የጀርመን ኤኮኖሚና የአዳጊው ዓለም ገበያ | ኤኮኖሚ | DW | 10.02.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የጀርመን ኤኮኖሚና የአዳጊው ዓለም ገበያ

ኤኮኖሚዋ በውጭ ንግድ ላይ ጥገኛ የሆነው ጀርመን ዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ በዚህ መስክ ካስከተለው ቀውስ በመላቀቅ የማገገም ሂደት እያደረገች ነው።

default

የአገሪቱ ፌደራል የሰንጥረዥ ቢሮ ዛሬ ባቀረበው ጊዜያዊ መረጃ መሠረት ጀርመን ባለፈው ዓመት ወደ ውጭ ከሸጠችው ምርት ወደ አገር ያስገባችው ተቀንሶ 136 ሚሊያርድ ኤውሮ ገደማ የሚጠጋ ትርፍ ለማግኘት በቅታለች። እርግጥ ይህ ቀደም ካለው ዓመት ሲነጻጸር በአርባ ሚሊያርድ ኤውሮ ያነሰ ቢሆንም የሂደቱ አገጋሚነት ግን ተሥፋን የሚያጠናክር ነው። ጀርመን በውጭ ንግዷ ለዓመታት የዓለም ሻምፒዮን ስትባል ከቆየች በኋላ ይህንኑ ቀደምት ቦታዋን በዓመቱ መግቢያ ላይ ለቻይና ማስረከቧ ይታወቃል። ለጀርመን የማገገም ሂደት የተሥፋ ምንጭ የሆነው በተለይ የውጩ ንግድ በዓመቱ መገባደጃ ባለፈው ታሕሣስ ወር 3 ከመቶ ከፍ ብሎ መገኘቱ ነው። ታዲያ አገሪቱ በውጩ ንግድ መልሳ ቀደምት ቦታዋን ለመያዝ ትችል ይሆን? ይህ ቢቀር በመጪዎቹ ሁለትና ሶሥት ዓመታት መሳካቱ ያጠራጥራል። ሆኖም ግን የውጭ ንግዱ መልሶ ማበቡ በአገዳጊው ዓለም ገበዮች ላይ መጠናከርን መጠየቁ የማይቀር ነው የሚመስለው።

ዓለምአቀፉ የፊናንስና የኤኮኖሚ ቀውስ በዓለም ንግድ ላይም ከባድ ማቆልቆል እንዲፈጠር ማድረጉ የሚታወቅ ነገር ነው። በዚህ ደግሞ ኤኮኖሚዋ በውጭ ንግድ ላይ ጥገኛ የሆነው ጀርመን ባለፉት ሁለት ዓመታት ከባድ ፈተና ላይ መውደቋ አልቀረም። ከዚህ አንጻር አሁን በቅርቡ በተሰናበተው ዓመት መገባደጃ ላይ ንግዱ የሶሥት በመቶ ዕድገት ማሣየቱ እጅግ የሚያበረታታና የወደፊቱን ተሥፋም የሚያጠናክር ነው። በነገራችን ላይ የዘርፉ ባለሙያዎች በተመሳሳይ ጊዜ የጠበቁት የ 0,7 ከመቶ ዕድገት ብቻ ነበር። ግማሹን ያህል ማለት ነው። እናም ያልተጠበቀው ዕርምጃው ብዙዎችን አስደንቋል። ጀርመን በ 2009 ዓ.ም. 803,2 ሚሊያርድ ኤውሮ የሚያወጣ ምርት ወደ ውጭ ስትልክ ወደ አገር ያስገባችው ደግሞ 667 ሚሊያርድ ኤውሮ የሚጠጋ ነበር ። በንግዱ እርግጥ ቀደም ያለውን ዓመት ያህል ባይሆንም ከ 136 ሚሊያርድ ኤውሮ የሚበልጥ ትርፍ ለማስገባት ተችሏል። እናም በአጠቃላይ የጀርመን የውጭ ንግድ በዓለምአቀፉ ቀውስ ከተደቆሰ በኋላ መልሶ የዕድገት መስመርን ይዞ ነው የሚገኘው።

ከሰባ ዓመታት ገደማ ወዲህ አቻ ያልታየለት ዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ ቀውስ በተለይም በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉትን መንግሥታት የምጣኔ-ሐብት ከበድ ባለ ሁኔታ ነው የፈተነው። በአንጻሩ ቻይናን የመሳሰሉት በተፋጠነ ዕርምጃ ላይ የሚገኙ አገሮች ችግሩን በሚያስደንቅ ሁኔታ በመቋቋም የተሻሉት ሆነው ታይተዋል። ከዚህ አንጻር የጀርመን ኤኮኖሚ በዚሁ በአዳጊው ዓለም ገበዮች ላይ መስፋፋቱ በሚቀጥሉት ዓመታት ቀጣይነት ያለው ዕርምጃን ለማስፈን ታላቅ አስተዋጽኦ የሚኖረው ነው። እርግጥ Germany Trade and Invest የተሰኘው የውጭ ንግድና የገበያ ይዞታ ጥናት ተቋም ሥራ አስኪያጅ ሚሻኤል ፋይፈር እንደሚያስገነዝቡት ጀርመን በምዕራብ አውሮፓና በአሜሪካ የቆዩ የውጭ ገበዮቿንም ችላ ማለት የለባትም።

Deutsche Wirtschaft wächstሆኖም ግን በአሕጽሮት ብሪክ በመባል የሚጠሩት በተፋጠነ ዕድገት ላይ ያሉ አራት ሃገራት ቻይና፣ ሕንድ፣ ሩሢያና ብራዚል፤ እንዲሁም ሳውዲት አረቢያንና ቱርክን የመሳሰሉት በዚህ ዓመት በተለይ ለጀርመን ኩባንያዎች የወደፊት ዕርምጃ ብዙ ዕድል የሚሰጡ ናቸው። ባለፈው 2009 ዓ.ም በነዚህ አገሮች ውስጥ የጀርመን የውጭ ንግድ ድርሻ ጨምሮ የታየው በቻይና ብቻ ነበር። ሚሻኤል ፋይፈር እንደሚሉት ከጀርመን በነዚህ ሃገራት ብዙ ተፈላጊነት ያለውም ከፍተኛው የቴክኖሎጂ ጥበብ ነው።

“ይህ በተለይ የምርት መሣሪያዎችን፣ የማሸጊያና የሕትመት መኪናዎችን፤ እንዲሁም የብረታ-ብረት ሥራ ዘርፎችን ይመለከታል። ከዚሁ ሌላ ጨርቃ-ጨርቅና ፕላስቲክ መሰል አምራች መኪናዎችን የሚሰሩ ኩባንያዎችም ተጠቃሚ የሚሆኑ ናቸው። ምክንያቱም የውጭ ንግድ ኢንዱስትሪው ዘርፍ እንደገና እየተነሣ በመሄድ ላይ የሚገኝ መሆኑ ነው”

ባለሙያው እንደሚናገሩት ለጀርመን ኩባንያዎች የሕንድም ገበያ ከቻይና ቀጥሎ ማራኪው እየሆነ ሄዷል። ምንም እንኳ ጀርመን ወደ ሕንድ የምታደርገው የውጭ ንግድ ባለፈው የቀውስ ዓመት አምሥት ከመቶ ቢቀንስም ለዘለቄታው ግን ጠንካራና አስተማማኝ እንደሚሆን ነው የሚታመነው። ይህንኑ ሃቅ ሰሞኑን በእሢያ ጉብኝታቸው ሕንድን ለአንድ ሣምንት የጎበኙት የጀርመኑ ፕሬዚደንት ሆርስት ኮህለርም በቅርብ ታዝበውታል። የጀርመን ኤኮኖሚ ዘርፍ በአገሪቱ ይበልጥ መዋዕለ-ነዋይ እንዲያፈስም አመቺ ሁኔታ መኖሩን በመግለጽ እያበረታቱ ነው።

“በወቅቱ በሕንድ ላይ ይበልጥ ባተኮረ አቅጣጫ የሚሄድ ለውጥ እየተደረገ ይመስለኛል። ምክንያቱም በአገሪቱ ሰፊ ዕድገትና ከፍተኛ የገበያ ዕድል መታየቱ፤ ከዚሁ ተያይዞም ከኛው የፖለቲካና የሕግ መሠረተ-ዓላማ ጋር አንድ የሆነ ስርዓት መኖሩ ነው። ዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ስርዓት! የጀርመን ኤኮኖሚ ዘርፍ እዚህ ትልቅ ዕድል መኖሩን የተገነዘበ ይመስለኛል። በዚህም በጣሙን ደስተኛ ነኝ”

የጀርመንና የሕንድ የንግድ ግንኙነት ብዙ ጉዳት ሳይደርስበት ተረጋግቶ ሲቀጥል ለንጽጽር ያህል 2009 ዓ.ም. በዓለምአቀፍ ደረጃ ግን በውጩ ንግድ ላይ ሃያ ከመቶ ማቆልቆል የታየበት ነበር። የሕንድና የጀርመን የንግድ ግንኙነት መሠረት እንግዲህ ከወቅቱ ይዞታው አንጻር ጠንካራ እየሆነ የሚቀጥል ነው የሚመስለው። ግዙፏ አገር ሕንድ ማራኪ እየሆነች የምትሄድበት የወደፊት አዝማሚያም ጎልቶ በመታየት ላይ ነው። አገሪቱ በሚቀጥሉት ዓመታት በተለይም ለመዋቅራዊ ግንባታ ብቻ 200 ሚሊያርድ ዶላር በሥራ ላይ ለማዋል ታቅዳለች። ከዚሁ በተጨማሪም እንደ ቻይና ሁሉ በሕንድም የተፈጥሮ ጥበቃና ቆሻሻን መልሶ የማጥራት ቴክኖሎጂ ፍላጎት እያደገ በመሄድ ላይ ነው።

“ካሉን መረጃ አሃዞችና ከተጠቀሰው የመዋቅራዊ ግንባታ መዋዕለ-ነዋይ ዕቅድ እንደምንመለከተው ሁኔታው በነዚህ አገሮች እየተለወጠ ነው። ጠንካራ ኤኮኖሚ ያላቸው፤ ማለት ባለፉት ጊዜያት ለተፈጥሮ ጥበቃ ግዴታዎች ብዙም ትኩረት የማይሰጡ አገሮች አሁን በዚህ መስክም ግልጽ የሆነ ዕርምጃ መውሰድ አለብን ማለት ይዘዋል። ይህ ብዙ የኤነርጂ ቁጠባ በሚጠበቅባቸው በቻይናና በሩሢያም ጎልቶ የሚታይ ነገር ነው”

የተፈጥሮ ጥበቃው ቴክኖሎጂ ደግሞ ለጀርመን የውጭ ንግድ ኤኮኖሚ ጠቃሚ ከሆኑት ምሶሶዎች አንዱ ነው። ለዚሁ አስፈላጊ የሆነውን ዕውቀት በማዳበሩ ረገድ የጀርመንን ያህል ገፍቶ የተራመደ መሰል አገር የለም። ከይህም በመሆኑ የጀርመን የንግድና መዋዕለ-ነዋይ ጥናት ተቋም ጥናት እንደሚያመለክተው በአገሪቱ ለመቆናጠጥ ገንዘባቸውን በሥራ ላይ የሚያውሉት የውጭ ኩባንያዎች ቁጥር እየጨመረ ሄዷል።

“የመዋዕለ-ነዋይ ባለቤቶች ወደ ጀርመን እየመጡ ጀርመንን ማዕከል በማድረግ የሚሰሩ ሲሆን፤ ከዚያም ከዚሁ በመነሣት በዓለምአቀፍ ገበዮች ላይ ያተኩራሉ። እንግዲህ ይህ የሚያሣየው ጀርመን በመስኩ ቀደምት የመሆን ዝና እንዳላት ነው። ይህ ደግሞ የጀርመን ኩባንያዎች ደብተሮች በኮንትራት እንዲሞሉ ብቻ አይደለም የሚያደርገው። ወደ ጀርመን የሚመጡት የውጭ ኩባንያዎች ከዚህ ባገኙት የቴክኖሎጂ ዕውቀት በሌሎች አገሮች መሰማራት እንዲበቁም ጭምር ነው”

ሚሻኤል ፋይፈር አክለው እንደሚያስረዱት በውጭ ንግድ ላይ ላተኮሩት የጀርመን ኩባንያዎች ሩሢያና ብራዚልም ይበልጥ ማራኪ የወደፊት ገበዮች እየሆኑ በመሄድ ላይ ናቸው። ሩሢያ በያዘችው ቁርጠኛ የዘመናዊ ዕድገት ዕቅድ ከጀርመን ኩባንያዎች በተለይም የምርት መኪናዎችና ፋብሪካዎችን በጣሙን ትፈልጋለች። በኤኮኖሚዋ በውጭ ንግድ ላይ ብዙም ጥገና ያልሆነችው ብራዚልም ቢሆን ዓለምአቀፉን ቀውስ ያለ ብዙ ድቀት ስትቋቋም በ 2014 እና 2016 ለዓለም እግር ኳስ ዋንጫና ለኦሎምፒክ ጨዋታ መስተንግዶ በምታደርገው ዝግጅት በተለይም በግንቢያው ዘርፍ ሰፊ ገበያ ከፋች ናት። ሳውዲት አረቢያም በነዳጅ ዘይት ላይ ያላትን ጥገኝነት ለመቀነስ በኢንዱስትሪ ልማት ላይ በሚሊያርድ የሚቆጠር ገንዘብ ማፍሰሷን ቀጥላለች።

ጥናቱ አያይዞ እንዳመለከተው ለጀርመን የምርት መኪና አውጭ ኩባንያዎች ወደፊት በቱርክ የሚኖረው ዕድልም እንዲሁ ያማረ ነው። የቱርክና የጀርመን የንግድ ግንኙነት ባለፉት ዓመታት የተረጋጋ ገጽታ ሲታይበት የአገሪቱ የኤኮኖሚ ዕድገት ዘንድሮ 3,5 ከመቶ እንደሚደርስ ይጠበቃል። እንደ ሚሻኤል ፋይፈር ለጀርመን ኢንዱስትሪዎች ከዚህ ባሻገር በጠቅላላው የአፍሪቃና መካከለኛ ምሥራቅ አካባቢም ጥሩ ዕድል የሚታይበት ነው። ግብጽ የአውቶሞቢል ኢንዱስትሪ ዘርፋን ለማጠናከር ተነስታለች። በሊቢያ ደግሞ አገሪቱ ከጀርመን የምታስገባው ምርት በእጥፍ ነው የጨመረው።

“ለጀርመን ኩባንያዎች ሰሜናዊው አፍሪቃ እጅግ ጠቃሚ ነው። የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር በቅርቡ በሚካሄድባት በደቡብ አፍሪቃም እንዲሁ በተግባር ተሰማርተናል። አገሪቱ በዚህ ዝግጅት አራት ዓመት ቀደም ሲል ጀርመን ውስጥ የታየውን መሰል ግሩም መንፈስ ለመፍጠር ከቻለች ይሄው የጀርመን ኩባንያዎች እንደገና ወደ አፍሪቃ ጠንከር አድርገው እንዲሄዱ አንቀሳቃሽ ሊሆን የሚችል ነው”

በጥቅሉ እንግዲህ የጀርመን የውጭ ንግድ በያዝነውና በመጪዎቹ ዓመታት እየተጠናከረ እንደሚሄድ ነው የሚጠበቀው። እርግጥ በሌላ በኩል በዓለም ንግድ ላይም ብርቱ ተጽዕኖ ያሳደረው ዓለምአቀፍ የኤኮኖሚ ቀውስ በወቅቱ በያዘው የማገገም ሂደት ጸንቶ መቀጠል መቻሉን ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ሆኖ ማናገሩ ያዳግታል።

MM/DW

SL