የጀርመን አጠቃላይ ምርጫ ቅድመ-ውጤት ይፋ ኾነ | ኢትዮጵያ | DW | 24.09.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የጀርመን አጠቃላይ ምርጫ ቅድመ-ውጤት ይፋ ኾነ

በጀርመን አጠቃላይ ምርጫ የመጀመሪያ ዙር ውጤት መሠረት፦እንደተጠበቀው መጤ ጠሉ አማራጭ ለጀርመን (AFD) ፓርቲ ምክር ቤት መግባት የሚያስችለውን 13,4 በመቶ ድምጽ ማግኘት መቻሉ ተገለጠ። የክርስቲያን ዲሞክራቲክ ኅብረትና (CDU) የባየርኑ ክርስቲያን ሶሻሊስት ኅብረት (CSU) ጥምረት በ33,1 ከመቶ በማግኘት ይቀድማል።

ሶሻል ዲሞክራቶቹ (SPD) 20,4 ከመቶ ሲያገኝ፤ የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ 9.3 የነጻ ዲሞክራቶቹ ፓርቲ (FDP) 10.4 ግራዎቹ 8.9 እንዲሁም ሌሎች 4.7 ከመቶ አግኝተዋል። 42 ፓርቲዎች በምርጫው ተወዳድረዋል።

ጀርመን ዛሬ ምርጫ እያካሄደች ነው። በሀገሬው አቆጣጠር ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ጀምሮ 88, 000 የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች ክፍት ሆነው መራጮችን እያስተናገዱ ይገኛሉ። በጀርመን አጠቃላይ ምርጫ እስከ እኩለ-ቀን ድረስ ድምጽ ለመስጠት የወጣው መራጭ ቁጥር ከአራት ዓመት በፊት ከነበረው በመጠኑ ያነሰ ነው ተባለ።  

በጀርመን አጠቃላይ ምርጫ ድምጽ ለመስጠት የሚወጣው ሰው ከአራት ዓመት በፊት ከነበረው የተሻለ ይኾናል ተብሎ  ቢገመትም፤ እስከ እኩለ-ቀን ድረስ ድምጽ ለመስጠት የወጣው መራጭ ቁጥር ግን ከአራት ዓመት በፊት ከነበረው በመጠኑ ያነሰ መኾኑ ተገልጧል። የጀርመን ፕሬዝዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር በ“ቢልድ” ጋዜጣ የዛሬ እትም ላይ ባወጡት ፅሁፍ ጀርመናውያን በምርጫው በነቂስ እንዲሳተፉ ጠይቀዋል። “እያንዳንዱ ድምፅ ዋጋ አለው። የእርስዎም ድምፅ ዋጋ አለው” ሲሉ ዜጎች ጀርመናውያን ግዴታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል። “ድምፅ የማይሰጡ ሰዎች ሌሎች የሀገራችንን መጻኢ እንዲወስኑ ፈቀዱላቸው ማለት ነው” ብለዋል። 

ትንበያዎች እንደሚያሳዩት በዛሬው የጀርመን አጠቃላይ ምርጫ ለመሳተፍ ብቁ ከሆኑ 61.5 ሚሊዮን ጀርመናውያን ውስጥ 71.5 በመቶው በዛሬው ምርጫ ድምፅ ለመስጠት ይወጣሉ። 42 ፓርቲዎች እና 4‚828 ዕጩዎች ይሳተፋሉ፡፡ በርካታ ፓርቲዎች ለውድድር ቢቀርቡም ትኩረቱ ያለው ግን በሶስት ፓርቲዎች ላይ ነው፡፡ በምክር ቤት አብላጫ መቀመጫ ያለው የክርስቲያን ዲሞክራት ኀብረት ፓርቲ (CDU) እና ተቃናቃኙ የጥምር መንግሥት አባል የሶሻል ዲሞክራት ፓርቲ (SPD) ከፍተኛ ድምጽ ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ መጤ ጠሉ አማራጭ ለጀርመን የተሰኘው የፖለቲካ ፓርቲ (AFD) ከፍ ያለ ድጋፍ እያገኘ መምጣቱም እያነጋገረ ይገኛል፡፡

የጀርመን ሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ እጩ መራሄ መንግሥት ማርቲን ሹልስ ከባለቤታቸው ጋር በመሆን በኔዘርላንድስ ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው ቩርዝለን ከተማ ድምጻቸውን ዛሬ ረፋድ ላይ ሰጥተዋል፡፡ የአየር ሁኔታው ጥሩ መሆኑ በርካታ መራጮች ወደ ድምጽ መስጫ ጣቢያዎች እንዲመጡ አንድ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ሹልስ ተናግረዋል፡፡ 

የአንጌላ ሜርክል ዋነኛ ተፎካካሪ የሆኑት ማርቲን ሹልስ ድምጻቸውን ከሰጡ በኋላ እንደተናገሩት “በተቻለ መጠን በርካታ ሰዎች ድምጽ የመስጠት መብታቸውን ይጠቀሙበታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል፡፡ መራጮች “ለዲሞክራሲያዊ ፓርቲዎች ድምጽ በመስጠት ጀርመን ፌደራላዊ ሪፐብሊክን የዲሞክራሲ መጻኢ ያጠናክራሉ” ሲሉ ተስፋቸውን አንጸባርቀዋል፡፡ ይህ ንግግራቸው ለቀኝ አክራሪው አማራጭ ለጀርመን ፖለቲካ ፓርቲ የተሰነዘረ እንደሆነ የጀርመን ዜና አገልግሎት ዘግቧል፡፡ አማራጭ ለጀርመን ፖለቲካ ፓርቲ በዚህኛው ምርጫ ከ11 እስከ 13 በመቶ ድምጽ ያገኛል ተብሎ ተገምቷል፡፡ ፓርቲው የዛሬ አራት ዓመት በተካሄደው ምርጫ ወደ ምክር ቤት ማስገባት የሚችለውን አምስት በመቶ ድምጽ ማግኘት ተስኖት ነበር፡፡

 

በምርጫ ለመሳተፍ ብቁ ከሆኑ 61.5 ሚሊዮን ጀርመናውያን ውስጥ ሴቶች 51.5 በመቶ ይሸፍናሉ፡፡ 20 በመቶዎቹ ዕድሜያቸው 70 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ናቸው፡፡ ዕድሜያቸው ከ31 ዓመት በታች የሆኑ ወጣቶች ከመራጮቹ 15 በመቶውን ይይዛሉ፡፡ ከአጠቃላይ መራጮች ወደ 10.4 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ስደተኛ የሆኑ ወይም ቢያንስ ከወላጆቻቸው አንዱ ወደ ጀርመን በስደት የመጡ ናቸው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ድምፅ የሚሰጡ ጀርመናውያን 3 ሚሊዮን ገደማ ይሆናሉ። 

ተስፋለም ወልደየስ

ልደት አበበ

ማንተጋፍቶት ስለሺ
 

WWW links

ተዛማጅ ዘገባዎች