የጀርመን ውህደት አባት ሄልሙት ኮል | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 02.10.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የጀርመን ውህደት አባት ሄልሙት ኮል

ከብዙ ጥረት በኋላ ኮል ለዚያን ጊዜው የሶቭየት ህብረት መሪ ሚካኤል ጎርባቾቭ የጀርመንን ውህደትና የሶቭየት ወታደሮችም ከምስራቅ ጀርመን እንዲወጡ ለማሳመን በቁ ። የበርሊን ግንብ በፈረሰ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እ.ጎ.አ ጥቅምት 3 1990 የጀርመን ውህደት በሬችትና በፌሽታ ተከበረ ።

የጀርመን ውህደት አባት ሄልሙት ኮል
የቀድሞው የጀርመን መራሄ መንግሥት ሄልሙት ለመጀመሪያ ጊዜ መራሄ መንግሥት ከሆኑ ትናንት 30 አመት ሆናቸው። በጀርመን ፊደራል ሪፐብሊክ ታሪክ ረዥም ጊዜ ሥልጣን ላይ የቆዩት ኮል ምዕራብና ምሥራቅ ጀርመንን ዳግም በማዋህድ ትልቅ ሚና የተጫወቱ መሪ ናቸው ። የዛሬው አውሮፓና ጀርመን ዝግጅታችን በኮልና ለጀርመን ውህደት ባደረጉት አስተዋጽኦ ላይ ያተኩራል ። ለቅንብሩ ሂሩት መለሰ ።

የጀርመን ፌደራል ሪፕብሊክ 6 ተኛው መራሄ መንግሥት ሄልሙት ኮል በጀርመን ታሪክ ልዩ ስፍራ የሚሰጣቸው መሪ ናቸው ። ለ 16 አመታት በተከታታይ ጀርመንን ከመምራታቸውም በላይ ለጀርመን ውህደት ብሎም ለአውሮፓ የፖለቲካ ና የምጣኔ ሃብት ህብረት የጎላ ድርሻ አበርክተዋል ። የበርሊን ግንብ ከመፍረሱ አንድ ቀን አስቀድሞ የያኔው የጀርመን መራሄ መንግሥት ሄልሙት ኮል ከርሳቸው በፊት መራሄ መንግሥት የነበሩት ሶሻል ዲሞክራቱ ቪሊ ብራንድት እንዲሁም ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃንስ ዲትሪሽ ጌንሸር በምዕራብ በርሊኑ የሾነንበርገር ማዘጋጃ ቤት ተገኝተው ንግግር አድርገው ነበር ። ብራንት ና ጌንሸር በያኔው ንግግራቸው ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ ጀርመን ለመንቀሳቀስ የተገኘው የጉዞው ነፃነት ቀጥሎ ፣ የፖለቲካው ነፃነት መከተል እንደሚገባው ና የምሥራቅ ጀርመን ህዝብም የወደፊት እጣውን ራሱ መወሰን እንደሚገባው አሳሰቡ ። ኮል ግን በንግግራቸው ከዚህም የላቀ ጉዳይ ነበር ያነሱት


« በጀርመን ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ DDR ለተጨማሪ ነፃነትና ለእድገት የሚካሄደውን ለውጥ ለጀርመን ህዝብ አንድነት ስንል ባለብን የሞራል ግዴታ ድጋፍ እንሰጣለን ። ጉዳዩ የጀርመን ጉዳይ ነው ፤ የአንድነት ፣ የፍትህና የነፃነት ጉዳይ ነው ። ነፃው አባት አገር ጀርመን ለዘላለም ይኑር ፤ ነፃዋ አውሮፓችን ለዘላለም ይኑር »
ኮል በንግግራቸው የጠቀሱት ‚ነፃ አባት አገር ጀርመን ‘የሚለው አባባል የትልቋ ጀርመን መጥፎ ትዝታ ላላቸው ለተወሰኑ ግራ ኃይሎች ተንኳሽ አገላለፅ ነበር ። ጎረቤት የአውሮፓ አገሮችም ሳይቀሩ በበርሊኑ ግንብ መፍረስ ቢደሰቱም ይህን መሰሉ ስጋት አድሮባቸው ነበር ይሁንና በተወሰኑ ጀርመኖችም ሆነ በአውሮፓ ሃገሮች ላያ ያደረውን ይህን መሰሉን ስጋት ኮል ለማስወገድ ችለዋል ። ከብዙ ጥረት በኋላ ኮል ለዚያን ጊዜው የሶቭየት ህብረት መሪ ሚካኤል ጎርባቾቭ የጀርመንን ውህደትና የሶቭየት ወታደሮችም ከምስራቅ ጀርመን እንዲወጡ ለማሳመን በቁ ። የበርሊን ግንብ በፈረሰ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እ.ጎ.አ ጥቅምት 3 1990 የጀርመን ለሁለት መከፈል ምልክት በነበረው በበርሊኑ የብራንድንቡርግ በር የጀርመን ውህደት በሬችትና በፌሽታ ተከበረ ።
ድምፅ……………………………………..ሪችት


ኮል ራሳቸውን „አጋጣሚን መጠቀምን የታሪክን ካባ አጥብቆ ለመያዝ አስፈላጊ ነው „ በሚል ይገልጹት ነበር ። ልዩ ትኩረታቸው የነበረው ግን ራሷን ለቻለች የጋራ አውሮፓ ነበር ። የሉድቪክሃፈኑ ወጣቱ ሄልሙት ኮል ጦርነቱ ሲያበቃ ከቢጤዎቻቸው ጋር ወደ ፈረረንሳይ ድንበር ተጉዘው ነበር ። ፖለቲከኛ ከሆኑ በኋላም ኮል እንደዚህ ብለው ተናግረው ነበር ።
«ለኛ ለጀርመኖች የአውሮፓ አንድነት መርህን ይዞ መቀጠል የወደፊት እጣ ፈንታችንን እናኛነታችንን ወደ መጥፎ አቅጣጫ ያመራዋል ተብሎ የሚያከራክር ግልፅ ምክንያት አይኖርም ። የአውሮፓ አንድነት መርህ ከመከተል ውጭ ሌላ አሳማኝ አማራጭ አይኖረንም ። »
ከኮል ፍላጎቶች አንዱ ፣ ትክክለኛ ነው ብለው ያመኑበትን ሃሳብ ከፍፃሜ ለማድረስ ሥልጣን መያዝ ነበር ። ለዚህ ሊያበቃቸው ወደሚችለው የፖለቲካው አለም የገቡት በለጋ እድሚያቸው ነበር ። በ 17 አመታቸው ነበር የወግ አጥባቂው የጀርመን ክርስቲያን ዲሞክራት ህብረት ፓርቲ አባል የሆኑት ። ለመጀመሪያ ዲግሪያቸው በኋላም ለዶክትሬት ዲግሪያቸው ታሪክ ህግና የመንግሥት አስተዳደር ና መርህን በሚያጠኑበት ወቅት ኮል በፖለቲካው ንቁ ተሳታፊ ነበሩ ። በ 29 አመታቸው ራይንላንድፋልስ ፓርላማ ገቡ ። በ 33 አመታቸው ደግሞ በፓርላማው የ ፓርቲያቸው ሊቀ መንበር ሆኑ ።

በወቅቱ በጀርመን ፌደራዊ ክፍለ ሃገር ለዚህ ደረጃ በመብቃት ኮል በእድሜ ትንሹ ፖለቲከኛ ነበሩ ። ከ 6 አመታት በኋላም የፌደራል ክፍለ ሃገሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኑ ። 39 አመታቸው ነበር ያኔ ። ኮል በዚህ ሃላፊነት ለ8 አመታት አገልግለዋል ። እ.ጎ.አ በ1971 ለ ፓርቲያቸው ለክርስቲያን ዲሞክራት ህብረት ሊቀ መንበርነት አመልክተው ከ2 ዓመት በኋላ ተሳክቶላቸው እ.ጎ.አ ሰኔ 1973 የፓርቲውን ሊቀ መንበርነት ሥልጣን ያዙ ። በዚሁ ሥልጣናቸው 25 አመታት ቆይተዋል ።
ሊቀመንበር በሆኑበት እጎአ በ1970 ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ ነበር ። «መራሄ መነግሥት መሆን እፈልጋለሁ ። ምርጫውን አሸንፌ መራሄ መንግሥት መሆን እፈልጋለሁ ። »
እጎአ በ1976 ይህ ምኞታቸው ወደ መሳካቱ ተቃርቦ ነበር ። እ.ጎ.አ በ1976 አጠቃላይ ምርጫ ኮል የእህትማማቾቹ የክርስቲያን ዲሞክራትና የክርስቲያን ሶሻል ህብረት እጩ ተወዳዳሪ ሆነው ቀረቡ ። በዚሁ ምርጫ 48.6 በመቶ ድምፅ አገኙ ። ይህም በፓርቲያቸው ታሪክ ሁለተኛ ደረጃ የሚይዝ ከፍተና ድምፅ ነበር ። ይሁንና በወቅቱ በሄልሙት ሽሚት ይመራ የነበረውን የሶሻል ዲሞክራቶቹንና የነፃ ዲሞክራቶቹን ጥምር መንግሥት ግን ማሸነፍ አልቻሉም ። ከ 6 አመት በኋላ እጎአ ጥቅምት 1 ፣ 1982 የዛሬ 30 አመት የኮል ምኞት ተሳካ ። ያኔ በፓርላማው በተሰጠ የመታመኛ ድምፅ ከሶሻል ዲሞክራቶቹ ፓርቲ ጋር ተጣምረው ይሰሩ የነበሩት ነፃ ዲሞክራቶች በመሪያቸው በሃንስ ዴትሪሽ ጌንሸር ቀስቃሽነት አፈንግጠው ከክርስቲያን ዲሞክራት ህብረት ጋር መጣመርን በመምረጣቸው የፌደራሉ መንግሥት ፈረሰና ኮል መራሄ መንግሥት ሆነው አዲስ አስተዳደር መሰረቱ ። ሥልጣን በያዙበት በጥቅምት 1 ፣ 1982 ባሰሙት የመርህ ንግግራቸው የመንፈስና የሞራል ለውጥ መካሄድ እንደሚገባና በትግሉ ውስጥ ግራዎቹ የያዙትንም አቋም በግልፅ አስረዱ ።

Die nordrhein-westfälische Ministerpräsidentin Hannelore Kraft (SPD) spricht am Montag (03.10.2011) beim Festakt zum Tag der Deutschen Einheit im WCCB, dem ehemaligen Bundestag, in Bonn. Das Fest zum 21. Jahrestag der Wiedervereinigung wird gemeinsam mit dem 65. Gründungstag Nordrhein-Westfalens bereits seit Samstag (01.10.2011) gefeiert. Foto: Rolf Vennenbernd dpa/lnw


« የነፃ የንግድ ተቋማትና የግለሰቦችም ነፃ እንቅስቃሴ መንግሥት በበላይነት ከሚቆጣጠረውና ከሚጫነው አሰራር የተሻለ ነው የሚል እምነት አለን ። መፃኤ እድሉን በራሱ የሚወስን ዜጋ ላይ እምነት አለን »
እ.ጎ.አ በ 1983 በተካሄደ ወቅቱን ባልጠበቀ ምርጫ እጅግ አድካሚ ከሆነ የምርጫ ዘመቻ በኋላ ድል ተቀዳጁ ። ብዙም ሳይቆዩ በመንግሥታቸው አዲስ የምጣኔ ሃብትና የማህበራዊ መርህ ተግባራዊ ማድረግ ጀመሩ ። ከዚህ በኋላም በቀደሙት ዓመታት እጅግ ከፍተኛ የነበረው የጀርመን አመታዊ እዳ ማሽቆልቆለ ጀመረ ። ይሁንና የኮል መንግሥት ሥራ አጥነትን መቆጣጠር አልቻለም ። በዚህ የተነሳም የህዝብ ቅሬታ እየጨመረ በመምጣቱ የ1987 ቱ አጠቃላይ ምርጫ ውጤት ጥሩ የሚባል አልነበረም ። የጀርመን ውህደት አስቀድሞ ባይመጣ ኖሮ ኮል ቀጣዩን የ1990 ውን ምርጫ ማሸነፋቸው አጠራጣሪ ነበር ። እጎአ በ1980 ዎቹ መጨረሻ የሶቭየት ህብረቱ መሪ ሚካኤል ጎርባቾቭ ፕሬስቶሪካ ለውጥና ግላስኖስት ግልፅነት ብለው በጀመሩት የፖለቲካ መርህ ኮል ለዘለቄታው ተጠቃሚ መሆን ችለዋል ።

እጎአ ሰኔ 1989 ጎርባቾቭን በያኔው የምዕራብ ጀርመን ዋና ከተማ ቦን ተቀብለው ካስተናገዱ በኋላ የተለያዩ ድርጊቶች በፍጥነት ይከናወኑ ጀመር ። ከጥቂት ወራት በኋላ የበርሊኑ ግንብ ፈረሰ ። ሄልሙት ኮልም በፍጥነት ይለዋወጥ የነበረውን ሁኔታ በመጠቀም ሁለቱ የጀርመን ሪፐብሊኮች የሚዋሃዱበትን 10 ነጥብ የያዘ እቅድ አቀረቡ ። ያቀረቡት እቅድ ተቀባይነት አግኝቶም ምሥራቅና ምዕራብ ጀርመን የዛሬ 22 አመት ለመዋሃድ በቁ ። በወቅቱ ሁለቱ ጀርመኖች ከተዋሃዱ ኃይላቸው ይጠናከራል ብሄሔረተኛም ይሆናሉ የሚለውን ስጋት ለማለዘብም ሞክረዋል ። ኮል ለጀርመን ውህደት የተቻላቸውን ሁሉ ጥረት አድርገው ቢሳካላቸውም ውህደቱ ያስከተላቸውን መዘዞች ግን መቋቋም አልቻሉም ። ከውህደቱ በኋላ የመንግሥት ወጪዎች ከቁጥጥር ውጭ መሆን ጀመሩ ። በተዋሃደችው ጀርመን ያበበው የሥራ እድል ብዙም አልዘለቅም ። ሳይቆይ የሥራ አጡ ቁጥር እየጨመረ መጣ ። ያም ሆኖ ኮል እጎአ የ1994 ቱን ምርጫ ደካማ ተፎካካሪ ስላጋጠማቸው ማሸነፍ ቻሉ ። ሆኖም በቀጣዩ በ1998 ግን ከመሸነፍና ሽንፈታቸውንም በፀጋ ከመቀበል ውጭ ሌላ እድል አልነበራቸውም ።


« የተወዳደርነውና የተወዳደርኩት ምርጫውን ለማሸነፍ ነበር ። በምርጫው ግን ተሸንፈናል ። ሶሻል ዲሞክራቶቹና ና የቀይና አረንጌዴዎቹ ጥምረት ማሸነፋቸው ግልፅ ነው ። ስለ ውጤቱም የሚያከራክር አይደለም ። በዚህም ምክንያት ይህን አጋጣሚ በመጠቀም የኒደር ሳክዘስንን ጠቅላይ ሚኒስትር ጌርሃርድ ሽሩደርን ለአዲሱ እና በጣም አስፈላጊ ለሆነው ሥልጣን በመብቃታቸው ለሃገራችን ጥቅም በመረከባቸው መልካም ምኞቴን እገልፅላቸዋለሁ ። » ።
ኮል ከ 16 አመታት የመንግሥት መሪነት ከወረዱ በኋላ በጀርመን ፓርላማ የተቃዋሚዎችን ቦታ ያዙ ። በአመቱ በሥልጣን ዘመናቸው ከህግ ውጭ በሚስጥር የባንክ ሂሳብ ለፓርቲያቸው የገንዘብ እርዳታ ተቀብለዋል የሚል ዜና መሰራጨት ጀመረ ። ኮል መጀመሪያ ላይ ድርጊቱን አስተባብለው ኋላ ላይ ግን እውነትነቱን አምነዋል ። በቀጣዩ ምርጫ ያል ተወዳደሩት ኮል ከዚያን ጊዜ አንስቶ ከጀርመን የፖለቲካ መድረክ እንደተገለሉ ነው ። ኮል ለመጀመሪያ ጊዜ መራሄ መንግሥት የሆኑበት 30 ኛ አመት በጀርመን ታስቧል ። ይህ የተደረገውም ለጀርመንና ለአውሮፓ ውህደት ያደረጉት ጥረት ትልቅ አስተዋጾ ግምት ውስጥ በማስገባት ነው ።

ሂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic