የጀርመን ኩባንያዎችና ደቡብ አፍሪቃ | ኤኮኖሚ | DW | 24.10.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የጀርመን ኩባንያዎችና ደቡብ አፍሪቃ

በአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም ዋነኛዋ የጀርመን ኩባንያዎች የኤኮኖሚ ትብብር ማተኮሪያ ደቡብ አፍሪቃና በአጠቃላይም የደቡባዊው አፍሪቃ አካባቢ ነው።

በአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም ዋነኛዋ የጀርመን ኩባንያዎች የኤኮኖሚ ትብብር ማተኮሪያ ደቡብ አፍሪቃና በአጠቃላይም የደቡባዊው አፍሪቃ አካባቢ ነው። ደቡብ አፍሪቃ በክፍለ-ዓለሚቱ በኤኮኖሚ ራመድ ያለችው፤ በተፈጥሮ ሃብትና በምጣኔ-ሃብት አቅምም ጠንካራዋ እንደመሆኗ መጠን ትብብሩ ወይም ሽርክናው ጠለቅ ያለ መሆኑም አልቀረም።

ለጀርመን ኩባንያዎች በአፍሪቃ ታላቋ የውጭ ንግድ ተባባሪ የሆነቸው የደቡብ አፍሪቃ አጠቃላይ ብሄራዊ ምርት ባለፈው 2011 ዓመተ-ምሕረት 294 ሚሊያርድ ኤውሮ ሲደርስ ጀርመን የሸጠችው ምርትም በ 8,6 ሚሊያርድ ኤውሮ የሚገመት ነበር። ይህም የሽርክናውን ጥንካሬ በጉልህ የሚያሳይ ነው።

በአሁኑ ጊዜ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ሰፍረው የሚገኙት የጀርመን ኩባንያዎች ከ 450 የሚበልጡ ሲሆን እነዚሁም ዘጠና ሺህ ሰዎችን ቀጥረው ያሰራሉ። ከኩባንያዎቹ አንዳንዶቹም በአገሪቱ ዘመናዊና እጅግ ጠቃሚ የምርት ተቋማት ሆነው የሚታዩ ናቸው። ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ውክልና ያላቸው ደግሞ ታላላቁ የጀርመን የአውቶሞቢልና የኤሌክትሮኒክ ዘርፍ ኩባንያዎች ለምሳሌ ሜርሤደስን ወይም ዚመንስን የመሳሰሉት ብቻ አይደሉም። በተለይም መካከለኛ ኩባንያዎች በብዛት ሰፍረው ነው የሚገኙት።

የጀርመን የደቡባዊው አፍሪቃ የኢንዱስትሪና ንግድ ም/ቤት ከሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር ትናንትና ዛሬ በርሊን ውስጥ የጀርመንና ደቡብ አፍሪቃ የኤኮኖሚ መድረክ ጉባዔ በማካሄድ ትብብሩ በሚስፋፋበት ሁኔታ መክሮ ነበር። በመድረኩ ላይ 300 ገደማ የሚጠጉ ከፍተኛ የሁለቱ ሃገራት የፖለቲካና የምጣኔ-ሃብት ዘርፍ ተጠሪዎች ተገናኝተው ተነጋግረዋል። የደቡብ አፍሪቃ መንግሥት በተለይም በመዋቅራዊ ልማት ረገድ ዕድገትን ለማራመድ መነሳሳቱ ለመዋዕለ ነዋይ ባለቤቶች ይበልጥ ማራኪ እየሆነ በመሄድ ላይ ነው።

ከመንገድ ሥራ እስከ ሃዲድ ዝርጊያ፤ ከከተሞች ልማት እስከ ታዳሽ ኤነርጂ ምርት ብዙ የመስፋፋት ውጥን አለ። በሌላ በኩል በቅርቡ በደቡብ አፍሪቃ የማዕድን ሠራተኞች ዓድማ ሳቢያ ፖሊስ ተኩስ ከፍቶ ብዙ ሰዎች ከተገደሉ በኋላ ሁኔታው ብዙ የውጭ ኩባንያዎችን ስጋት ላይ መጣሉ አልቀረም። በጉዳዩ የጀርመንን የደቡባዊው አፍሪቃ የኢንዱስትሪና የንግድ ም/ቤት ስራ አስኪያጅ ማቲያስ ቦደንበርግን ዛሬ በስልክ አነጋግሬ ነበር። በርሳቸው አባባል የጀርመን ኩባንያዎች ፈተናውን ተቋቁመው ለማለፋቸው ብዙም ጥርጣሬ የለም።

«ደቡብ አፍሪቃ በደቡባዊው አፍሪቃ አካባቢ ማራኪዋ አገር መሆኗ እርግጥ የታወቀ ነገር ነው። በኤኮኖሚ ረገድም በአካባቢው ሃያሏ ናት። ይህም ባለበት ይቀጥላል። ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በወቅቱ 450 የጀርመን ኩባንያዎች ሰፍረው ይገኛሉ። እንዚህም በእርካታ በተግባር የተሰማሩ ሲሆኑ በዚያው የሚያወጡትን ምርት በአፍሪቃና ከአፍሪቃ ውጭም የሚሸጡ ናቸው። በማዕድኑ ዘርፍ የተከሰተው ዓድማ እርግጥ አንዱን ወይም ሌላውን ስጋት ላይ መጣሉ አልቀረም»

ሆኖም ግን የጀርመን ኩባንያዎች ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ለብዙ ዓመታት የቆዩ ሲሆኑ ከዚህ ቀደም በየጊዜው የተከሰቱ ማዕበሎችንም ተቋቁመው ለማሳለፍ የቻሉ ናቸው። «እርግጥ ዓድማዎቹ በተለመደው የታሪፍ ድርድር በሙያ ማሕበራት ስር የሚካሄዱ አለመሆናቸው ለኩባንያዎች መጨውን ሁኔታ መለየቱን የከበደ ያደርገዋል። የኛ ተግባር ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ኩባንያዎቹ ያደረጓቸው ስምምነቶችና የተያያዙ አካል ደምቦች መከበራቸውን ማረጋገጥ ነው። ይህ ለተሳካ የኤኮኖሚ ትብብር ቅድመ-ግዴታ ሲሆን ለሁለቱም ወገን ጥቅም አስፈላጊነትም አለው»

ግን ይህ ቅድመ-ግዴታ ከሆነ ለመሆኑ በወቅቱ የጀርመን ኩባንያዎች የሚፈልጉት ሁኔታ ተረጋግጧል ለማለት ይቻላል ወይ? ቦደንበርግ ብዙም ስጋት የላቸውም።

«አዎን፤ ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት የጀርመን ኩባንያዎች ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ረዘም ያለ ታሪክ ነው ያላቸው። የኢንዱስትሪና ንግድ ም/ቤታችን ለምሳሌ በቅርቡ፤ ከሁለት ሣምንታት በፊት ምክትል ፕሬዚደንት ሞትላንቴ በተገኙበት 60ኛ ዓመቱን አክብሯል። የጀርመን ኩባንያዎች እንግዲህ ከረጅም ጊዜ አንስቶ በቦታው የሚገኙ ናቸው። በዚሁ ጊዜም እርግጥ ብዙ ውጣ ውረድ የታየባቸውን ሁኔታዎች አሳልፈዋል። አሁንም ታዲያ ችግሩን ተቋቁመው እንደሚያልፉ ዕምነቴ ነው»ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በርካታ መዋዕለ-ነዋይን የሚጋብዙ መስኮች መኖራቸው በተደጋጋሚ ነው የሚነገረው። ለምሳሌ መዋቅራዊውን መስክ ለመጥቀስ ይቻላል። ከከተሞች ልማት እስከ መገናኛና ኤነርጂ ድረስ ኩባንያዎችን ሰፊ ዕድል ነው የሚጠብቃቸው። ይህ የጀርመን የደቡባዊው አፍሪቃ የኢንዱስትሪና የንግድ ም/ቤት ስራ አስኪያጅ የማቲያስ ቦደንበርግም አመለካከት ነው።

«ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ መዋቅራዊ ግንባታ በወቅቱ ትልቁ ጉዳይ ነው። እርግጥ ይህ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ብቻ ሣይሆን አካባቢውንም ይጠቀልላል። ከትራንስፖርት መንገዶች አንስቶ እስከ ወደብ ግንባታ፤ ከባቡር ሃዲድ እስከ አየር ጣቢያዎች ድረስ መዋዕለ-ነዋይ እየተደረገ ነው። በመገናኛ ረገድም እንዲሁ! እንግዲህ መዋቅራዊው ግንባታ ዓቢይ ጉዳይ ነው ማለት ነው። አሁን ሰሞኑን፤ ከአራት ቀናት በፊት ፕሬዚደንት ዙማ በመጪዎቹ ዓመታትና አሠርተ-ዓመታት ሂደት እስከ አራት ትሪሊየን ራንድ ወይም 400 ሚሊያርድ ኤውሮ መዋዕለ-ነዋይ የሚደረግባቸው 18 ፕሮዢዎችን አስተዋውቀው ነበር። ይህ ደግሞ የጀርመንና የአውሮፓ ኩባንያዎች በአካባቢው መዋዕለ-ነዋይ እንዲያደርጉ አበረታችና ማራኪ ነገር ነው»

አፍሪቃ ውስጥ፤ በደቡባዊው አፍሪቃ አካባቢ ጭምር የቻይና መስፋፋት እጅግ ጎልቶ የሚታይ ነገር ነው። በአካባቢው የሕንድና የብራዚል የኤኮኖሚ መስፋፋት ዘመቻም እያየለ መምጣቱ የተሰወረ ነገር አይደለም። ከዚህ አንጻር ደግሞ የጀርመን ኩባንያዎች እየጠነከረ የሚሄደውን ፉክክር መቋቋም ይኖርባቸዋል። እርግጥ እንደ ማቲያስ ቦደንበርግ ከሆነ ለስጋት አንዳች መንስዔ የለም።

«አዎን፤ እርግጥ ነው፤ አሁን የቻይና፣ የሕንድና የብራዚልም ኩባንያዎች ይበልጥ በደቡባዊው አፍሪቃ በተግባር እየተሰማሩ ናቸው። ይህን እርግጥ በጥሞና ነው የምንመለከተው። ሆኖም የጀርመን ኩባንያዎች ወደፊትም በደቡባዊው አፍሪቃ አካባቢ የተሳካ ዕርምጃ እንደሚያደርጉ አልጠራጠርም። ምክንያቱም በኤኮኖሚ እንቅስቃሴያቸው የረጅም ጊዜ የትብብር ልምድ አላቸው። ሽርክናው ነው በተለይ የጀርመን ኩባንያዎች ጥንካሬ! እንግዲህ እኛ በጋራ ፕሮዤዎች ረገድ የደቡብ አፍሪቃ ኩባንያዎች ተባባሪ ነን። በዚህ ስልት ደግሞ ከዚህ ቀደም ስኬታማ ዕርምጃ ስናደርግ የወደፊቱም ከዚህ የተለየ የሚሆን አይመስለኝም»የጀርመን ኢንዱስትሪና ንግድ ም/ቤት ስራ አስኪያጅ ማቲያስ ቦደንበርግ እንዳስረዱት የጀርመን ኩባንያዎች በመጪዎቹ ዓመታት ደግሞ ከደቡብ አፍሪቃ ባሻገር በተለይም ጥሬ ሃብት ባላቸው በአካባቢው ሃገራት ላይ ይበልጥ የማተኮር ውጥን አላቸው።

«ቀደም ሲል እንደጠቀስነው ከ 14 ቀናት በፊት በደቡባዊው አፍሪቃ 60ኛ ዓመት ሕልውናችንን አክብረን ነበር። ከዚህ ባሻገርም ከአካባቢው የኤኮኖሚ ዕርምጃ አንጻር በደቡብ አፍሪቃ ጎረቤት ሃገራት ላይ ይበልጥ ለማተኮር ወስነናል። በተለይም የጥሬ ዕቃን ዋስትና መረጋገጥ በተመለከተ ለምሳሌ በሞዛምቢክ፣ ዛምቢያ፣ ናሚቢያ ወይም ቦትሱዋና!የጀርመን ኩባንያዎች በትብብርና አግባብ ያለው ሥልጠና በመስጠት የታወቁ በመሆናቸው በነዚህ ሃገራት ሰፊ ተቀባይነት ነው ያላቸው»

ይህ ደግሞ ትልቅ መቀራረብን ለመፍጠር እንደሚበጅ የጀርመኑ የኢንዱስትሪና የንግድ ም/ቤት ባልደረባ ጽኑ ዕምነት ነው።

መሥፍን መኮንን

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 24.10.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/16VEu

ተዛማጅ ዘገባዎች

 • ቀን 24.10.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/16VEu