የጀርመን ኤኮኖሚ፤ ምርምርና ተሃድሶ | ኤኮኖሚ | DW | 01.03.2006
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የጀርመን ኤኮኖሚ፤ ምርምርና ተሃድሶ

በሌላ አነጋገር እንበል በአምሥት ዓመት ጊዜ ውስጥ ጥሩ የንግድ ውጤት የሚጠብቅ አንድ ኩባንያ ዛሬውኑ ለአዲስ ዕድገት ተገቢውን ወጪ መድቦ በሥራ ላይ ማዋል ይኖርበታል ማለት ነው። ከሆነ በዚህ በኩል በጀርመን ያለው ዝግጁነት እስከምን ድረስ ነው? በ 60ኛና 70ኛዎቹ ዓመታት “ተዓምራዊ” የተባለ፤ አቻ ያልታየለት የተፋጠነ ዕድገት ያሣየችው ጀርመን ዛሬ በምርምርና በዘመናዊው የቴክኖሊጂ ተሃድሶ ጥረት አኳያ አሜሪካንና ጃፓንን ከመሳሰሉት ቀደምት መንግሥታት ስትነጻጸር ደከም ያለች ሆና ነው የምትገኘው። መንግሥትም ሆነ የኢንዱስትሪው ዘርፍ ጊዜውን ተከትለው ለምርምርና ተሃድሶ የሌሎቹን መሰል መንግሥታት ያህል ጠንካራ ትኩረት አልሰጡም።

በመሆኑም ባለፉት ሁለት አሠርተ-ዓመታት እያቆለቆለ ለመጣው የኤኮኖሚ ዕድገትና ለሥራ አጥነት ጠንቅ መንስዔ የሆነው ይሄው ጉትት ሂደት መሆኑን ከፖለቲከኞች እስከ ጠበብት ብዙዎች በየጊዜው መናገራቸው አልቀረም። ምርምር እርግጥ ውጤቱን ለማየት ጊዜ የሚወስድ በየማዕከሉ ማለት ላቦራቶሪ ብዙ ገንዘብ የሚፈስበት ጉዳይ ነው። ፍሬውን መልሶ ለማግኘት ትዕግሥትንና ጽናትን ይጠይቃል። እንግዲህ አዲስ ምርትን ፈጥሮ ለገበያ ለማብቃት በቅድሚያ በምርምርና የልማት ጥረት ላይ ገንዘብ ለማፍሰስ ዝግጁነት የግድ ይጠበቃል ማለት ነው።

ባለፈው ዓመት አጋማሽ ላይ በዚያው ወቅትና አሁን በያዝነው 2006 ሂደት ለምርምርና ልማት መዋዕለ-ነዋይን በሥራ ላይ በማዋሉ ዕቅድ 1.500 የሚሆኑ የአገሪቱ ኩባንያዎች መጠይቅ ተደርጎላቸው ነበር። በመጠይቁ ውጤት መሠረት የጀርመን ኩባንያዎች ወጪውን ይበልጥ ለማሳደግ እንደገና ፈቃደኛ መሆናቸውን አመልክተዋል። መለስ ብሎ ለማስታወስ ያህል ኩባንያዎቹ በ 2004 ቀደም ካለው ዓመት ሲነጻጸር አነስ ያለ ገንዘብ ለምርምርና ልማት ተግባር ሲያውሉ የ 2005 ዕቅዳቸው 47 ሚሊያርድ ኤውሮ፤ የዚህ ዓመቱ ደግሞ እንዲያውም 48 ሚሊያርድ የሚደርስ ነበር።

ወጪው ከተወሰነ ግብታ በኋላ እንደገና ማደግ ይዟል ማለት ነው። በሌላ በኩል ይሁንና ከዘጠናኛዎቹ ዓመታት አሥር በመቶ ዕድገት አንጻር ሲታይ እመርታው የኢምንትን ያህል ነው ለማለት ይቻላል። ወደፊትም ቢሆን ቀደም ያለውን ጊዜ መሰል ዕድገት ይኖራል ተብሎ አይጠበቅም። ይህ ምርምርን የሚያራምዱት ኢንዱስትሪዎች ማሕበር ምክትል ፕሬዚደንትና የታላቁ ንጥረ-ነገር ኩባንያ የ BASF ሊቀ-መንበር የዩርገን ሃምብሬሽት አመለካከትም ነው።

“በምርምርና በልማቱ አኳያ በአሁኑ ጊዜ ቀልጠፍ ያለ የአሠራር ዘዴ ላይ ደርሰናል። ለምሳሌ ያህል ዛሬ በንጥረ-ነገር ኢንዱስትሪው ዘርፍ ቀድሞ ብዙ ጊዜ ይፈጁ የነበሩ የሙከራ ተግባራትን አጣምሮና አፋጥኖ ማካሄድ ይቻላል። ሁለተኛው ሃቅ እንደቀድሞው ታላላቅ የሙከራ መሣሪያዎችን የመገልገሉ ጊዜ ማለፉ ነው። ብዙ ነገሮችን በትናንሽ መጠንና በቅልጥፍና መሥራት ከሚቻልበት ዘመን ተደርሷል።”

በዩርገን ሃምብሬሽት አባባል እንግዲህ በአጠቃላይ ዛሬ ምርምርና ልማትን ማካሄዱ ከፍተኛ ብቃት ላይ ደርሷል። ይህም ማለት ያለውን የምርምር ውጤት ደረጃ ለመጠበቅ ከአጠቃላዩ ብሄራዊ ምርት አንጻር ሲታይ ከዓመታት በፊት ከነበረው ከፍተኛ ወጪ ያነሰ ገንዘብ ይበቃል ማለት ነው።
በሌላ በኩል ዛሬ ግልጽ ሆኖ የሚታየው በዓለም ላይ ለወደፊት ዕርምጃቸው፤ ወይም ለምርምርና ተሃድሶ የበለጠ ገንዘብ የሚያወጡት በተለይ ትናንሽ አገሮች ናቸው። ለምሳሌ እሥራኤል ከአጠቃላይ ብሄራዊ ምርቷ 4.5 በመቶውን፤ ስዊድን 4-ና ፊንላንድ ደግሞ 3.5 በመቶውን በሥራ ላይ ያውላሉ። ጀርመን ዝቅተኛ በሆነ በ 2.5 ከመቶ ድርሻ ከአሜሪካና ከጃፓን ቀጥላ በሰባተኛ ቦታ ላይ ነው የምትገኘው።

ዓለምአቀፉ ንጽጽር ይህን የመሰለ ሲሆን በጀርመን ምርምርና ልማትን ለማራመድ ሁለት-ሶሥተኛ የሚሆነውን ወጪ የሚሸፍነው የምጣኔው-ሐብት ዘርፍ ነው። የዚሁ ወገን ድርሻ ያለማቋረጥ በማደግ በ 2004 ዓ.ም. 67 በመቶ ገደማ ደርሶ ታይቷል። በዚሁ መጠን እርግጥ የመንግሥት ድርሻ፤ የመሠረታዊ ምርምር ተግባራት ወጪም እያቆለቆለ ነው የመጣው። ይህ ደግሞ የኤኮኖሚውን ዘርፍ ተጠሪዎች ማሳሰቡ አልቀረም።

“ሁኔታው በዚህ መልክ ከቀጠለ በጀርመን የሣይንስ ማዕከልነት ላይ ዘላቂ ጉዳት የሚኖረው ሁኔታን ማስከተሉ የማይቀር ነው። በመሠረታዊ ምርምሮች ላይ መንግሥት በሥራ የሚያውለው ወጪ በማቆልቆሉ ሂደት መቀጠል የለበትም። ምክንያቱም ዩርገን ሃምብሬሽት እንደሚሉት በዚህ ተግባር ነው ለነገዎቹ ምርቶችና አጠቃቀማቸው መሠረት የሚጣለው።”

ጥልቅ መነሻ ምርምር ለኩባንያዎች በተግባር ላይ ያተኮረ ምርምር መሠረት ነው። በዚህ የዕውቀት መስክ በጀርመን የአገሪቱ ብቻ ሣይሆኑ የውጭ ኩባንያዎችም ገንዘብ ያወጣሉ። ከአራት አንዱ በሥራ ላይ የሚውል ኤውሮ የሚመነጨው በውጭ ይዞታ ከሚገኙ ኩባንያዎች ነው። እርግጥ አንድ የጀርመን ኩባንያ ለሌላ የውጭ ኩባንያ በሚሸጥበት ጊዜ የምርምሩ ማዕከል በአብዛኛው አገር አይለቅም። ግን ታዲያ የውጭ ምርምር ማዕከል ሆኖ ነው የሚቆጠረው።

ይሁንና ሆን ብለው በጀርመን ምርምር የሚያካሂዱ የውጭ ኩባንያዎችም አሉ። ለምሳሌ ያህል ከደቡባዊው ጀርመን ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ማዕከላት ጋር የተሻለ ትብብር ለማድረግ ሚዩኒክ ውስጥ የራሱ የምርምር ላቦራቶሪይ ያለው ጀነራል-ኤሌክትሪክ አንዱ ነው። እርግጥ በዚህ ተግባር ሁሉም መንግሥታት በሥራ ተሰማርተው አይገኙም። ለምርምር አስተዋጽኦ የሚያደርጉት የጀርመን ኢንዱስትሪዎች ማሕበር ጠቅላይ ጸሐፊ አንድሬያስ ሽሉተር እንደሚያስረዱት፤

“የውጭ ኩባንያዎች በጀርመን በሚያካሂዱት የምርምርና የልማት ተግባር በ 2003 ዓ.ም. 60 በመቶው ድርሻ የአውሮፓውያን፤ 37 በመቶ ገደማ የሚጠጋው ደግሞ የሰሜን አሜሪካ ነበር።” በሌላ በኩል የጀርመን ኩባንያዎችም በውጭ ሃገራት የምርምርና የልማት ተግባር ያራምዳሉ። ሆኖም በአጠቃላይ የውጭ ኩባንያዎች በዚህ በጀርመን ለምርምር የሚያውሉት ወጪ የጀርመን ኩባንያዎች በሌሎች አገሮች ከሚያወጡት የሚበልጥ ነው።

ታዲያ ጀርመን በተሃድሶ ማዕከልነት ክብደት ብታጣ ምክንያቱ ምርምርና ልማት ወደውጭ በመሸጋሸጉ ሣይሆን የጀርመን መንግሥትና ኩባንያዎች በአጠቃላይ ለዕውቀት በቂ ወጪ አለማድረጋቸው ነው። ይህ ደግሞ በወደፊቱ የዕድገት እሽቅድድም አገሪቱን ጨርሶ ወደኋላ እንዳያስቀር በጣሙን ያሰጋል።

ከሣሃራ በስተደቡብ በሚገኘው የአፍሪቃ ክፍል የኤኮኖሚ ዕድገት መጓተት ድህነትን ለማስወገድ የተያዘውን ዕቅድ ገቢርነት አጠያያቂ አድርጎ ባለበት በአሁኑ ወቅት ከሶሥት አሠርተ-ዓመታት የእርስበርስ ጦርነት አዘቅት የወጣችው አንጎላ የተፋጠነ ዕርምጃ መያዟና የውጭ መዋዕለ-ነዋይን እየሳበች መሆኑ ነው የሚነገረው። የአንጎላ መንግሥት አገሪቱ በዚህ በያዝነው 2006 ዓ.ም. 28 በመቶ ገደማ የሚጠጋ ዕድገት እንደሚታይ ይተነብያል። የመዋዕለ-ነዋይ ባለቤቶች በተለይም የቀድሞይቱ ቅኝ-ገዥ የፖርቱጋል ኩባንያዎችና የገንዘብ ተቋሟት በሰፊው ወደ አገሪቱ እየጎረፉ ነው።
የፖርቱጋሉ ሶሻሊስት ጠቅላይ ሚኒስትር ሆሴ ሶክራቴስ ከብራዚል ቀጥላ በዓለም ላይ ባታላቅነቷ ሁለተኛዋ የነበረችውን የአራቸውን የቀድሞ ቅኝ-ግዛት በፊታችን ሚያዚያ ወር ይጎበኛሉ። ሶክራቴስ ወደ ሉዋንዳ የሚያደርጉት ጉዞ ሥልጣን ከያዙ ከአንድ ዓመት ገደማ ወዲህ በተለያዩ አገሮች የሚያደርጉት ይፋ ጉብኝት አንድ አካል መሆኑ ነው። የጉዞ ዓላማቸውም የፖርቱጋልን መዋዕለ-ነዋይ ፖሊሲ በቀደምትነት በማራመድ አዲስ ምዕራፍ መክፈት ነው ብለውታል።

እርግጥ የፖርቱጋል የገንዘብ ተቋማት፣ የንግድና የቴክኒክ አዋቂዎች ልዑካን ከአሁኑ ወደ ደቡብ-ምዕራብ አፍሪቃይቱ አገር በመዝለቅ በዓለም ላይ ፈጣን ዕድገት እየታየባቸው ካሉት አንዱ ሆኖ የተገኘውን ገበያ እያጠኑ ነው። ከነዚሁ መካከል በሰላሣ ዓመታት የእርስበርስ ጦርነት የወደመችው አገር መልሶ-ግንባታ የሚሰጠውን ሰፊ ዕድል ለመጠቀም የተነሳሱት ዋና ዋና የግንቢያ ኩባንያዎች፤ ለምሳሌ ሶዋሬስ-ዳ-ኮስታን የመሳሰሉት ይገኙበታል።

ከዚሁ ባሻገር የአንጎላን ገበዮች ለመጋራት በተግባር የተሰማሩ በርካታ የትራንስፖርት፣ የሕትመት፣ የሲሚንቶ፣ የአውቶሞቢልና የኤሌክትሮኒክ ኩባንያዎችም አልጠፉም። የፖርቱጋል ቀደምት ባንኮችም በአንጎላ ላይ ትኩረታቸውን ካሳረፉት መካከል አንዳንዶቹ ናቸው። ታዛቢዎች የወደፊቱን ሂደት ብሩህ አድርገው ነው የሚመለከቱት። በተለይ በውጭ ሃገራት በትምሕርት ላይ የቆዩ በርካታ አንጎላውያን አሁን በየኩባንያው የአመራር ሥልጣን መያዝ በመጀመራቸውና በየመንግሥቱ ተቋማትም ሥር በመስደዳቸው የውጭ ባለሃብቶች በሌሎች የአፍሪቃ አገሮች ይታይባቸው የነበረው ፍርሃቻ እየቀነሰ በመሄድ ላይ መሆኑ ነው የሚነገረው።

ይሁንና በሰላሣ ዓመታት ጦርነት አጠቃላዩ መዋቅር ጨርሶ በወደመባት አገር ወደፊት የኤሌክትሪክ ሃይልና የውሃን እጥረት የመሳለ መሠረታዊ ችግር ሊገጥም መቻሉ መዘንጋት እንደሌለበት ማስገንዘባቸውም አልቀረም። በወቅቱ ቢቀር የወደመው የምድር ባቡር መስመር በቻይና አማካይነት መልሶ እየተገነባ መሆኑ የልማቱን ጥረት ከሉዋንዳ ባሻገር በአገር-አቀፍ ደረጃ ለማራመድ የሚያስችል ተሥፋን የሚሰጥ ነው።

በአንጎላ በአጠቃላይ መንግሥት የሚያልመውና ሌሎችም ተሥፋ የጣሉበት የተፋጠነ ዕድገት ዕውን እንዲሆን የአገሪቱ ዋነኛ የኤኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሞተር የሆኑት የአልማዝና የነዳጅ ዘይት ኢንዱስትሪዎች ዕርምጃ ወሣኝነት ይኖረዋል። አገሪቱ የከፋውን ድህነት ለማለዘብም ተፈጥሮ ያደላትን የእርሻና የአሣ ሃብት በአግባብ ማሳደግ፤ መጠቀም ይጠበቅባታል። የአንጎላ መንግሥት በዚህ ዓመት ያለመው ከፍተኛ ዕድገት የሚደረስበት ከሆነ አቻ የማይገኝለት ነው የሚሆነው።