የጀርመን አምባሳደር ስለ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 05.06.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የጀርመን አምባሳደር ስለ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ

በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ብሪታ ቫገነር ስለ ኢትዮጵያ የለውጥ ሒደት፤ ስለተራዘመው ምርጫ እንዲኹም ኮቪድ-19 የአፍሪቃ ኅብረት እና የአውሮጳ ኅብረት ላይ ስላስከተለው ተጽዕኖ ከዶይቸ ቬለ ጋር ተነጋግረዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 05:02

ቃለ መጠይቅ ከአምባሳደር ብሪታ ቫገነር ጋር

አዲስ አበባ በሚገኘው የጀርመን ኤምባሲ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ2017 ጀምሮ ብሪታ ቫገነር በጀርመን አምባሳደርነት በማገልገል ላይ ይገኛሉ። ጀርመን ከአፍሪቃ ኅብረት ጋር ላላት ግንኙነትም ኃላፊነቱ የአምባሳደሯ ነው። ሉድገር ሻዶምስኪ ከአምባሳደር ብሪታ ቫገነር ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ በቅድሚያ  ያቀረበላቸው ጥያቄ፦ ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ  ያለውን ጊዜ እንዴት ይመለከቱታል የሚል ነበር። በተለይ አምባሳደሯ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ሲጓዙ ራሳቸው ካዩት እና በዋናነት ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ የፖለቲካ መድረኩን ለመክፈት በገቡት ቃል መሠረት በፖለቲካው አውድ ከተገነዘቡት አንጻር እንዲመልሱ ተጠይቀውም ቀጣዩን ብለዋል።

«እንግዲህ ያ በእውነቱ አንዳች ሳይጠበቅ የመጣ ትልቅ ለውጥ ነበር። እናም ያ እኔን ጨምሮ ብዙ በቅርበት ተመልካቾችን በአወንታዊነት በድንገት እጅግ ያስደመመ ነበር። እኔ እዚህ በመጣኹበት አካባቢ በዓመቱ መገባደጃ በነበሩት ወራትም በቀደመው አስተዳደር የነበረውን ሰቆቃ በመጠኑ ታዝቤያለኹ። በርካታ አለመረጋጋቶች ነበሩ፤ በስተመጨረሻም  በተደጋጋሚ ኹሉም ነገር ቀጥ ብሎ ነበር። እናም ያ ያጫረው ስሜት እዚህ ለኹሉም አንዳች እፎይታ የሰጠ በደንብ ያነቃቃም ነበር። ለእኔ ከፕሮፌሽናል ዕይታ አንጻር ለየት ያለ ነበር። በሀገሪቱ የነበረው ስሜት ከፍተኛ ደስታ እና የመነቃቃት ስሜት ታይቶበታል።»

በወቅቱ የተፈጠረው ልዩ ስሜትም መልካም በኾኑ ፈጣን ርምጃዎች የታገዘ እንደነበር አምባሳደሯ አክለዋል።

በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ብሪታ ቫገነር

በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ብሪታ ቫገነር

«የነበረው ከፍተኛ ደስታ እና የመነቃቃት ስሜት በቅጽበት ነበር በሚታዩ ቀና ውጤቶች የታጀበው። በርካታ የፖለቲካ እስረኞች ወይንም በኋላ ላይ ኹሉም የፖለቲካ እስረኞች መለቀቃቸው፤ አዲስ አበባ ውስጥ ታዋቂው የማዕከላዊ እስር ቤት መዘጋቱ፤ ብዙ ያናገርኳቸው ጋዜጠኞች ‘የለም፤ ከእንግዲህ አንዳችም ስጋት የለብንም’ ማለታቸው፤ ስሜቱ እጅግ ቀና የሚባል ነበር። ግን ደግሞ እንዲያ ካለ የመጠበቅ ስሜት በመሰረቱ ኹሉንም ለማሳካት የመቻሉ  ነገር  እጅግ አጠራጣሪ  ነበር። በግዞት ላይ የነበሩ የፖለቲካ ተቃዋሚዎች ወደ ሀገር ገብተው የፖለቲካ ሒደቱ ላይ ተሳታፊ እንዲኾኑ ጥሪ መደረጉ፤ ሕግጋት፦ የሲቪል ማኅበረሰቡ ተቋማት እንደቀድሞው ገደብ ሳይኖርባቸው ይበልጥ ነጻ ኾነው እንዲንቀሳቀሱ ለማስቻል መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች ሕግ ላይ ፈጣን በሚባል መልኩ ማሻሻያ መደረጉ፤ ከዚያ አንጻር በርካታ ቀና የሚባሉ ነገሮች ነበሩ። ግን ደግሞ ከዚያ ባሻገር ብዙ የሚጠበቁ ቀና ነገሮችም ነበሩ፤ አጠቃላይ መሰረታዊ የአቅጣጫ ለውጥ እና የስርዓት ቅየራ ሊያስከትል የሚገባ እናም በስተመጨረሻ ጊዜ የሚሻ ሒደት። »

አምባሳደር ብሪታ ቫገነር፦ በሀገሪቱ የተከሰተው የኮሮና ቀውስ በርካታ የለውጥ እንቅስቃሴዎችን ከምንም በላይ ደግሞ በሕገ መንግስቱ መሰረት ቀጠሮ ተይዞለት የነበረውን ሀገር አቀፍ ምርጫ እንዲቆም ማድረጉ እና ማዛባቱ አሳዛኝ ነው ብለዋል። መንግሥት፤ የምክር ቤት አባላት እና ባለሞያዎች በሚያደርጉት ጥረትም የመንግሥትን ሥልጣን ማራዘም ሊኾን ይችል ይኾናል ብለዋል። ያም ከሕግና ከፖለቲካ አንጻር አስተማማኝ ሊኾን እንደሚገባ አሳስበዋል።

ጀርመን ምጣኔ ሐብታዊ እና ፖለቲካዊ የለውጥ ሒደቱን ለመደገፍ ፍላጎት እንዳላት ያንንም እየተገበረች መኾኑን ጠቊመዋል። በዓመቱ መጀመሪያ ላይም 340 ሚሊዮን ዩሮ አዲስ ርዳታ ለማድረግ ከጀርመን መንግሥት ይኹንታ መገኘቱን አስታውሰዋል። ለምርጫ ዝግጅት ጀርመን ከአውሮጳ ኅብረት በተጨማሪ 10 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ማድረጓን ከለውጡ ጎን መንግስታቸው መቆሙን እንደሚቀጥልበት በተደጋጋሚ መግለጹን ተናግረዋል። በሀገሪቱ ስለሚታዩ ግጭቶች የሚሰማቸውንም ብለዋል።

«የጎሳ ግጭት ወይንም ጎሳን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ ግጭት እጅግ አሳሳቢ ነው።  የኮሮና ቀውስ ለተደቀነበት መንግሥት ይኼ በእርግጥም ብርቱ ተግዳሮት ነው። ያ በተያያዥነት በምርጫው ላይ ወሳኝ ሚና የሚጫወት ነጥብ ነው። ጀርመን በእዚህ ጉዳይ የተለያዩ ጉባኤዎችን እና ውይይቶችን በማሰናዳት ለተለያዩ የፖለቲካ አካላት ድጋፍ አድርጋለች። ያ ለእኛ ይበልጥ ትኩረት የምንሰጥበት ጠቃሚ ጉዳይ ነው።»

ከዚያም ባሻገር የኢትዮጵያ ምክር ቤት አባላት ጀርመን ተጉዘው የመንግሥትን አሠራር መጎብኘታቸውን አስታውሰዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ከቻይናዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኬ ኪያንግ ጋር

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ከቻይናዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኬ ኪያንግ ጋር

በዓለም አቀፍ ፖለቲካዊ ግንኙነት ወቅት ኢትዮጵያ ድጋፍ አገኝበታለኹ ብላ ወደሚሰማት  አቅጣጫ እንደምታቀና አውሮጳ እና ጀርመን ግን እንደቀድሞው ኹሉ ወሳኝ አጋሮች ናቸው ብለዋል። በምጣኔ ሐብታዊ አጋርነት እና በኮሮና ትግል ከጎን መኾናቸውን አክለዋል። ለኮሮና ትግል ጀርመን 120 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ መፍቀዷንም ጠቁመዋል። ያ በኢትዮጵያ መንግሥት እጅግ በጥሩ ኹኔታ መታየቱን ገልጠዋል። የአውሮጳ ኅብረት እና የአፍሪቃ ኅብረት መቀራረባቸውን ይበልጥ ለማጎልበት በተነቃቊበት እና ጥረት በሚያደርጉበት ወቅት ኮሮና መከሰቱ ፍጹም የማያስደስት ነው ብለዋል። የተጀመረው ንግግር ግን በታቀደለት መሠረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመው፤ ኮሮናን በተመለከተ ከአፍሪቃ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማእከል ጋር በቅርበት እንደሚሠሩ ተናግረዋል። ሙሉ ቃለ መጠይቁን ያደረገው የዶይቸ ቬለ (DW) አማርኛው ክፍል ኃላፊ ሉድገር ሻዶምስኪ ነው።

ሉድገር ሻዶምስኪ/ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች