የጀርመን ወታደሮች ፀረ ኤቦላ ዘመቻ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 05.02.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የጀርመን ወታደሮች ፀረ ኤቦላ ዘመቻ

የጀርመን ወታደሮች የኤቦላ ተሐዋሲን መስፋፋት ለመግታት በሚካሄደዉ ዘመቻ ለመሳተፍ ወደዚያ ማቅናታቸዉን የሚደግፉ እንዳሉ ሁሉ ስኬት አልታየም በሚል የሚተቹም አልጠፉም። ለዚህ ተግባር ወደላይቤሪያ ዘምተዉ የተመለሱ ወገኖች ላይቤሪያ ዉስጥ የኤቦላ ወረርሽኝ እየቀነሰ መሄዱን ያመለክታሉ።

ለዚህም የጀርመናዉያኑ ተሳትፎ ትልቅ ሚና እንዳለዉም ይጠቁማሉ። የጀርመን አረንጓዴ ፓርቲ ፖለቲከኛ በበኩላቸዉ ወታደሮቹ እዚያ ያለሥራ ለሳምንታት ተቀምጠዋል በሚል ትችት ሰንዝረዋል። ኮሎኔል ዶክተር ዚፈን ፉንከ ከስድስት ሳምንታቱ የላይቤሪያ ግዳጃቸዉ በኋላ ተመልሰዉ የበርሊኑን ቴግል አዉሮፕላን ማረፊያ ገና መርገጣቸዉ ነዉ።ከእሳቸዉ ጋ አብረዉ ለተመሳሳይ ተግባር ሞኖሮቪያ ከቆዩ ስድስት ባልደረቦቻቸዉ ጋ የተመለሱት የጦርኃይሉ ዶክተር አሁን ለየት ያለ ስሜት ነዉ የተሰማቸዉ።

Freiwillige für Kampf gegen Ebola

የበጎ ፈቃድ ዘማቾቹ

«በጣም ደስ የሚል ስሜት ነበር። ላይቤሪያ ዉስጥ ለግዳጅ በቆየንባቸዉ ጊዜያት አዳዲስ የኤቦላ ተጠቂዎች ቁጥር ቀንሷል። ይህ ነዉ ትንፋሽ እንድንወስድ ወይም ወደዚህ እንድንመለስ አጋጣሚዉን የፈጠረልን።»

ኮሎኔል ዶክተር ፉንከ በምዕራብ አፍሪቃ የተባባሰዉን የኤቦላ ተሐዋሲ ስርጭት ለመግታት በበጎ ፈቃደኝነት ነዉ ለመዝመት የወሰኑት። የጀርመን የመከላከያ ሚኒስትር ዑርዙላ ፎን ደር ላይን ባለፈዉ መስከረም ወር ነበር ለዚህ ለየት ያለ ግዳጅ ፈቃደኞች እንዲዘምቱ ጥሪ ያቀረቡት።

«የኤቦላን ወረርሽኝ የመዋጋቱ ጥረት ሁላችንንም ይመለከታል። ይህ ለየት ያለዉ አጋጣሚ ዓለም ዓቀፍ ምላሽ ይጠይቃል። እናም የእኛን ሀገር ጀርመንንም ይመለከታል።»

ነበር ያሉት በወቅቱ። በመጀመሪያ አካባቢ ብዙዎች ያን ያህል በጎ ፈቃደኛ ላይገኝ ይችላል የሚል ጥርጣሬ ነበራቸዉ። በተለይም ወታደሮቹ በበሽታዉ የተያዙትን ረድተዉ ወደሀገራቸዉ ይመለሱ ይሆን በሚል። ኮሎኔል ዶክተር ዚፈን ፉንከ ከኮብለንዝ የጤና ጣቢያ በርካቶች ለዚህ ዘመቻ መመዝገባቸዉን ያስታዉሳሉ።

«ሚኒስትሯ ጥሪዉን ካስተላለፉ በኋላ ያለዉን ነገር ስንመለከት በጣም አስገራሚ ነበር። በትክክል ቁጥሩን ባላስታዉሰዉም በግብረ ኃይሉ ለመካተት በሚያስደንቅ መልኩ ከ5000 በላይ ሰዎች ነበሩ ያመለከቱት።»

Liberia Monrovia DRK & Bundeswehr Ebola-Hilfsstation

በጀርመን ባለሙያዎች የተሠራዉ የጤና ማዕከል

የኤቦላን ስርጭት ለመግታት ባለመዉ በዚህ ፀረ ኤቦላ ግብረኃይል ወደ150 የሚሆኑ የጀርመን ወታደሮች ተካተዋል። ከጀርመን ቀይ መስቀል ጋ በመተባበርም ሞኖሮቪያ ላይቤሪያ ዉስጥ በዓለም የጤና ድርጅት መሪነት የኤቦላ ታማሚዎች ማቆያ ጣቢያ ገንብተዋል። ሆኖም ጣቢያዉ ሥራ የሚጀምርበት ጊዜ ተጓቷል። ለዚህ የተሰጠዉ ምክንያት ደግሞ ከላይቤሪያየጤናጥበቃሚኒስቴርጋ በተፈጠረው አለመግባባትነዉየሚልነዉ። በአጋጣሚዉ ታዲያ የበሽተኞቹ አልጋ የተደረደረበት የእንጨት ወለል መሻገት ጀምሯል። በዚሁ ወቅት በእንጨቱምትክ የሲሚንቶው ወለል ተለስኖ ባበቃበት ጊዜ፣ ጀርመንም በስፍራዉ የጀመረችዉን የሕክምና አገልግሎት መስጫ ጣቢያ በወጉ አጠናቃለች። ኮሎኔል ዶክተር ፉንከ እንደሚሉት፣ የኤቦላ ታማሚዎች ማቆያ ጣቢያ በተከፈተበት ጊዜ ወረርሽኙ በመቀነሱ፣ ወደጣቢያው ሊታከሙ የመጡት የወባ ወረርሽኝ ተጎጂዎች ነበሩ።ሁኔታዉን ያስተዋሉት የጀርመን ጦርኃይል አባላትና የቀይመስቀል ባልደረቦች ለኤቦላ ታማሚዎች የገነቡት ማቆያ ጣቢያ የአካባቢዉ ስጋት የሆነዉን የወባን በሽታ ጨምሮ እንዲከታተል መወሰኑ ግድ ሆነባቸዉ።

ቀደም ሲል ላይቤሪያ፣ ሴራሊዮንና ጊኒ ይታይ የነበረዉ የኤቦላ ስርጭት ፍጥነቱ የተገታ ይመስላል። 95 በመቶዉ የሚሆኑት በበሽታዉ የተያዙ ወገኖች በምርመራ ተለይተዉ የብቻ ማቆያ ስፍራ እንዲገቡ ተደርጓል። እንዲያም ሆኖ ግን የተረፈዉ ሲታይ በሽታዉ በቁጥቋጦ ዉስጥ እንደተሰወረ እሳት ሳይታሰብ በርካቶችን ሊጎዳ የመቻሉ ነገር አሳሳቢ መሆኑን ኮሎኔል ዶክተር ፉንከ ይናገራሉ።

«ቀሪዉ አምስት በመቶ የሚሆነዉ እንደወባ፣ ኮሌራ እና ማጅራት ገትር በመሳሰሉ በሌሎች ተላላፊ በሽታዎች ዉስጥ በጥንቃቄ አድፍጦ የተሰወረ ነዉ።»

በሌላ በኩል የጀርመን የጦር ኃይል አባላት የፀረ ኤቦላ ዘመቻ በሀገሪቱ ምክር ቤት እንደየአረንጓዴዉ ፓርቲ የጤና ፖለቲካ ቃል አቀባይ እምነት እምብዛም ስኬት አላስመዘገበም። አረንጓዴዉ ፓርቲ ስለሀገሪቱ ፀረ ኤቦላ ዘመቻ ማብራሪያ እንዲሰጠዉም ምክር ቤቱን ጠይቋል። ኮርዱላ ሹልስ አሸ ጀርመን በሽታዉን ለመከላከል ለቀረበዉ ጥሪ ምላሿ ዘግይቷል ባይ ናቸዉ። ከመነሻዉ ምንም እንኳን በርካታ የእርዳታ ድርጅቶች የድረሱ ጥሪ ቢያሰሙም በበሽታዉ የተጠቁትን ሃገራት ለመርዳት የተደረገ ነገር እንዳለነበረ እና ጀርመን የወሰደችዉ እርምጃም ያልተቀናጀ ነዉ ሲሉ ተችተዋል።

«ለምሳሌ ወይዘሮ ፎን ደር ላየን ያስተላለፉት የእርዳታ ጥሪ፤ ያለዝግጅት ወደስፍራዉ በድንገት መኮንኖችን የመላክ ርምጃን ማስከተሉ ታይቷል።»

ያም ሆኖ ግን ፖለቲከኛዋ በመጨረሻ የዘመቱት የጀርመን ኃይሎች አዎንታዊ ዉጤት ማሳየታቸዉን ሳይገልፁ አላለፉም።

ፒተር ሂለ/ ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic