የጀርመን -አፍሪቃ የኃይል ምንጮች ገበያ | ኤኮኖሚ | DW | 23.04.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኤኮኖሚ

የጀርመን -አፍሪቃ የኃይል ምንጮች ገበያ

ጀርመን በተለይ የኃይል አቅርቦትን በተመለከተ ከአፍሪቃ ጋር ከፍተኛ የኢኮኖሚ ትስስር አላት።

ባለፉት ዓመታት የአፍሪቃ የኃይል ምንጭ ዘርፍ ከፍተኛ ስኬቶች አስመዝግቧል። ይሁንና እንደ የጀርመን የኢኮኖሚ እና ልማት ትብብር ሚኒስቴር ድረ ገፅ ከሆነ ከሰሀራ በስተደቡብ የሚገኙ 590 ሚሊዮን ሰዎች አሁንም ምንም አይነት የኤሌክትሪክ መብራት አያገኙም። ፀሐይዋ ስትጠልቅ አካባቢው በሙሉ በጭለማ ይዋጣል። ይህ ችግር ኮረንቲ ባልተቀጠለባቸው አካባቢዎች ብቻ ሳይሆን ያለው በከተሞችም ቢሆን በየጊዜው «መብራት ጠፋ» የማይል የለም። አሁንም ድረስ ከሰሀራ በስተ ደቡብ ባሉት አብዛኞቹ ሃገራት 80 ከመቶ የሚሆነው ሕዝብ ምግቡን የሚያበስለው በእንጨት እና በከሰል ነው።

የሕዝቡ ቁጥር በየጊዜው በሁለት በመቶ መጨመሩ እና ኢኮኖሚዉም 7 ከመቶ እድገት ማስመዝገቡ የአፍሪቃ የኃይል ፍላጎት እንዲጨምር ምክንያት እንደሆነ ነዉ የሚነገረዉ። እንዲያም ሆኖ ካለዉ ፍላጎት አኳያ ሲታይ የሚዘረጉት የኤሌክትሪክ መስመሮች እና የሚገነቡት የኃይል ማመንጫዎች ተመጣጣኝ ሊሆኑ አልቻሉም። አፍሪቃ ለህዝቧ በቂ የኤሌክትሪክ ኃይል ማቅረብ እንድትችል የአፍሪቃ ሃገራት ከአፍሪቃ ኅብረት ጋር በመሆን የኃይል ምንጮች መሠረተ ልማቱን በማስፋፋቱ ረገድ አብረው ይሠራሉ። በዚህም ጀርመን ትልቁን ሚና ትጫወታለች። የጀርመን የኢኮኖሚ እና ልማት ትብብር ሚኒስቴር ከሰሀራ በስተ ደቡብ ከሚገኙ 18 የአፍሪቃ ሃገራት ጋር በመሥራት ላይ ይገኛል። ባለፈው ሳምንት በጀርመኗ ሐምቡርግ ከተማ በተካሄደው 8ኛው የጀርመን -አፍሪቃ የኃይል ፍላጎትና አቅርቦት መድረክ ላይም ጀርመን ከኃይል ምንጭ ጋር በተያያዘ አፍሪቃ ውስጥ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ የምትችልባቸው አማራጮች ተነስተዋል። ስለ ኃይል አማራጮች ሲወራ ደግሞ ያለፉትንም መለስ ብሎ መቃኘት ግድ ይላል፤ በፀሀይ ከታደሉ በረሃማ ቦታዎች ታዳሽ ኃይልን ለማመንጨት የዴዘርቴክ ድርጅትን ሀሳብ መጥቀስ ይቻላል። ድርጅቱ ከዓመታት በፊት ቢመሠረትም ብዙ ስኬት አላሳየም፤ ይልቁንስ ቻይናውያን እዚህ ላይ መውዋለ ንዋይ ለማፍሰስ ልቀዉ ተገልኝተዋል። ዕቅዱ እውን ያልሆነበት ምክንያት ምን ይሆን? «የጀርመን በደቡባዊ አፍሪቃ ሃገራት የኢኮኖሚ ተሳትፎ» በምህፃሩ ሳፍሪ ሥራ አስኪያጅ - ለ አንድሪያስ ቬንዥል ከዶይቸ ቬለ የቀረበ ጥያቄ ነው።

«ከሩቅ ሆኖ ይህ ነው ለማለት ይከብዳል። ይሁንና እስካሁን በሚደረጉት የጀርመን ጥረቶች ከፖለቲካዉ መዲና በርሊን ለአፍሪቃ በቂ ድጋፍ እንደሌለ አስተውለናል። ለዚህ በተለይ በፕሮጀክቶች አካባቢ በርካታ ምሳሌዎች አሉ። ዴዘርቴክ አንዱ ነዉ። ምንም እንኳን ዴዘርቴክ በጀርመን መንግሥት መልካም አቀባበል ቢደረግለትም ፤ ፖለቲካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ ግን አላገኘም። ይህ ሲሆን ደግሞ ፖለቲካዊ ጫና በሚታይባቸው የአፍሪቃ አካባቢዎች ለምሳሌ አሁን በሰሜን አፍሪቃ ፕሮጀክቶቹ በአደባባይ ተግባራዊ እንደማይሆኑ ግልፅ ነው። እናም ፖለቲካዊ ድጋፍ ከጎደለ ምንም ማድረግ አይችሉም።»

ጀርመን ከአፍሪቃ ጋ በሁለትዮሽ የምትገናኝባቸዉ መድረኮች አሏት። በበርሊንም አሁን አሁን ስለአፍሪቃ ፖለቲካ ብዙ ይወራል። የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይን ማየር በቅርብ ነው ከአፍሪቃ ጉዟቸው የተመለሱት። ከዚህ በመነሳት ቬንዥል የጀርመን ከአፍሪቃ ጋ አብሮ የመሥራትን ሁኔታ እንዴት ይመዝኑት ይሆን?

«ከሁሉ አስቀድሞ አፍሪቃ የፌደራላዊት ጀርመን አጀንዳ ሆና ብትቆይ ደስተኛ ነን። እንደሚመስለኝ ከሶስት ዓመታት በፊት መሠረት የተጣለዉ የአፍሪቃ ፅንሰ ሀሳብ እያደገ መሄዱ ጥሩ ይመስለኛል። ወደፊትም ቀጥሎ ተግባራዊ መሆን ይገባዋል። ትንሽ የሚያሳስበን ግን ተግባራዊ የሚሆንበት ፍጥነት እና ስፋት ነው። ምክንያቱም አሁን ያለው ነገር በንቃት የመንቀሳቀስ ነገር የሚጎድለዉ ይመስላል። »እሳቸዉ እንደሚሉት ከሆነም ይህ የሆነበት ዋናዉ ምክንያት በቶሎ ውጤቱን ለማየት ከመቸኮል የመጣ ነው።

«አፍሪቃ ዉስጥ በእርዳታም ሆነ በዘላቂነት አብሮ የመሥራት ጉድኝት በተለይም በኢኮኖሚያዊዉ ረገድ፤ ውጤቱን ብቻ ሳይሆን ሂደቱንም ጨምሮ ያገናዘበ መሆን ይኖርበታል። እንደዚህ አይነቱ አስተሳሰብ በመጠኑ እንደሚጎድል አያለሁ። ችግሩ የኤኮኖሚዉ ጉዳይ መቅደሙ ይመስለኛል። ለኛ ወሳኙ ነገር የጀርመን ኩባንያዎች እንዴት መካፈል ይችላሉ፣ በአህጉሪቱ ዉስጥ ባለዉ የፖለቲካ ማዕቀፍ እንዴት መንቀሳቀስ እንችላለን የሚለው ነው። ይህ ደግሞ ከአፍሪቃዊ አጋሮቻች ጋር በጋራ ቢታይ ይመረጣል።»

Solarenergie in der Wüste Flash-Galerie

ምንም እንኳን ቬንዝል የአፍሪቃ የኃይል ምንጮች ፍላጎትና ገበያ፤ ከጀርመን አልፎ ሌሎችንም ሊያስትፍ ይችላል የሚል እምነት ቢኖራቸዉም የአውሮጳ ኅብረት ይህን ተጠቅሟል ብለዉ አይገምቱም። እንደዉም በዚህ ረገድ የኅብረቱና የአፍሪቃ ግንኙነት ከጀርመን ጋር እንዳለው ጠንካራ ነው ብለው አያምኑም።

« በአሁኑ ሰዓት የማየው በበርካታ ጉዳዮች ላይ ያተኮረዉ የአውሮፓ- አፍሪቃ ግንኙነት በአግባቡ ባልተያዙ የኢኮኖሚ ስምምነቶች ላይ የተመረኮዙ ሆነው ነው። ይህም የአውሮጳ ኅብረት እና አፍሪቃ ግንኙነት ለም ባልሆነ መሬት ላይ የበቀለ ነው ብዬ እንዳስብ አድርጎኛል። የጀርመን ኢኮኖሚ ግንኙነት ግን በአንፃሩ በአፍሪቃ ትልቅ ደረጃ የሚሰጠዉ ነው። ብዙ አቅም አለው። ምሳሌ ጠርቻለሁ፣ ታዳሽ ሀይል እና የኃይል አጠቃቀምን መርሳት የለብንም። ይሄንንም የጀርመን መንግሥት ሊያተኩርበት የሚችል ይመስለኛል። ሁል ጊዜም ቢሆን ከዘርፈ ብዙዉ ይልቅ የሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ ይበልጥ ማተኮር እንደሚኖርበትም ያመላክታል። »

በ8ኛው የጀርመን -አፍሪቃ የኃይል ፍላጎትና አቃቦት መድረክ ከተለያዩ የአፍሪቃ ሃገራት ተሳታፊዎች መካከል፤ ቴምባኒ ቡኩላ ፤ ከደቡብ አፍሪቃ ብሔራዊ የኃይል አስተዳደር አንዱ ናቸው። በጉባኤውም ላይ ብዙ መንግስታዊ ስላልሆኑ የኃይል አመንጪ ኩባንያዎች አስረድተዋል። ትርፋማነቱ እና የገበያ እድሉ ምን ላይ ነው? ያብራራሉ።

«ከዚህ በፊት የመንግሥት የነበሩት አገልግሎት ሰጪ መሥሪያ ቤቶች የዘርፉን መሠረተ ልማት በመገንባት አንቀሳቅሰዉታል። አሁን የደረስንበት ነገር ቢኖር እነዚህ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ባለዉ የአሁን ዋጋ ኃይል ማመንጫ የሚገነቡበት አቅም እንደሌላቸው ነው። ይህ ነው የኃይል መሠረተ ልማቱን በመገንባት እንዲረዱን ሌላ ገንዘብና አቅም ያላቸዉ ሰዎችን በአማራጭነት እንድንፈልግ ያደረገን።»

ከዚህ ቀደምም ታዳሽ የኃይል ምንጮችን ተጠቅሞ ኤሌክትሪክ ማምረቱ ብቻ ሳይሆን ለተጠቃሚዎችም የሚቀርበዉ በዉድ ዋጋ እንደነበር ያመለከቱት ቡኩላ፤ አሁን ቅናሽ መኖሩን ነዉ የገለፁት። ለምሳሌ ከነፋስ የሚመነጨዉ የአንድ ኪሎ ዋት ዋጋ ከ60 የደቡብ አፍሪቃ ሳንቲም አንስቶ እስከ 66 ሳንቲም ይደርሳል። ይህ ብቻ አይደለም። ከፀሀይ ብርሃን እና ከባዮ ማስ የሚገኘው ኃይል ዋጋ ደግሞ ከአንድ ራንድ ከፍ እንደሚል ቡክላ ያብራራሉ። ጀርመን ዉስጥ ከኒኩሌር የኤክትሪክ ኃይል ማመንጨቱ እንዲቀር በርካታ ድርድሮች ተካሂደዋል። አብዛኛው ሰውም ይህን አይደግፍም። ጀርመን ከዚህ በምትላቀቅበት ሰዓት እንደ ደቡብ አፍሪቃ ያሉ ሃገራት ዘላቂ የኃይል ምንጫቸው መሆኑ ይታያል።

«ሁሉንም የኃይል ምንጮች ያካተተዉ እቅዳችን እንደሚያመላክተው በሚቀጥሉት 20 ዓመታት ውስጥ ተጨማሪ 5000 ሜጋ ዋት ከከሰል እና 9600 ሜጋ ዋት ከኒኩሌር ምንጭ እንደምናገኝ ነው። የተቀረው ጋዝ እና ታዳሽ ኃይል ነው የሚሆነው። »

ቡኩላ እንደሚሉት በሚቀጥሉት 2 አስርተ ዓመታት ኒኩሌር እና ከሰል ከደቡብ አፍሪቃ የኃይል ምንጭነት ቢወጡ የኃይል አቅርቦቱን ይበልጥ ይቀንሰዋል። ታዳሽ ኃይል ምንጭን በተመለከተ ደቡብ አፍሪቃ የምትገኝበትን አስመልክተዉ ደግሞ እንዲህ ይላሉ?

« ደቡብ አፍሪቃ እና አንዳንድ የጎረቤት ሃገራትን የተመለከትን እንደሆን ከዜሮ እና ከአምስት ሜጋ ዋት በ2010 እና2011 ተነስተን ነዉ አሁን በ2014 7000 ሜጋ ዋት ማምረት የቻልነዉ። ስለዚህ ይህ እንቅስቃሴ አለ። »

የጀርመን-አፍሪቃ የኃይል ምንጮች ገበያ ላይ ያተኮረው የዛሬውን የከኢኮኖሚው ዓለም ዝግጅት ከድምፅ ዘገባው ያገኙታል።

ልደት አበበ

ሸዋዬ ለገሰ