የጀርመን አይሮፕላን ፈረንሳይ ዉስጥ ተከሰከሰ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 25.03.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የጀርመን አይሮፕላን ፈረንሳይ ዉስጥ ተከሰከሰ

150 ሰዎችን አሳፍሮ ከስጳኝ ወደ ጀርመን ይበር የነበረ አንድ «ጀርመንዊንግስ» የተባለ አየር መስመር አይሮፕላን በደቡብ ፈረንሳይ ዉስጥ ተከሰከሰ።

«ጀርመንዊንግስ» የተባለው የጀርመናውያኑ አየር መስመር ሉፍትሀንዛ ቅርንጫፍ አየር መንገድ አይሮፕላን ዛሬ ከቀትር በፊት በደቡብ ፈረንሳይ መከስከሱን የፈረንሳይ ፖሊስ እና የበረራ ተቆጣጣሪ ባለስልጣናት ነበር ያሳወቁት።

144 መንገደኞችና፣ ሁለት የአይሮፕላኑ አብራሪዎች እና አራት ሠራተኞችን ያሳፈረው «ኤ 320 » ኤርባስ አይሮፕላን ከስጳኟ ባርሰሎና ወደ ጀርመኗ ዱስልዶርፍ ከተማ ይበር በነበረበት ጊዜ ነው በደቡባዊ የአልፕስ ተራራ በምትገኘው የባርሰሎኔት አካባቢ አደጋ ያጋጠመው። የፈረንሳይ ፕሬዚደንት ፍራንስዋ ኦሎንድ በአደጋው ተሳፋሪዎቹ በጠቅላላ መሞታቸዉን አስታውቀዋል። የጀርመን መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል በዚሁ አስደንጋጭ አደጋ የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልጸዋል።


« በዛሬው ዕለት የሚያሳስበኝ ይኸው አስደንጋጭ አደጋ በብዙ ሰዎች ላያ ያደረሰው ከፍተኛ ሀዘን ነው። በዚሁ አጋጣሚ የእኔ እና መላው የጀርመን መንግሥት ሀሳብ በዛሬው ዕለት በዚህ አደጋ ሕይወታቸውን ካጡት ጋ መሆኑን በማመልከት፣ የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን እንገልጻለን። ከሟቾቹ መካከልም ብዙ ጀርመናውያን ይገኙባቸዋል። የቤተሰቦቻቸው ሀዘንም በጣም ጥልቅ ነው። እና በዚህ ዓይነት ሁኔታ የሚያስፈልገውን ርዳታ እና ድጋፍ እንዲያገኙ የሚቻለንን ሁሉ እናደርጋለን። »


ከመንገደኞቹ መካከል 67 ጀርመናውያን ሲሆኑ፣ 45 የስጳኝ ተወላጆችም እንደነበሩ ተገልጿል። ከ67 ጀርመናዉያን መካከል 16 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች እና ሁለት መምህራን እንደሚገኙበት ታዉቋል። ተማሪዎቹ በስጳኝ በሚገኝ አንድ አጋር ትምህርት ቤት ቆይታ አድርገዉ ወደ ሃገራቸዉ እና ወደ የቤተሰቦቻቸዉ በመለስ ላይ ነበሩ።

በደቡባዊ የአልፕስ ተራራ150 ሰዎችን ይዞ የተከሰከሰዉ ይህ አዉሮፕላን የመረጃ መሰብሰብያ ሳጥን መገኘቱ ተገልፆአል። ቦታዉ ተራራማ እና በረዶአማ በመሆኑ የተሳፋሪዎችን አስክሪን ለማግኘት የሚደረገዉን ጥረት እጅግ እንዳጓተተዉ ተመልክቶአል። አዉሮፕላኑ ከተከሰከሰበት አስር ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ለፍለጋ የተዘጋጁ ሄሊኮፕተሮች የሚያርፉበትና የተሳፋሪ ቤተ-ዘመዶች የሚቆዩበት ጊዜያዊ ቦታ መዘጋጀቱን የመገናኛ ብዙሃኖች ዘግበዋል።እንደ ቅድመ የአየር ሁኔታ ተንባዮች አዉሮፕላኑ በተከሰከሰበት አካባቢ በረዶ ይጥላል በማለታቸዉ ምናልባትም የፍለጋ ሥራዉን ያጓትታል የሚል ሥጋት አሳድሮአል።

ይህን አደጋ ተከትሎ በጀርመን በርካታ ፖለቲከኞች በሃገሪቱ ታዋቂ የሆኑ ሰዎች ሐዘናቸዉን በተለያዩ የመገኛኛ ብዙሃኖች እየገለፁ ነዉ። ፔሩ ላይ ጉበኝት ላይ የነበሩት የጀርመኑ ፕሬዚዳንት ዮአሂም ጋዉክ ጥልቅ ኃዘናቸዉን አስተላልፈዋል፤ የጀመሩትንም ጉብኝት አቋርጠዉ ወደ ሃገራቸዉ እንደሚመለሱ ተመልክቶአል። መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል እስካሁን በውል ያልታወቀው የአደጋ መንሥዔ እንደሚጣራ ነዉ የገለፁት። የፈረንሳይ እና የስጳኝ መንግሥታትም ለሟቾቹ ቤተሰቦች የሀዘን መግለጫ አስተላልፈዋል።

አርያም ተክሌ

ልደት አበበ