የጀርመን ዉኅደት ዓመታዊ ክብረ በዓል | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 08.11.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የጀርመን ዉኅደት ዓመታዊ ክብረ በዓል

ጀርመንን ለኹለት ከፍሎ የነበረው የበርሊን ግንብ የተደረመሰበት 25ኛ ዓመት በዓል በበርሊን ከተማ ታሪካዊው የብራንደንቡርግ በር ላይ በሚከናወን የሙዚቃ ድግስ እንደሚጠናቀቅ ተገለጠ።

ግንቡ የነበረበትን የቀድሞው የምስራቅ እና የምዕራብ ጀርመን 15 ኪሎ ሜትሮች ድንበር አቅጣጫ እንዲወክሉ የተቀመጡት በዓየር የተሞሉ ብርሃን ፈንጣቂ 7000 የፕላስቲክ ፊኛዎች(ባሉኖች) ማምሻውን ወደ ሰማይ እንደሚለቀቁ ተነግሯል። ባሉኖቹ ወደ ሰማይ መጥቀው ዓየር ላይ እየተንሳፈፉ መበታተናቸው የበርሊን ግንብ መፈራረስን በተምሳሌትነት ይወክላሉ ተብሏል። የጀርመን መራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ከ25 ዓመታት በፊት የተደረመሰው የበርሊን ግንብ ለሌሎች የነፃነት ንቅናቄዎች አብነት ነው ሲሉ ጠቅሰዋል፤ አያይዘውም «የግንቡ መደርመስ ህልሞች ሁሉ ዕውን ሊሆኑ እንደሚችሉ አሳይቶናል» ብለዋል። የበርሊን ግንብ የተወገደበት 25ኛ ዓመት በዓል መዝጊያ ሥነ ሥርዓት ላይ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል። ጀርመንን ለኹለት ከፍሎ የቆየው ግንብ የተገረሰሰበትና ኹለቱ ጀርመኖች ውህደት የፈጠሩበት 25ኛ ዓመት በርሊን ውስጥ እየተከበረ ነዉ። በ15 ኪሎ ሜትሮች ርዝመት ወደ 7000 የሚጠጉ ክብ አንፖሎች ብርሃን እየፈነጠቁ እንደወሰን ቆሞ የነበረዉን ግንብ ማመላከታቸዉ ለበርሊን ነዋሪዎችና ከመላው ዓለም ለተሰበሰቡ ጎብኝዎች መስህብ መሆናቸዉ ተነግሮአል።
በእዚሁ ክብረ-በዓል አንፑሎቹ ብርሃን በሚፈነጥቁበት አካባቢ ስለ ግንቡ ግንባታና መፍረስ የሚያወሳ ታሪክ ይነገራል፤ የግንቡን ታሪክ ያዩ ምስክርነት በመስጠት ጎብኝዎችን ያነጋግራሉ። የቀዝቃዛዉን የዓለም ጦርነት በተመለከተ በርሊን ላይ በተደረገ አንድ ሲንፖዚየም የቀድሞዉ የሶቭየት ሕብረት ፕሬዚዳንት ሚሃኤል ጎርቫቾቭ የዩክሬይን ቀዉስ አስመልክቶ ምዕራቡ ዓለም ዳተኛ ኹኗል ሲሉ ከፍተኛ ወቀሳ ማሰማታቸዉ ተጠቅሶአል። ጎርቫቾቭ በሲንፖዚሙ ላይ ባደረጉት ንግግር «ዓለም አዲስ የቀዝቃዛ ጦርነትን ተቀብሎአል፤ የነበረዉ እምነትም ባለፉት ወራቶች ተሰብሮአል ብለዋል። የ83 ዓመቱ የሰላም ኖቤል ተሸላሚ ሚሃኤል ጎርቫቾቭ በ1989 ዓ,ም በተደረገዉ ትልቅ ለዉጥ ላይ የተገባዉ ቃል አልተጠበቀም ሲሉ ምዕራቡን ዓለም በተለይም ዩኤስ አሜሪካ ላይ ወቀሳ አሰምተዋል። ቃል ከመጠበቅ ይልቅ የታየዉ የቀዝቃዛዉ ጦርነት አሸናፊ ማንነት ለመግለፅ ሙከራ ሲደረግና የቀድሞ ሶቭየት ሕብረት መከፋፈልን ተከትሎ ጥቅም ለማግኘት ተሞክሮአል ሲሉ መናገራቸዉ ተመልክቶአል። ጎርቫቾቭ የዛሬውን ቀን በተመለከተ «በአውሮጳ የሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ ክብረ በዓል ነው» ሲሉ «ቢልድ» ለተሰኘው ጋዜጣ ተናግረዋል። አያይዘውም ጀርመኖችን ለሁለት ከፍሎ የነበረው ግንብ ተደርምሶ አንድ መሆናቸው፤ ጀርመኖች የቀዝቃዛዉ የዓለም ጦርነት ግብአተ መሬት እንዲፈፀም ትልቅ አስተዋፅኦ አድጓል ብለዋል።
የጀርመን ውህደት ስኬታማነት ገና አለማበቡ
በአንድ ዓመት ጊዜ ዉስጥ 400 ሺ ህዝብ ከምስራቅ ወደ ምዕራቡ የጀርመን ክፍል ሲሰደድ ሁኔታዉ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም። ይህ የሆነዉ በጎርጎረሳዊዉ 1989 ዓ,ም ነዉ። በዓመቱ 400 ሺ ህዝብ ዳግም መኖርያዉን ጥሎ ወደ ምዕራቡ ክፍል ተሰደደ። ከቀድሞዋ ዲሞክራቲክ ጀርመን ወደ ሌላዉ የጀርመን ግዛት በነቂስ መሰደድ የጀመረዉ ሕዝብ ከአካባቢዉ ወደሌላ ይሂድ እንጂ በሀገሩ ወደሌላ ቦታ የመሄድና የመኖር መብቱ የተጠበቀ ነዉ። ከምስራቅ ጀርመን ወደ ምዕራቡ የሚገባዉን እጅግ በርካታ ሕዝብ ቁጥር ተከትሎ ከፍተኛ ጫና በዝያን ግዜዉ የጀርመን መራሄ መንግስት ሄልሞት ኮል ደረሰ። መራሄ መንግሥት ኮል ሁለቱ ጀርመኖች ከተቀላቀሉ ከሶስት ወር በኋላ፤ ከጎርጎረሳዉያኑ ሐምሌ 1, 1990 ዓ,ም ጀምሮ የምሥራቅ ጀርመን ነዋሪዎች በሀገራቸዉ በምዕራብ ጀርመን መኖር እንዲችሉ የመገበያያ ገንዘብ ጥምረት እንደሚደረግ አስታወቁ። ይህ ጉዳይ ዛሬ ዋጋ እያስከፈለ ነዉ።
የኤኮኖሚ ጉዳይን የሚመረምሩ ምሑራን ምክር ቤት «የተከበሩ መራሄ መንግሥት» ብሎ ለመራሄ መንግሥት ሄልሞት ኮል በላከላቸዉ ደብዳቤ ፤ የገንዘብ ጥምረት ከመደረጉ በፊት የኤኮኖሚ ተኅድሶ መደረግ አለበት። ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ የሚፈልሰዉን ሕዝብ ለመግታት በዚህ ፍጥነት የገንዘብ ለዉጥና የጋራ መገበያያ ገንዘብ ማድረጉ ትክክለኛ አለመሆኑን እንገልፃለን» ሲል ፅፎላቸቸዉ ነበር።
ኮል ይህን ሃሳብ አልተቀበሉትም። ከጎርጎረሳዉያኑ ሐምሌ 1, 1990 ዓ,ም ጀምሮ በጀርመን የደምወዝ፤ የቀረጥ፤ የጡረታ ክፍያ በጀርመን የገድሞ ብሄራዊ መገበያያ ማርክ መክፈል ተጀመረ። የምስራቅና የምዕራብ ጀርመን የገንዘብ አንድ ለአንድ እኩል መለወጡ በሁለቱም ማኅበረሰብ ዘንድ ፍሬን አላስገኘም። እንደዉም የምንዛሪዉ መጠን በምስራቅ የገበያዉን ሁኔታ በእጥፍ አናረዉ። በምስራቅ ጀርመን አምባገንን መንግሥት ጊዜ የነበረዉ ምርት ጥራት ከምዕራብ ጀርመኑ ምርት በሶስት እጥፍ ያነሰ ነበር።በመጨረሻም የምስራቅ ጀርመን የኤኮኖሚ ዘርፎች ከምዕራቡ ጋ ዉድድሩን አልቻሉትም። በጎርጎረሳዊዉ 1991 ዓ,ም ላይ የምዕራብ ሠራተኛ ማኅበሮች የሥራ ሰጭዎች ወይም ባለሃብቶች የምሥራቅ ጀርመኖችን ደሞዝ በሚመለከት ለመደራደር ወደ ምሥራቅ ጀርመን ሄደዉ ነበር። በድርድሩ ለምሥራቅ ጀርመን ሠራተኞች ከፍተኛ የደምወዝ ጭማሪ ማድረግ ነበረባቸዉ ሲሉ በጀርመን ሃለ ከተማ የሚገኘዉ የኤኮኖሚ ምርምር ተቋም ጌሃርድ ሃይምፖልድ ይገልፃሉ
ድምፅ 1
«በዓመቱ መጀመርያ ለምሥራቅ ጀርመን ሠራተኞች ከፍተኛ የደምወዝ ጭማሪ ተደረገ። ከዝያ በመቀጠል የደምወዙ እድገት ከምርታማነቱ እድገት በልጦ ተገኘ። ይህ ማለት ደግሞ ባለሃብቶች ይህን መቋቋም አልቻሉም ይህን ተከትሎ በርካታ የኤኮኖሚ ዘርፎች መዘጋት ነበረባቸዉ»
ከዝያም በርካታ የኤንዱስትሪ ዘርፎች ተዘጉ ። ይህ ደግሞ እስከ ጎርጎረሳዊዉ 2005 ዓ,ም በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ የሥራ ቦታዎች እንዲዘጉ ማድረጉን ጌሃርድ ሃይምፖልድ ገልፀዋል። በ1997 ዓ,ም የሥራ አጡ ቁጥር 17,7 በመቶ ደርሷል። በዚህም ምክንያት በርካታ ወጣቶችና ጥሩ የሞያ ስልጠና የነበራቸዉ የምስራቅ ጀርመን ዜጎች ወደ ምዕራብ እንዲፈልሱ ዳርጓል። በጎርጎረሳዊዉ 2005 ዓ,ም በምስራቅ ጀርመን የስራ አጡ ብዛት 18,8 በመቶ መድረሱ ተመዝግቦአል።
በጎርጎረሳዊዉ 2006 ዓ,ም የማገገምያ ዓመት ሆነ። የሥራ አጥ ቁጥር እየቀነሰ መጣ በጎርጎረሳዊዉ 2013 ዓ,ም የሥራ አጡ ቁጥ ወደ10,3 በመቶ ቀንሶ ተገኘ። ይህ ቁጥር ግን አስተዉሎ ላየ ለዉጡን በምስራቅ እና በምዕራብ ጀርመን ብቻ ማየቱ በቂ አይሆንም። ለምሳሌ የምስራቅ ጀርመንዋ ቱሪንገን ግዛት በምዕራብ ጀርመን ከሚገኘዉ ከኖርር ራይን ቬስት ፋለን ግዛት በኤኮኖሚ ተሽሎ ይገኛል። በምስራቅ ጀርመን የሚገኙ አንዳንድ ከተሞች እና ወረዳዎች የሥራ አጥ ቁጥር እንደ ባደን ቩተንበርግና ባየርን ግዛት ሁሉ በአራትና በስድስት በመቶ አስመዝግበዉ ይገኛሉ ።
በምስራቃዊትዋ ጀርመን የጎደለ ነገር ቢኖር ማዋዕለ ንዋይ አፍሳሽ ባለሃብት ነዉ። የጀርመን መዋለ ንዋይ አፍሳሾች ሁሉ ምዕራባዊትዋ የሃገሪትዋ ክፍል ተቀምጠዉ፤ በጀርመን ዛሬም ምስራቅና ምዕራብ የሚል ልዩነት እንዲኖር ዳርገዋል። በምዕራብ ጀርመን የዉጭ ንግድ ኮታ 50 % እጅ ሲሆን በምስራቃዊቱ የሃገሪቱ ክፍል ደግሞ ከ 30% በላይ እጅ ነዉ። ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች በጥቅሉ ብዙ የምርምር ሥራዎችን ያካሂዳሉ, ስለዚህም አዳዲስ የፈጠራ ስራዎችንም

የሚያገኙትም እነሱ ናቸዉ፤ በዉድድሩም ቀድመዉ ይገኛሉ። በምዕራቡ የሚገኘዉ የኤኮኖሚ ዘርፍ 70% ለምርምርና ለእድገት ወጭ ሲያደርግ በምሥራቅ የሚገኘዉ ግን 40% ብቻ ነዉ ማዉጣት የሚችለዉ።እስከ ጎርጎረሳዉያኑ 2030 ዓ,ም በምሥራቅ ያለዉ የሰራተኛ ቁጥር በሚሊዮን ዝቅ እንደሚል ይገመታል። ሲሉ በድሪስደን የመረጃ ተቋም ዮሃኢም ራግኒትዝ ይገልፃሉ

ድምፅ
«የአዛዉንቶች ቁጥር መጨመር እና የሰራተኛዉ የወጣቱ ቁጥር መቀነስ የሚያመጣዉን ችግር ለመቅረፍ ማድረግ የሚቻለዉ እንድ ነገር ብቻ ነዉ አጥጋቢ የሆነ እዉቀትን በከፍተኛ ደረጃ መጠቀም የሚችል ምርምር የተዋለበት ስራ ስራን ማካሄድ ነዉ»
ጥሩ የትምህርት ስልጠና ያላቸዉ ወጣቶች ወደ ምዕራቡ ክፍል መፍለስ እንዲሁም በጀርመን በአጠቃላይ የሚታየዉ በእድሜ የገፉ ነዋሪዎች ቁጥር መጨመር በምሥራቃዊዉ ጀርመን የሚታየዉን ችግር አባብሶታል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ተክሌ የኋላ