የጀርመን እና የኢጣልያ እግር ኳስ ግጥሚያ | ስፖርት | DW | 28.06.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የጀርመን እና የኢጣልያ እግር ኳስ ግጥሚያ

በፖላንድ መዲና ዎርሶ ዛሬ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ በሚደረገው የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ የጀርመን እና የኢጣልያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድኖች ይጋጠማሉ። አሸናፊው ትናንት ከፖርቱጋል ጋ ተጋጥሞ በፍፁም ቅጣት ምት ለፍፃሜ ጨዋታ ካለፈው በዩክሬይን መዲና ኪየቭ የፊታችን እሁድ የስጳኝ ቡድን ጋ ይጋጠማል።

ይህ በጉጉት የሚጠበቀው ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር የሚታይበት እንደሚሆን ተገልጾዋል።

ፖርቱጋልን፡ ኔዘርላንድስን፡ ዴንማርክን እና ግሪክን አንፎ አሁን ለግማሽ ፍፃሜ የደረሰው የጀርመን ቡድን ካለፉት አሥራ ሰባት ዓመታት ወዲህ ዋንጫ በሚያሰጥ የአውሮጳም ሆነ ዓለም አቀፍ ጨዋታ ላይ አሸንፎት ከማያውቀው የኢጣልያን ቡድን ጋ በዛሬው ዕለት የሚጋጠም ሲሆን፡ ብዙ ጀርመናውያን የ«እርግማን» ያህል የሚቆጥሩትን ሁኔታ ቀይሮ ለፍፃሜ ጨዋታ መብቃት ይጠበቅበታል።


ኢጣልያ ጀርመንን ሦስት ጊዜ፡ ማለትም፡ እአአ በ 1970 ዓም በዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ላይ አራት ለሦስት፡ እአአ በ1982 ዓም በፍፃሜ ግጥሚያ ሦስት ለአንድ ፡ እአአ በ 2006 ዓም በዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ላይ ሁለት ለአንድ ማሸንፍዋ የሚታወስ ነው። በተለይ ከስድስት ዓመታት በፊት በዶርትሙንድ የተሸነፉበት ግጥሚያ ትዝታ አሁንም ትኩስ ነው።

Germany's national soccer coach Joachim Loew gestures during a news conference before their Euro 2012 soccer match against Italy in Gdansk, June 26, 2012. REUTERS/Thomas Bohlen (POLAND - Tags: SPORT SOCCER)

የጀርመን አሰልጣኝ ዮአኺም ለቭ

በዚህም የተነሳ፡ ያለፈውን ወደኋላ በመተው፡ ዛሬ ይህን የሽንፈት ሠንሠለት በመበጠስ ድል አድራጊ ለመሆን ቆርጦ መነሳቱን የጀርመን አልጣኝ ዮአኺም ለቭ አስታውቀዋል።

« ጥንካሬአችን የት ላይ መሆኑን በሚገባ እናውቃለን። በጣም በጣም ጠንካራ ቡድን አለን። ኢጣልያንም ጭምር ለማሸነፍና ወደ ፍፃሜ ጨዋታ ለማለፍ በሚያስችል አቋም ላይ እንገኛለን። »

የቡድኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኦሊቨር ቢርሆፍ ግጥሚያው ቀላል ባይሆንም ቡድኑ ለዛሬ ግጥሚያ በሚገባ መዘጋጀቱን ገልፀዋል።።
« ለኢጣልያን ቡድን ከፍተኛ አክብሮት አለን። እንደሚመስለኝ፡ ጀርመን ባላፉት ጊዚያት በየትኞቹ ጨዋታዎች መሸነፏን በሚመለከት የሚወጡ መዘርዝሮች በተጫዋቾች ዘንድ ሚና አይጫወትም። እርግጥ ይህ ገሀድ ሁሌ ያለ ቢሆንም፡ ይህ ብቻውን ተጫዋቾቹን የሚያስጨንቅ አይመስለኝም። »
ጀርመን ለፍፃሜ ግጥሚያ ማለፍ ከፈለገች የፈጣኖቹን ኢጣልያ ቡድን አከፋፋይ አንድሬ ፒሮልንና የመሀል ተጫዋቹን ማርእዮ ባሎቴሊንና የeብ ጠባቂ ጂያንሉጂ ቡፎንን ጨዋታና እንቅስቃሴ ማደናቀፍ ይኖርባታል።

Italy's Andrea Pirlo controls the ball during the Euro 2012 soccer championship quarterfinal match between England and Italy in Kiev, Ukraine, Sunday, June 24, 2012. (Foto:Ivan Sekretarev/AP/dapd)

የኢጣልያ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋች አንድሬ ፒርሎ


« ወሳኙ እነዚህ ተጫዋቾች የሚንቀሳቀሱበትንና ኳስ ወደሌላ ለማሳለፍ የሚያደርጉትን ትረት እና እንቅስቃሴ ማሰናከሉ ነው። ከዚህ በተጨማሪም የኢጣልያውያኑን የጨዋታ ሥልት አሰናክለን የራሳችንን ጨዋታ መምራት በምንችልበት ሁኔታ ላይ መገኘታችን በጨዋታው ሂደት ላይ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል። »

በጀርመና በኢጣልያ መካከል የሚደረገውና በጉጉት የሚጠበቀውን ጨዋታ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የእግር ካኳስ አፍቃሪዎች፡ በጀርመን የሚኖሩ ብዙዎቹ ኢጣልያውያንም በርሊን አደባባይ በተዘጋጀ ትላልቅ ቴሌቪዤን ፣ እንዲሁም፡ በየቡና በየምግብ ቤቶች በህብረት ይመለከታሉ።

አርያም ተክሌ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic