የጀርመን እስራኤል ግንኙነት | ዓለም | DW | 16.02.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የጀርመን እስራኤል ግንኙነት

የእስራኤል ጠ/ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ሀገራቸዉን ሲያምሰዉ በከረመዉ የፍልስጤም አይሁድ ግጭት ምክንያት ቢዘገዩም ከጀርመን ባለስልጣናት ጋር ለመምከር ወደበርሊን ዛሬ መጥተዋል። የእስራኤል ካቢኔ ወደበርሊን ብቅ ብሎ በሁለቱ ሃገራት የፀጥታም ሆነ የኤኮኖሚ ትብብር መጠናከር ላይ እንዲመክር በተደጋጋሚ ሲጋበዝ ከርሟል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:47
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:47 ደቂቃ

ጀርመን እና እስራኤል

በዚህ የሁለቱ ሃገራት ባለስልጣናት ስብሰባም ሌሎች ጉዳዮችን አክሎ በተለይ የሶርያ ግጭት በሚያስከትለዉ ተፅዕኖ እንዲሁም ከኢራን ጋር በተደረሰዉ ስምምነት ላይ እንደሚያተኩር ይጠበቃል።
ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ወዲህ እስራኤል እና ጀርመን ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት ከመሠረቱ 50ኛ ዓመታቸዉን ባለፈዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2015 ላይ አስበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከፌደራል ጀርመን ባለስልጣናት ጋር ለመነጋገር ዋና ዋና ሚኒስትሮቻቸዉን አስከትለዉ በርሊን ተገኝተዋል። ኔታንያሁ ከመራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ጋር በሚያደርጉት ዉይይትም የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት ተጠናክሮ የሚቀጥልባቸዉ ነጥቦች ላይ እንደሚያተኩሩ ተገልጿል። ከአንድ ወር በፊት እስራኤል ከጀርመን የገዛቻቸዉ ስድስት ባህር ጠላቂ የጦር መርከብ ሜዲትራኒያን ባህርን ተንተርሶ በሚገኘዉ ሃይፋ ወደብ ደርሰዋል። የጦር መርከቦቹ የአቶም ጦር መሣሪያን መከላከል እንዲችሉ ሆነዉ ነዉ የተገነቡት። በዚህም እስራኤል ከጠላት የሚላክባትን ጥቃት መከላከል ትችላለች። የእስራኤል መንግሥት የኢራን የአቶም መርሃግብር እጅግ ስጋት ፈጥሮበታል። በደቡብ ምዕራብ ስዊትዘርላንድ በምትገኘዉ ሎዛን ከተማ የተካሄደዉ ጀርመን የተሳተፈችበት የአቶም መርሃግብር ስምምነት ለእስራኤል በቂ ዋስትና የሰጣት አይመስልም። ይህን አስመልክቶም ኔታንያሁ ሜርክል ስጋታቸዉን እንደሚረዱ ነዉ የተናገሩት።


«ሎዛን ላይ ከቀረበዉ የስምምነት ዉል የተሻለ ቢኖር የሚል አስተያየት አለን። ይህም ለጋራ የወደፊት እጣ ፈንታችንም ሆነ ደህንነታችን ጠቃሚ ነዉ ብዬ አምናለሁ። ከመራሂተ መንግሥት ሜርክል ጋር የመነጋገር እድሉን ባገኘሁ ቁጥር እነዚህን ከባድ ተግዳሮቶች በሚመለከት ባላቸዉ ግንዛቤ እደነቃለሁ።»
እንዲያም ሆኖ በእስራኤል እና ጀርመን ባለስልጣናት መካከል ለስድስተኛ ጊዜ የሚካሄደዉ የግንኙነት ትብብርን ለማጠናከር ያቀደዉ የዉይይት መድረክ ፍልስጤማዉያን በእስራኤሎች ላይ በስለት የሚያደርሱት ጥቃት ጥቁር ጥላዉን አጥልቶበታል። በሁለት ወገኖች መካከል የቀጠለዉ ግጭት በአካባቢዉ ሰላም ለማስፈን የሚደረገዉን ዓለም አቀፍ ጥረትና ተስፋ ዋጋ እንዳያሳጣ ተፈርቷል። ከእስራኤል ባለስልጣናት የጀርመን ጉብኝት ቀደም ብለዉም የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር በየቀኑ በሚባል ደረጃ ፍልስጤማዉያን በየጎዳናዉ እስራኤላዉያን ላይ በስለት የሚያደርሱትን ጥቃት «አስፀያፊ ሽብር» በማለት አዉግዘዋል። በፍልስጤማዉያን የስለት ጥቃት እስካሁን የ27 እስራኤላዉያን ህይወት ጠፍቷል። የጀርመኑ ዕለታዊ ጋዜጣ ቢልድ እንደዘገበዉም ጀርመን በእስራኤል እና ፍልስጤም መካከል ሰላም ለማስፈን የሁለት መንግሥታት መፍትሄ ተስፋ እንዲኖረዉ እዉነተኛ ድርድር መካሄድ አለበት የሚል ጠንካራ አቋም ይዛለች።

U-Boot Dolphin Klasse / Israel / Deutschland *** Overlay-fähig ***

ባህር ጠላቂ መርከቦች በሐይፋ ወደብ


የእስራኤል መንግሥት በተለይ በወታደራዊ ረገድ ከጀርመን ጋር የሚያደርገዉ ትብብር በመተማመን ላይ የተመሠረተ መሆኑን ያዉቃል። ለአምስት አስርት ዓመታት የዘለቀዉ የጀርመን እስራኤል ግንኙነት ጠንካራ ቢባልም በርሊን በእስራኤል የአይሁድ ሰፈራ መርሃግብር ላይ የምትሰነዝረዉ ትችት ግን እንደየፖለቲካ ትንኮሳ ነዉ ቴልአቪቭ ላይ የሚታየዉ። የእስራኤል መንግሥት እንደዉም አንጌላ ሜርክል በአዉሮጳ ኅብረት መድረክ ላይ ይህን የሀገራቸዉን አቋም በማንፀባረቃቸዉ እስከአሁን ድረስ ቅር አሰኝቶታል። ይህንንም የእስራኤል የፍትህ ሚኒስትር አየልት ሻኪድ ባለፈዉ ታህሳስ ወር በርሊን ላይ ከጀርመኑ አቻቸዉ ሃይኮ ማስ ጋር በተነጋገሩበት ወቅት ሳይገልፅ አላለፉም።
«እንዲህ ያለዉን ለእስራኤል ተቃዋሚዎች አንድ ርምጃ እንዲወስዱ የሚረዳ ከአዉሮጳ ኅብረት የሚሰነዘር ትችትን በጣም በትኩረት እንደምንመለከተዉ ለወዳጄ በሚገባ አስረድቻለሁ። እናም የፍትህ ሚኒስትሩን ቢያንስ ጀርመን ዉስጥ እንኳ ይህን መሰሉን ትችት ከመስጠት መታቀብ እንዲቻል ተማፅኛቸዋለሁ።»
ምንም እንኳ እንዲህ ያሉ አንዳንድ አለመጣጣሞች በሁለቱ ሃገራት መካከል ቢታዩም ለእስራኤል አዉሮጳ ዉስጥ ጀርመን ጠቃሚ ተጓዳኝ ናት። በተለይም ብሔራዊ ወግ አጥባቂዉ ኔታንያሁ ከዴሞክራቱ የዋይት ኃይት ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ጋር ያላቸዉ ግንኙነት በቀዘቀዘበት ወቅት ለኢየሩሳሌም የበርሊን አስፈላጊነት በጣም ከፍ ብሏል። ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ባለስልጣኖቻቸዉን አስከትለዉ በርሊን ሲደርሱ፤ በዓመታዊዉ የበርሊንአለ ፊልም ድግስ የደመቀችዉ ከተማ የፀጥታ ጥበቃ መጠናከሩ ተገልጿል።

ሴባስቲያን ኤንግልብረሽት/ ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic