶ ይበልጣል። ሆኖም በውሕደቱ ወቅት የምሥራቅ ጀርመን ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ሎታር-ዴ-ሜዚየር ችግሩ ከውሕደቱ የመነጨ አይደለም ይላሉ።

“ዛሬም ብዙ ነገሮችን የጀርመን አንድነት ውጤት አድርገን እንመለከታለን። ለነገሩ ግን ችግሮቹ የዓለም ኤኮኖሚ አጽናፋዊነት ያስከተላቸው ናቸው። በዓለም ኤኮኖሚ ላይ በተከሰተው የመለወጥ ሂደት የተፈጠሩ ናቸው ለማለጥ ይቻላል። እርግጥ ከውሕደቱ ጋር የተጣበቁ በርካታ ችግሮች አሉን። ግን አንድነቱ የፈጠራቸው አይደሉም”
ያም ሆነ ይህ የቀድሞው የፊናንስ ሚኒስትር ቴዎ ቫይገል እንደሚሉት ውሕደቱ ጀርመንን ጠቀመ እንጂ አልጎዳም። አንድ በየጊዜው የሚያገኙት የአሜሪካ ኩባንያ ሃላፊ ምሥራቅ ጀርመንን በመግዛት ጥሩ ንግድ አላደረጋችሁም በሚል ሰንዝሮት ለነበረው አስተያየትም፤ እርሳቸው እንደሚሉት ምላሻቸው የማያወላዳ ነበር።

“እርግጥ ግንባታው ረጅም ጊዜና ካሰብነው በላይ ገንዘብ ነው የፈጀው። ግን 18 ሚሊዮን ሕዝብ ዛሬ በነጻ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ ይኖራል። እናንተ በአሥር ዓመት የኢራቅ ቆይታችሁ ተመሳሳይ ውጤት ማስመዝገብ ከቻላችሁ ይህን ጥያቄ መልሰህ ልታቀርብልኝ ትችላለህ”

የቀድሞው ባለሥልጣን እንደሚናገሩት የምሥራቁ ግንባታ ከምዕራቡ ሕዝብ ድጋፍ አንጻር በጀርመን ምድር መቼም አቻ ያልታየለት ታላቅ ዕርምጃ ነው። የምሥራቁ ወገን ክፍለ-ሃገራት ገና በራሳቸው የፊናንስ ፍላጎታቸውን ሊያሟሉ ስለማይችሉም ባለበት ይቀጥላል። ይሄው ሕዝብ በግብር መልክ የሚሰጠው የምሥራቅ ግንባታ ድጋፍ መንግሥት እስካሁን ባለው ዕቅድ መሠረት እስከ 2019 መዝለቁ አይቀርም። እንግዲህ በሚቀጥሉት ዘጠኝ ዓመታትም ብዙ ገንዘብ ከምዕራብ ወደ ምሥራቅ ይ’ሸጋገራል ማለት ነው።

ከዚያ በኋላ ምን እንደሚከተል ጠብቆ መታዘቡ ግድ ይሆናል። ምናልባት ድጋፉ ሌላ ስም ይዞ በፌደራሉ ክፍለ-ሐገራት የፊናንስ ማስተካከያ ወይም ማጣጣሚያ ደምብ ሊረጋገጥ ይችላል። በዚሁ መሠረት ሃብታሞቹ ፌደራል ክፍለ-ሐገራት ድሆቹን መርዳት የሚኖርባቸው ሲሆን በምዕራቡ ክፍል ይህ ዛሬም የሚሠራበት ዘዴ ነው።

መሥፍን መኮንን

አርያም ተክሌ