የጀርመን እና የአፍሪቃ ግንኙነት | አፍሪቃ | DW | 23.02.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የጀርመን እና የአፍሪቃ ግንኙነት

የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በምስራቅ አፍሪቃ ለአራት ቀናት ያደረጉትን ጉብኝት አጠናቀቁ። ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ጀርመናውያን ስለ አፍሪቃ ያላቸው አመለካከት መለወጥ አለበት ሲሉ ተናግረዋል።

የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር በአፍሪቃ ያደረጉትን የአራት ቀናት ጉብኝት ትናንት አጠናቀቁ። ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኬንያ እና ሩዋንዳ የጀርመንን ትኩረት እንደሚያገኙ ጠቁመዋል። በዩክሬን ፍጥጫ እና የግሪክ ቀውስ መካከል ወደ ምስራቅ አፍሪቃ ሃገራት ያቀኑት ሽታይንማየር ጀርመናውያን ስለ አፍሪቃ ያላቸውን አመለካከት መቀየር እንደሚኖርባቸው ተናግረዋል።

«አፍሪቃን በአዲስ መንገድ መመልከት አለብን። ለጀርመናውያን አፍሪቃ አሁንም የቀውስ እና የግጭት ምድር ተደርጋ ትወሰዳለች። አዎ ቀውስ እና ግጭት አለ። ይህ ግን መላ አፍሪቃን የሚወክል አይደለም። ለብሄራዊ ጥቅማችን ስንል ትኩረታችንን የሳቡ የተረጋጉ ሃገራት አሉ።»

ሽታይንማየር ይህን ያሉት ስለ ሩዋንዳ ነበር።ሩዋንዳ ከጎረቤት ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ጋር ያላት ግንኙነት ጤና ቢያጣም ዴሞክራሲያዊ መንግስት መመስረት አልቻለችም ተብላ ብትታማም ለሽታይንማየር አሁን ያላት መረጋጋት ይበል የሚያስብል ነው። ሽታይን ማየር በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ቆይታቸው በእሳተ ጎሞራ ፍሳሽ ከጥቅም ውጪ ከሆነው የጎማ አውሮፕላን ማረፊያ በከፊል በጀርመን የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት እገዛ የተገነባውን መርቀው ከፍተዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ አማጺያን የገቢ ምንጭ ናቸው ላሉት ህገ-ወጥ የማዕድናት ንግድ መፍትሄ ለማበጀት የቁጥጥር መንገድ ሊበጅ እንደሚገባ ጠቁመዋል።በህገ-ወጥ መንገድ የጎረቤት ሃገራትን ድንበር ተሻግረው ለአለም አቀፍ ገበያ የሚቀርቡትን ማዕድናት ምንጭ የሚጠቁም የምርምር ማዕከል በቀጠናው ለማቋቋም በሃኖቨር የሚገኘው የጀርመን የመሬት ሳይንስ እና የተፈጥሮ ማዕድናት ማዕከል እቅድ ይዟል።

ሽታይንማየር በሩዋንዳ፤ኬንያ እና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ጉብኝታቸው ጀርመን በቀጠናው የምታፈሰውን መዋዕለ ንዋይ እንድታሳድግ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል ተብሏል። ከአውሮጳ ሃገራት ታላቋ ብሪታንያ፤ ፈረንሳይ እና ቤልጅየም በአህጉሪቱ ከፍ ያለ ተጽዕኖ አላቸው ያሉት የሩዋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሉዊዝ ሙሺኪዋቦ «ጀርመን ከወዴት አለች? ጀርመን በዚህ አህጉር እና በቀጣናው ከፍ ያለ ተሳትፎ እንዲኖራት እንሻለን።»ሲሉ ጀርመን በአፍሪቃ ያላትን ተሳትፎ እንድታሳድግ ጠይቀዋል።

የሩዋንዳዋ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሉዊዝ ሙሺኪዋቦ በጀርመን በዓመት 100 ሚሊዩን ዩሮ ድጋፍ የሚደረግለትን በምሕፃሩ«MONUSCO»ተብሎ የሚጠራው በዴሞክራቲክኮንጎየተሰማራውየተ.መ.ድ. ተልዕኮ ሃገራቸው ደስተኛ አለመሆኗን ተናግረዋል። በኮንጎ የሚንቀሳቀሱት የሩዋንዳ ሁቱ አማጽያን በድንበር አካባቢዎች እየተዘዋወሩ የጎሳ ግጭት ለመጫር ይሞክራሉ ያሉት ሉዊዝ ሙሺኪዋቦ የተልዕኮው ሃላፊ ማርቲን ኮብለር አማጽያኑን ማጥፋት አልቻሉም ሲሉ ወቅሰዋል።

ሽታይንማየር በጉብኝታቸው መጨረሻ የረገጧት ኬንያ በውስጣዊ ፖለቲካዋ እና የአሸባብ ታጣቂ ቡድን ተደጋጋሚ ጥቃት መረጋጋት ቢሳናትም በምስቅራቅ አፍሪቃ ማህበረሰብ (East African Community (EAC) በኩል የጎላ ሚና መጫወት እንደምትችል ተናግረዋል።

«የተመለከትኳቸው ነገሮች ካላታለሉኝ በቀር ምስራቅ አፍሪቃ ወደ ተረጋጋ የፖቲካ ቀጠና እያደገ ነው። ይህ ደግሞ አንዱ ከሌላው ጋር በመገናኘት ወደ ፖለቲካዊ መረጋጋት ያድጋል።»

እሸቴ በቀለ

ሒሩት መለሰ

Audios and videos on the topic