የጀርመን ወታደራዊ ስልጠና በማሊ | አፍሪቃ | DW | 29.07.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የጀርመን ወታደራዊ ስልጠና በማሊ

በጎርጎረሳዊዉ 2013 ዓ,ም የተለያዩ ፅንፈኛ እስላማዊ ቡድኖች የማሊዋን መዲና ባማኮ ለመዉረር ጥቂት ነበር የቀራቸዉ። ይህን ተከትሎ የቀድሞዋ ቅኝ ገዥ የፈረንሳይ ወታደራዊ ኃይል የፅንፈኛዉን እስላማዊ ቡድን ጥቃቶች ማጨናገፉ ይታወቃል። በዚያ ወቅት የማሊ ወታደራዊ ኃይል ጥቃቱን ለመመከት አቅምና ችሎታ አልነበረዉም።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:38
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:38 ደቂቃ

የጀርመን ወታደራዊ ስልጠና በማሊ

ከዚህ በኋላ ነበር የአዉሮጳ ሕብረት የወታደራዊ ስልጠና ተልኮ « EUTM» የተቋቋመዉ። በዚህ የወታደራዊ ስልጠና መረሃ- ግብር ላይ ጀርመናዉያን ወታደሮችም ይገኙበታል። ከሁለት ዓመታት በፊት በማሊ የሚገኘዉ ወታደራዊ የሥልጠና ማዕከል ጥቂት ሰልጣኞችን ይዞ ነበር ሥራዉን የጀመረዉ።

Ausbilder der Bundewehr in Mali

ወታደሮች በስልጠና ላይ

በአሁኑ ወቅት ግን «ETUM» ተብሎ በሚታወቀዉ የአዉሮጳ ሕብረት የሥልጠና ተልዕኮ ማዕከል ዉስጥ አንድ ብርጌድ የሚሆን ጦር ለሥልጠና ገብቶአል። በዚህ ማዕከል ምንም እዉቀት ያልነበራቸዉ ፤ ከዚህ ቀደም በነጠላ ጫማ ይዋጉ የነበሩ አሁን የሰለጠኑ ወታደሮች መሆናቸዉን ማሊያዊዉ ሌተናንት ዩሱፍ ዲራ ይናገራሉ። እንደ ዩሱፍ የመድፍ እራት የነበሩት ማልያዉያን በአሁኑ ወቅት ጀሃዲስቶችን ለማባረር በሙሉ ልብ ወደ ጦሩ ሜዳ ይዘምታሉ።
« ስልጠናዉ እጅግ ከፍተኛ የሚባል ነዉ። ሥራችንን በአግባቡ ለመፈፀም በጥሩ ሁኔታ ተዘጋጅተናል። ለዚህም የአዉሮጳ ሕብረት ወታደራዊ ሥልጠና ተልዕኮን «ETUM» እናመሰግናለን። በሰሜናዊ ማሊ ከሚሰጠዉ የአስር ሳምንታት ስልጠና በኋላ፤ ወደ ግንባር ሄደን ጠላትን ለመደቆስ እና ሃገራችንን ከጠላት ለመጠበቅ በጉጉት ነዉ የምንጠብቀዉ።»
የማሊያዉያኑ ጠላት ገና ጨርሶ ሽንፈት አልደረሰበትም። በተለይ በሰሜናዊ ማሊ ያለዉ ሁኔታ በድንገት የሚፈነዳ አደገኛ ደረጃ ላይ ነዉ የሚገኘዉ። ባለፈዉ ሰኔ አጋማሽ በሰሜናዊ ማሊ የሚገኙት የትዋሬግ አማፅያን የባማኮዉን ስምምነት ቢፈርሙም፤ በተመድ ሰላም አስከባሪ «ሚኒሱማ» አልያም በማሊ ወታደራዊ ኃይሎች ላይ አሁንም ጥቃት ማድረሳቸዉ አልቆመም።
ለመገንጠል የሚንቀሳቀሱት እና ጽንፈኛ እስላማዉያኑ የሰላም ስምምነቱን ምን ያህል ያከብሩ እንደሆን የሚታወቅ ነገር የለም። ይህ ባለበት በአሁኑ ወቅት ደግሞ በሃገሪቱ የአዉሮጳ ሕብረት የስልጠና ተልዕኮ በከፍተኛ ሁኔታ ተፈላጊነትን አግኝቶአል። በአሁኑ ወቅት ከወታደራዊ ኃይል መሥራያ ቤት የመጡ 150 ጀርመናዉያን አሰልጣኞችን ጨምሮ ከሕብረቱ 20 ሃገራት የተዉጣጡ 550 ወታደሮች በማሰልጠን መረሃ-ግብሩ ተሳታፊዎች ናቸዉ።

Symbolbild - Tuareg in Mali

የትዋሪግ አማፅያን


በሬድዮ ዘገባዉ ዉስጥ የሚሰማዉ ተኩስ ከሰሜናዊ ባማኮ 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኘዉ የልምምድ ማዕከል ነዉ። የማሊ ወታደሮች ልክ ጦር ሜዳ እንዳሉ በሚያስመስለዉ ድምፅ መሣሪያ እየታገዙ ልምምድ ያደርጋሉ። የጀርመን ወታደራዊ ባለሞያዎች በበኩላቸዉ አሁን በቅርቡ በኒጀር ወንዝ ላይ ክብደት ያለዉና በዉሃ ላይ የሚንሳፈፍ የጦር ተሽከርካሪ እንዴት እንደሚንቀሳቀስ ለማሊ የጦር መርከበኞች ስልጠናን ሰጥተዋል። በሌላ በኩል የተቀበረ ፈንጂና ቦንብ እንዲሁም ሌሎች የሚፈነዱ ነገሮች እንዴት ማክሸፍና መሰብሰብ እንደሚቻል፤ እንዲሁም ዋና መስቀለኛ ጎዳናዎች ጠላት ዘልቆ እንዳይገባ በፍጥነት እንዴት መዝጋት እና መክፈት እንደሚቻል እንዲሁም ፈጣን የመረጃ ልዉዉጥ ስለማድረግም ይማራሉ። አካባቢዉ ላይ ከሚታየዉ 40 ዲግሪ የሙቀት መጠን ጋር ይህ ከፍተኛ ወታደራዊ ሥነ-ስርዓት የተላበሰ ከባድ የስልጠና መርሃግብር ለሰልጣኞቹም ሆነ ለአሰልጣኞቹ እጅግ አድካሚና ከባድ ሥራ መሆኑ አይታበልም።
ጀርመናዊዉ ወታደራዊ ዋና ቃል አቀባይ ቲሞ ቪትዝ ባደረጉት አጠር ያለጉብኝት ለጋዜጠኞች እንደገለፁት ሰልጣኞቹና አሰልጣኞቹ እጅግ ተግባብተዉ ይሰራሉ።
« ማሊ ደሃ ብትሆንም በጣም ዉብ የሆነች ሃገር ናት። ከሁሉ ከሁሉ ሕዝቡ እጅግ ተግባቢ ነዉ። በነበርኩበት የትም ቦታ ሁሉ የማየዉ ጥሩ ፊትና ጥሩ መስተንግዶን ነዉ ያገኘሁት። እዚህ ተቀባይነትን አግኝተናል። እንደ አንድ ግለሰብም ይህ አይነት ስሜት ነዉ ያለኝ»

MINUSMA Soldaten UN Mission Mali

በተመድ ተልኮ የሚኒሱማ ወታደሮች


የማሊ ወታደሮች አሁን በሚያገኙት ስልጠና የጦርነት ላይ ሕግጋቶችና የሰብዓዊ መብት ትምህርት ይሰጣል። ከሁለት ዓመት ተኩል በፊት በማሊ ወታደራዊ ኃይል ላይ እንደታየዉ በጦርነት ወቅት የብቀላ ተግባር ዳግም እንዳይከሰት ገለፃ ይሰጣል።
የፊደራል ጀርመን ፓርላማ ባሳለፈዉ ዉሳኔ መሠረት የጀርመን ወታደሮች በማሊ የመቆያ ጊዜያቸዉ እስከ 2016 ዓም ተራዝሞአል፤ የወታደሮቹም ቁጥር ወደ 350 ከፍ ብሎአል።
ወታደሮቹ በማሊ ያስተምራሉ ያሠለጥናሉ። የጀርመንዋ መከላከያ ሚኒስትር ኡርዙላ ፎን ደርላይን የዛሬ ዓመት በማሊ ወታደሮቹን በጎበኙበት ወቅት ባደረጉት ንግግር ጀርመናዉያኑ ወታደሮች በማንኛዉም የትግል ሜዳ ላይ መሳተፍ አይችሉም።
« አይችሉም ፤ የተሰጠዉ ፈቃድ እንዲያሠለጥኑ እንጂ ጦር ሜዳ ላይ እንዲሳተፉ የሚል አይደለም። ለምሳሌ በጦርነት ወቅት የማሊን ወታደሮችም መርዳትም ሆነ በጦርነቱ መሳተፍን አያካትትም፤ አይፈቀድም።»
በማሊ ጀርመን የተረከበችዉ የአዉሮጳ ሕብረት ወታደራዊ ሥልጠና ተልዕኮ መሪነት ሀገሪቱ በማሊ ያለባትን ኃላፊነት ከፍ ያደርገዋል። በአሁኑ ወቅት ይህ ተልዕኮ መቼ እንደሚያበቃ መናገር ግን አይቻልም።

ሴሲሊያ ራይብል/አዜብ ታደሰ


ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic