የጀርመን ኩባንያዎች በአፍሪቃ | ኤኮኖሚ | DW | 03.04.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የጀርመን ኩባንያዎች በአፍሪቃ

ነዳጅ ዘይት ይሁን ጋዝ፤ መዳብ ይሁን ብረት እንደ አፍሪቃ በተፈጥሮ ጸጋ የታደለ ሌላ የዓለም ክፍል የለም።

default

በሌላ አነጋገር የአፍሪቃን የተፈጥሮ ጸጋ ሌሎቹ ክፍለ-ዓለማት ሊያልሙትም አይችሉም። ታዲያ አፍሪቃ የጥሬ ሃብት ባለጸጋ የመሆኗ ሃቅ የቀሪው ዓለም ፍላጎት በክፍለ-ዓለሚቱ ላይ በግልጽ እያደገ እንዲሄድ ነው ያደረገው።

በመዋቅራዊ ግንባታ ልዋጭ ጥሬ ሃብትን ማግኘት፤ ይህን መሰሉ ትብብር እንዴት ሊራመድ እንደሚችል ቻይና ማሣየት ከጀመረች ዓመታት አልፈዋል። የቻይና መስፋፋት ደግሞ የጀርመንም ሆኑ የሌሎች ምዕራባውያን ሃገራት ኩባንያዎች ሊቋቋሙት ያልቻለ ነገር ሆኖ ነው የቆየው። ይሁን እንጂ በአጭርም ይሁን በረጅም ጊዜ ጨርሶ ዕድል አይኖራቸውም ማለት አይደለም። ዕድል መኖሩን ለምሳሌ ሄረንክኔሽት አክሢዮን ማሕበር የተሰኘው መካከለኛ የጀርመን ኩባንያ በማሣየት ላይ ነው።

ኩባንያው ታላላቅና ትናንሽ መተላለፊያ ዋሻዎች የሚቆፈሩባቸውን መሣሪያዎች የሚያመርት ሲሆን »«ከኛ ጋር የቆፈረ መገናኛ ይፈጥራል» በሚል መርሆ ነው ተግባሩን የሚያራምደው። ሄረንክኔሽት ከአቡ ዳቢ እስከ ሣንት ፔተርስቡርግ፤ በቻይና፣ በበርሊን፣ በኢስታምቡልና አሁን በአፍሪቃም በዓለም ዙሪያ በመቶዎች በሚቆጠሩ ግንቢያዎች ተሳታፊ ሆኖ ነው የሚገኘው፤ ለዋሻ መቅደዱ ተግባር ሃላፊ የሆኑት የኩባንያው ባልደረባ ኡልሪሽ ሻፍሃውዘር እንደሚሉት።

«አዎ፤ እስካሁን ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ አንዳንድ ለምድር ባቡርና ለመንገድ መተላለፊያ ዋሻዎች የሚሆኑ ታላላቅ ፕሮዤዎችን አካሂደናል። የውሃ መተላለፊያ ቧምቧዎች ዝርጊያን የመሳሰሉ የመዋቅራዊ ዘርፍ መለስተኛ ፕሮዤዎችንም እንዲሁ!ይህም ሆኖ ግን ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ገበያው ገና ክፍት ነው። እናም ብዙ ልንሰራ እንችላለን። ደቡብ አፍሪቃ እንግዲህ ዓቢይ ማተኮሪያችን እንደሆነች ወደፊት ትቀጥላለች ማለት ነው»

Solarenergie in der Wüste Flash-Galerie

የጀርመኑ ኩባንያ ሄረንክኔሽት በሰሜናዊው አፍሪቃም በአልጄሪያ፣ በሞሮኮና በግብጽ ተግባሩን ያካሂዳል። በአንጻሩ የማዕከላዊው አፍሪቃ አካባቢ ሃገራት እስካሁን በኩባንያው አጀንዳ ላይ የሰፈሩበት ጊዜ የለም። ግን ይህም ቢሆን እየተቀየረ መሄዱ እንደማይቀር ነው የሚነገረው። ይሁንና ሻፍሃውዘር እንደሚያስረዱት ለጊዜው በመጀመሪያ ሊታሰብባቸው የሚገቡ አንዳንድ ነገሮች አሉ።

«ትልቁ ጠቃሚ ነገር የጸጥታው ሁኔታ ነው። ይህ ለአፍታ እንኳ ከዓይን ሊሰወር አይገባውም። እንግዲህ ደህንነት ተረጋግጧል ብለን ማመን በምንችልበት ጊዜ በፕሮዤው ገቢርነትና በፊናንሱ ሁኔታ ላይ እናተኩራለን። የውሃ መተላለፊያ ቧምቧዎችን በተመለከተ የአካባቢውን የሕዝብ መጠን መጤን ይጠይቃል። የፊናንሱን ሁኔታ የሚወስነው ደግሞ በአንድ አገር ውስጥ ጥሬ ሃብት መኖር አለመኖሩ ነው። እንግዲህ የሚተኮርበት አገር ጥሬ ሃብት ካለው ገንዘቡ ይቀርብለታል። አለበለዚያ ከዓለም ባንክ የገንዘብ ብድር መውሰድ መቻሉ፤ ወይም በመዋዕለ-ነዋይ መልክ ከውጭ ድጋፍ ማግኘቱ አስፈላጊ ነው»

የጀርመኑ ኩባንያ ሄረንክኔሽት በወቅቱ አተኩሮ የሚገኘው በናይጄሪያ ላይ ነው። ይህም ጊዜውን የተከተለ ዕርምጃ ነው ለማለት ይቻላል። በአሁኑ ጊዜ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ካለው ገበያ ጎን ለጎን በርካታ የክፍለ-ዓለሚቱ መንግሥታት የጀርመን ኩባንያዎች የዓይን ማረፊያ እየሆኑ ነው። ከነዚህም ናይጄሪያ አንዷ ናት። በኤኮኖሚ ረገድ በውጭ በተግባር ተሰማርተው ከሚገኙት የጀርመን ኩባንያዎች መካከል ዛሬ ከአፍሪቃ ጋር የሚነግዱት 21 ከመቶውን ድርሻ ይይዛሉ። ከአንድ ዓመት በፊት 18 በመቶ ብቻ ነበሩ።

መረጃውን ያቀረበው በጉዳዩ መጠይቅ ያደረገው የጀርመን ኢንዱስትሪና ንግድ ም/ቤት ነው። እርግጥ ኩባንያዎቹ ወደ አፍሪቃ የሚልኩት ምርት ሲበዛ ትንሽ ነው። የኢንዱስትሪና ንግድ ም/ቤቱ የአፍሪቃና የልማት ፖሊሲ ጉዳይ ሃላፊ የሆኑት ሃይኮ ሽቪደሮቭስኪ እንደሚሉት ከምርቱ ይልቅ የአገልግሎት ዘርፉ ተግባር ያመዝናል።

«ኩባንያዎቹ በአብዛኛው ከመዋቅራዊ ግንባታ ጋር የተያያዙ ናቸው። ብዙዎቹ በአማካሪ የኢንጂነር ቢሮነት ይሰራሉ። ሌሎቹ ደግሞ በትምሕርቱ ዘርፍ የተሰማሩ ናቸው። ማለት ለምሳሌ ጤና ጥበቃ ዘርፍን የተመለከተ የሙያ ሥልጠናና በተለያየ መልክ የቴክኖሎጂ ሽግግር»

ጀርመን ከአፍሪቃ ጋር የምታካሂደው የውጭ ንግድ ከተቀረው ዓለም ሲነጻጸር ገና በጨቅላነት ደረጃ ላይ ነው ያለው ለማለት ይቻላል። አገሪቱ ባለፈው 2012 ዓ-ም ከ 1,1 ቢሊዮን ኤውሮ በላይ የሚያወጣ ምርት ወደ ውጭ ስትልክ ከዚሁ ወደ አፍሪቃ የተሻገረው ድርሻ በ 21 ሚሊያርድ ኤውሮ የተወሰነ ነበር። ይህም ሁለት ከመቶ መሆኑ ነው። ከዚሁ ሁለት በመቶ ድርሻ ለዚያውም አርባ በመቶው ወደ ደቡብ አፍሪቃ የተላከ መሆኑ መዘንጋት የለበትም።

ለንጽጽር ያህል የቻይናና የአፍሪቃ ንግድ በተፋጠነ ዕድገት በመጨመር ባለፈው ዓመት ከ 166 ሚሊያርድ ዶላር በልጦ ነበር። የቻይና ቀጥተኛ መዋዕለ-ነዋይ አቅርቦትም በ 2012 አጋማሽ ላይ በቀረበ መረጃ መሠረት 15,3 ሚሊያርድ ዶላር የሚደርስ ነው። ይህም በአሥር ዓመት ውስጥ ሰላሣ በመቶ ዕድገት ሲሆን ቻይናን መፎካከሩ ቀላል የሚሆን አይመስልም።

ሆኖም ግን ለጀርመን ኩባንያዎች በሩ ሙሉ በሙሉ ተዘግቷል ማለት አይደለም። የጀርመን ኩባንያዎች ለምሳሌ በወቅቱ ከቻይና ግዙፍ መስፋፋት ተጠቃሚ ሆነው ይገኛሉ። ቻይና አፍሪቃ ውስጥ ጥሬ ሃብት ለማግኘት በልዋጩ መዋቅራዊ ግንባታ ታካሂዳለች። ሆኖም ግን አፍሪቃውያን ሸሪኮቿ ቀስ በቀስ ጥራቷን አጠያያቂ ማድረግ ጀምረዋል። አንዳንዶቹ እንዲያውም ሃይኮ ሽቪደሮቭስኪ እንደሚሉት የጀርመን ኩባንያዎችን እንደ ግምቢያ ሃላፊና ጥራት ተቆጣጣሪ በተግባር ማሰማራታቸው እየተስፋፋ በመሄድ ላይ ነው።

«ይሄ የሶሥት ወገን ፕሮዤ የሚሉት ነገር ሲሆን በወቅቱ በተለይም በአንጎላ ጠንካራ በሆነ መልክ የምንታዘበው ነው። መንግሥት እዚያ መንገዶችን ወይም ወደቦችን የማነጽ ኮንትራት ይሰጣል። የጀርመን ኩባንያዎች ደግሞ በጨረታው የዋጋ ፉክክሩን ሊወጡት አይችሉም። ሆኖም በቅርቡ የቻይና የአስተናነጽ የጥራት ዝቅተኛነት በአንጎላውያን ዘንድ ትችት መቀስቀሱ አልቀረም። አንጎላ ውስጥ ዛሬ በቅድሚያ የጀርመን ኩባንያዎችን ቁጥጥር ካለፉ በኋላ የሚከፈቱ አዳዲስ መንገዶች አሉ»

አንጎላ አፍሪቃ ውስጥ በኤኮኖሚ የተፋጠነ ዕድገት በማድረግ ላይ ናቸው ከሚባሉት ሃገራት አንዷ ናት። ሌሎቹ ኬንያና ናይጄሪያን የመሳሰሉ ሀገራትም ከአማካዩ መጠን በላይ ዕድገት እንደሚያርጉ ነው የሚነገረው። ይሁን እንጂ ለጀርመን ኩባንያዎች ይህ ብቻውን በቂ ወይም ማራኪ ነገር አይደለም። ውስጣዊው የፖለቲካ ሁኔታም ወሣኝነት አለው። ይህም እርግጥ የፖለቲካ እርጋታ፤ በጎ አስተዳደር ማለት ነው።

«ሩዋንዳን ብንወስድ አገሪቱ የዓለም ባንክ በሚያወጣው የንግድ ዘገባ በያመቱ ቀደምቱ ቦታ ላይ ሰፍራ ነው የምትገኘው። እርግጥ የአገሪቱ ገቢያ በንጽጽር ውስብስብ ያልበዛውና ትንሽም ነው። ሆኖም አገሪቱ ለመዋዕለ-ነዋይ አቅራቢዎች አመቺ ሁኔታ ለመፍጠር በልዩ ትኩረት በመጣር ላይ ነው የምትገኘው። ታንዛኒያም በዚህ መልክ ከሚታዩት ሃገራት መካከል የምትመደብ ናት። ጋናን ከወሰድን ደግሞ ምዕራብ አፍሪቃይቱ አገር ዴሞክራሲያዊ አስተዳደርን በማስፈን ማራኪ ሆና መቆየቷ ይታወቃል። በተቀረ ጋና በቅርቡ የነዳጅ ዘይት ሃብት ካገኘች ወዲህ ሁኔታው እንዴት እንደሚቀጥል እያደር የሚታይ ነው። በጥቅሉ ግልጽነትንና በጎ አስተዳደርን በተመለከተ በወቅቱ ትኩረት የሚደረግባቸው የአፍሪቃ ሃገራት ብዛት በደርዘን ይቆጠራል»

የጀርመን ኩባንያዎች የተጠቀሱት ቅድመ-ሁኔታዎቹ ከተሟሉ በኢንዱስትሪና ንግድ ም/ቤቱ የአፍሪቃ ጉዳይ ሃላፊ በሃይኮ ሽቪደሮቭስኪ አባባል ከአካባቢው ጥሬ ዕቃ ማውጣት ብቻ ሣይሆን በዚያው ሊያመርቱም ይችላሉ። ይህ እስካሁን በደቡብ አፍሪቃ ብቻ ተወስኖ ነው የቆየው።

« ይህ እኛም እጅግ የምንሻው ነገር ነው። ጉዳዩ በተለይም የምርት መኪናዎችን ወይም ተሽከርካሪዎችን ለሚሸጡት ኩባንያዎቻችን ማራኪነት አለው። ለዚህም ነው ጥሬ ዕቃ ወይም የእርሻ ምርቶች በቅድመ-ባህርያቸው ከአፍሪቃ መውጣታቸው ቀርቶ በዚያው ተሰርተው እንዲያልቁ የበኩላችንን ጥረት የምናደርገው። ለዚህ እርግጥ ቴክኖሎጂ የሚያስፈልግ ሲሆን ይህን ለማቅረብም ዝግጁ ነን»

የደቡብ ጀርመኑ ኩባንያ ሄረንክኔሽትም ቴክኖሎጂን ለማስተላለፍ ይፈልጋል። ሆኖም የኩባንያው ተጠሪዎች ናይጄሪያም ውስጥ ሆነ ሌላ ቦታ መቼ ተግባሩ ሊጀምር እንደሚችል በወቅቱ ለመናገር አይደፍሩም። በተለይም የዋስትናው ጉዳይ ብዙ ጥያቄዎችን የሚያስነሣ እንደሆነ መቀጠሉ የማይቀር ነው የሚመስለው።

መሥፍን መኮንን

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic