የጀርመን ውህደት 25 ተኛ ዓመት | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 07.10.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የጀርመን ውህደት 25 ተኛ ዓመት

ምሥራቅና ምዕራብ ጀርመን የተዋሃዱበት 25 ተኛ ዓመት ባለፈው ቅዳሜ ተከብሯል ። በያኔው መጠሪያቸው የጀርመን ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የምሥራቅ ጀርመንን እና የጀርመን ፌደራል ሪፐብሊክ የምዕራብ ጀርመንን ውህደት ያፋጠነው ሁለቱን ሃገራት የከፈለው የበርሊን ግንብ መፍረስ ነው ።

«ዓላማዬ ታሪካዊው ሰዓት በሚፈቅድበት ወቅት ህዝባችንን አንድ ማደረግ ነው »ለ16 ዓመታት ጀርመንን የመሩት ና የጀርመን ውህደት አባት በመባል የሚጠሩት የቀድሞ የጀርመን መራሄ መንግሥት ሄልሙት ኮል ምኞት ነበር ። ኮል ምኞታቸው ምኞት ብቻ ሆኖ አልቀረም ። በጎርጎሮሳውያኑ ጥቅምት 3 ፣1990 እውን ሆነ ። ለ28 ዓመታት ሁለት አገር ሆነው በግንብ ተለይተው የቆዩት ምሥራቅና ምዕራብ ጀርመን በይፋ ተዋሃዱ ። ታሪካዊው የምዕራብና ምሥራቅ ጀርመን ውህደት ባለፈው ቅዳሜ 25 ዓመት አለፈው ።በያኔው መጠሪያቸው የጀርመን ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የምሥራቅ ጀርመንን እና የጀርመን ፌደራል ሪፐብሊክ የምዕራብ ጀርመንን ውህደት ያፋጠነው ሁለቱ ሃገራት የከፈለው የበርሊን ግንብ መፍረስ ነው ።ለግንቡ መፍረስ መነሻ የሆነው ደግሞ በጎርጎሮሳውያኑ ህዳር 9፣ 1989 የያኔው የምሥራቅ ጀርመን ገዥ ፓርቲ ማለትም የጀርመን ሶሻሊስታዊ አንድነት ፓርቲ ሃላፊና ፖሊት ቢሮ አባል ጉንተር ሻቦቭስኪ ይፋ ያደረጉት አዲስ የጉዞ ህግ ነበር ።

«እያንዳንዱ የጀርመን ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ(የምሥራቅ ጀርመን) ዜጋ የGDRን የድንበር ኬላዎች ተሻግሮ ወደ ውጭ መጓዝ እንደሚችል ዛሬ አንድ ደንብ አውጥተናል ። »
ሻቦቭስኪ ይህን ባሳወቁ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ በሺህዎች የሚቆጠሩ ምሥራቅ ጀርመኖች ወደ ምዕራብ ጀርመን መጉረፍ ጀመሩ ። ከዚያ ቀደም ሲል በዚሁ ዓመት በበጋ ወራት በ10 ሺህዎች የሚቆጠሩ ጀርመኖች በሃንጋሪና በኦስትሪያ ድንበሮች በኩል ወደ

Deutschland DDR Volkskammer Abstimmung zum Beitritt

ሄልሙት ኮል

ምዕራብ ጀርመን ገብተዋል ። በታሪካዊቷ ህዳር 9 በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ህዝቦች የቀድሞዋን የጀርመን ዋና ከተማ በርሊንን ለሁለት በከፈለው በበርሊን ግንብ ዙሪያ ተሰባሰቡ ። በማግስቱም ጀርመናውያን ግንቡን ማፍረስ ጀመሩ ። በጥቂት ወራት ውስጥ የቀዝቃዛው ጦርነት ምልክት የነበረው ሁለቱን ጀርመኖች ከጎርጎሮሳዊው 1961 እስከ 1989 ለያይቶ ያቀየው የበርሊን ግንብ እንዳልነበረ ሆነ ። ምሥራቅ ጀርመን የገነባችው ይህ ግንብ ምዕራባዊ በርሊንን ፣ ከሚያዋስኗት ምሥራቅ ጀርመንና ምሥራቅ በርሊን የነጠለ ነበር ። የበርሊን ግንብ መፍረስ ከጀመረ ከ4ተኛው ቀን በኋላ የምሥራቅ ጀርመን ህዝቦች ፓርቲ ሃንስ ሞድሮውን በመሪነት መረጠ ። የምዕራብ ጀርመን ፓርላማ ቡንደስታግ ደግሞ በይፋ ስለ ጀርመን ውህደት መነጋገር ጀመረ ።ህዳር 20 1989 በምሥራቅ ጀርመንዋ በድሬስደን ከተማ ሩብ ሚሊዮን የሚደርስ ህዝብ አደባባይ ewheደቱን በመደገፍ አደባባይ ወጣ ።የበርሊን ግንብ ከፈረሰ በኋላ በተከተሉት ሶስት ሳምንታት ውስጥ ከተከሰቱት ሁኔታዎች ብዙዎች ፍፁም የማይታሰቡ ነበሩ ። አንዳንዶቹ ደግሞ ሊሳኩ እንደሚችሉ መገመት ይቻል ነበር ። በወቅቱ የውህደት ሃሳብ አንገብጋቢው ጉዳይ ነበር ። ከዚሁ ጋር ኮንፌደሬሽንና የGDR ሶሻሊስታዊን መንገድ ማሻሻል በዚያን ጊዜ የመነጋገሪያ ነጥቦች ነበሩ ። እነዚህን የተለያዩ ሃሳቦች በአንድ አቅጣጫ የሚመሩበትን መንገድ ይፈልጉ የነበሩት የዚያን ጊዜው የምዕራብ ጀርመን መራሄ መንግሥት ሄልሙት ኮል ህዳር 28 ለጀርመን ምክር ቤት ቡንደስታግ ባለ አስር ነጥብ እቅድ አቀረቡ ።ይህም ወደ ብሄራዊ ህብረት የሚወስድ እቅድ ነበር ።

«ወደፊት በዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚመረጥ መንግሥት ካለ ያ ልዩ አጋጣሚ ይፈጥራል ። ደረጃ በደረጃ ተቋማዊ የሆነ አዲስ የትብብር ዘዴ ሊፈጥርና ሊስፋፋም ይችላል ። ይህ ዓይነቱ አብሮ የማደግ ሂደት የጀርመንን ታሪክ ቀጣይነት ያሳየናል ። እንዲህ ዓይነቱ መንግሥታዊ አደረጃጀት ኮንፈደሬሽንና ፌደሬሽን ሁሌም በታሪካችን ነበር ።ከዚህ ታሪካዊ ተሞክሮ በመነሳት አንዲት የተዋሃደች ጀርመን ምን ልትመስል እንደምትችል ልንገነዘብ እንችላለን ። ያ ምን ሊሆን እንደሚችል ዛሬ የሚያውቅ የለም ።ጀርመን ያለ ህዝብ ከፈለገ አንድነቱ መምጣቱ የማይቀር መሆኑን እርግጠኛ ነኝ ። »

ታህሳስ 3 ምሥራቅ ጀርመኖች እንደገና ለተቃውሞ አደባባይ ወጡ ። ጫናው የበረታበት የምሥራቅ ጀርመን መንግሥት ባለሥልጣናትና የገዥው ፓርቲ ከፍተና አመራር አካላት ሥልጣናቸውን ለቀቁ ።ታህሳስ 19 ሄልሙት ኮል ድሬስደን ተገኝተው ያሰሙት ንግግር ለውህደት የጓጉትን የብዙዎች ጀርመኖች ስሜት አነሳሳ ።በሰላምና በነጻነት የሚዋሃድን ህዝብ ዓላማ ያሳወቁበት ይህ ንግግራቸውም የዓለም ዓቀፉን ማህበረሰብ ትኩረት ሳበ ።

«ዓላማዬ ታሪካዊው ሰዓት በሚፈቅድበት ወቅት ህዝባችንን አንድ ማደረግ ነው »

ኮልም ከአጠቃላዩ ፖለቲካዊ ህይወታቸው በተለይ ድሬስደን የተገኙበት አጋጣሚ በእጅጉ ከመሰጧቸው ጉዳዮች አንዱ መሆኑን ተናግረዋል ።በምሥራቅ ጀርመን ታሪካዊው የለውጥ ሂደት ቀጥሉ መጋቢት 18 ፣1990 በጀርመን ታሪካዊ ምርጫ ተካሄደ ። በዚህ ምርጫ ወግ አጥባቂው የኮል ክርስቲያን ሶሻል ዲሞክራት ፓርቲ አሸነፈ ።ከዚህ በኋላ የጀርመን ውህደት እውን መሆን እንዲሁም በምሥራቅ ጀርመን የማህበራዊ ገበያ ኤኮኖሚ ሥራ ላይ እንደሚውል አላጠራጠረም ። በያኔዋ የምዕራብ ጀርመን ዋና ከተማ ቦን የኤኮኖሚ የገንዘብ ና የማህበራዊ ህብረት ስምምነቶች ተፈረሙ ። አነዚህ ስምምነቶችም በዚሁ ዓመት ከሐምሌ አንድ አንስቶ ተግባራዊ እንደሚሆኑ ተገለፀ ። የGDR ዜጎች በምዕራብ ጀርመን ገንዘብ መገበያየት ጀመሩ ። ሐምሌ አጋማሽ ላይ በውጭ ፖሊሲ ዘርፍ የምትዋሃደው ጀርመን የNATO አባልነት የሞስኮ ስጋት ሆኖ ነበር ። ሆኖም የያኔው የሶቭየት ህብረት ኮምኒስት ፓርቲ ዋና ፀሃፊ ሚኻኤል ጎርባቾቭ እና ኮል በወቅቱ ሩስያ ውስጥ ካካሄዱት ውይይት በኋላ የሩስያ ስጋት ተነስቶ በሃሳቡ ተስማማች ። በነሐሴ ወር የውህደቱ ጉዳይ መፋጠን ያዘ ነሐሴ 23 የGDR ፓርላማ ተበትኖ ከጀርመን ፌደራል ሪፐብሊክ ምክር ቤት ጋር ተቀላቀሉ ። መስከረም 12 የቦን አስተዳደር ሶቭየት ህብረት ቀዩን ጦርዋን ከምሥራቅ ጀርመን ለማስወጣትዋ ጀርመን 12 ቢሊዮን የጀርመን ማርክ ሰጠ ።ጎርባቾቭ ይህ በቂ አይደለም ብለው በመጠየቃቸው ሶስት ቢሊዮን ማርክ ጨመሩላቸው ኮል ። እርሳቸውም ተቀበሉት ።በዚያው እለት የምሥራቅና የምዕራብ ጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች

Deutschland Kohl stellt den Zehn-Punkte-Plan für die Wiedervereinigung vor

የምሥራቅ ጀርመን ምክር ቤት በጎርጎሮሳዊው 1990ውህደቱን ሲያፀድቅ

ፈረንሳይ ብሪታንያ ዩናይትድ ስቴትስና ሶቭየት ህብረት በተገኙበት ሞስኮ ውስጥ በተካሄደ የፊርማ ስነስርዓት ታሪካዊውን ምዕራፍ ከፍፃሜ አደረሱ ።ጥቅምት ሦስት የምሥራቅ ጀርመኑ ህዝባዊ ፓርቲ የመጨረሻውን ስብሰባ አካሄደ ።በዚያን እለት የሁለተኛው ዓለም ጦርነት ድል አድራጊዎች በጎርጎሮሳዊው 1945 የናዚ ጀርመን ጦር ኃይል ከተሸነፈ በኋላ በጀርመን የነበራቸውን ልዩ መብትና ጥቅሞች ኒውዮርክ ውስጥ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸው በተገኙበት አነሱ ።በዚሁ ዕለት እኩለ ለሊት ከመሆኑ በፊት ምሥራቅ ጀርመን ከኔቶው ተቀናቃኝ ከሶሻሊስቶቹ የዋርሶ ስምምነት አባልነት ወጣች ። የጀርመን ባንዲራም በበርሊኑ የጀርመን ምክር ቤት ዳግም ተውለበለበ ። ይህን ስነ ስርዓት ከ2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በስፍራው ተገኝተው ተከታትለውታል ።

ምሥራቅና ምዕራብ ጀርመን ከተዋሃዱ በኋላ ባለፉት 25 ዓመታት ጀርመን በኤኮኖሚ ተጠናክራ ከግንባር ቀደሞቹ አንዷ ናት ። በአውሮፓ ህብረት ኃይሏና ተሰሚነቷ እያደገ ሄዷል ። በምሥራቃዊ ጀርመን ብዙ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ተካሂደዋል ። እስከዛሬ ድረስ ለምሥራቅ ጀርመን መልሶ ግንባታ ከሃገሪቱ ሠራተኛ የሚሰጠው የገንዘብ ድጋፍ ቀጥሏል ። ምሥራቁን ከምዕራቡ ለማስተካከል የሚደረገው ጥረት ቀጥሎ በተካሄደባቸው ጊዜያት በምሥራቅ ጀርመን ብዙ ለውጦች ታይተዋል ። ከመካከላቸው የምሥራቁ ክፍል ነዋሪ መቀነስ ሥራ አጥነት መስፋፋት እንዲሁም የቀኝ አክራሪዎች መጠናከርና የውጭ ዜጎች ጥላቻ ማቋጥቆጥ ይጠቀሳሉ ።

ኂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic