የጀርመን ቴክኖሎጅ ሽግግር ለኢትዮጵያ | ኢትዮጵያ | DW | 30.01.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የጀርመን ቴክኖሎጅ ሽግግር ለኢትዮጵያ

የጀርመኑ ፕሬዝዳንት ፍራንክ ዋልተር ሽታይንማየር ካለፈዉ ዕሁድ ጀምሮ በኢትዮጵያ ጉብኝት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።ከፕሬዝዳንቱ ጋር አብረዉ የተጓዙ «ሲመንስን» የመሳሰሉ  የጀርመን የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችም ኢትዮጵያ ዉስጥ ለመስራት ፈቃደኛ መሆናቸዉን ገልፀዋል።ከኢትዮጵያ መንግስት ጋርም ምክክር አድርገዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:00

«ትብብሩ ቴክኖሎጅን ለማሻሻል፣ ለማላመድና ለመቅዳት ያግዛል»


ጀርመን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በሳይንስና በቴክኖሎጅ የፈጠራ ስራዎች ቀዳሚ ስፍራ  ያላት ሀገር መሆኗን መረጃዎች ያሳያሉ።ሀገሪቱ በትምህርት፣በህክምና፤በመረጃና ግንኙነት፣በምህንድስና፣በመጓጓዣ ፣ በስነ-ህንፃ፣በስነ-ክዋክብት፣በኬሚስትሪ፣በፊዚክስ፣በስነ-ህይወት፣ በሂሳብ ወዘተ በመሳሰሉ ዘርፎች የዕለት ተዕለት ህይወትን ቀለል የሚያደርጉና የሰዉን ልጅ ኑሮን የሚያሻሽሉ ግኝቶችን በባለቤትነት አስመዝግባለች።ስለ ጀርመን የኢኮኖሚ ዕድገትና ጥንካሬ ሲወራ ሀገሪቱ በሳይንስና በቴክኖሎጅ እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች የምታስመዘግበዉ ፈጠራ እንዲሁም ፈጠራዎችን የማሻሻል ስራ የጀርባ አጥንት በመሆን እያገለገለ ይገኛል።
የሀገሪቱ ኩባንያዎች ወቅቱ የደረሰበትን ዘመናዊ የሳይንስና ቴክኖሎጅ  አሰራርን ተከትለዉ የሚያመርቷቸዉ የምርቶች ጥራትና ጥንካሬ ደግሞ «በጀርመን የተሰራ»የሚለዉን ስም በዓለም ላይ ተቀባይነት እንዲያገኝና የበለጠ ዋጋ እንዲሰጠዉ አድርጎታል። 


በሳይንስና ቴክኖሎጅዉ ዘርፍ ብዙ መጓዝ ለሚጠበቅባት ኢትዮጵያም እንደ ጀርመን ካሉ በዘርፉ ጥሩ ልምድ  ልምድ ካላቸዉ ሀገራት ጋር የምታደርገዉ ትስስር ጠቃሚ መሆኑ  ይነገራል። 
ይህን በመገንዘብ ይመስላል የኢትዮጵያ የኢኖቬሽንና የቴክኖሎጅ ሚንስቴር በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት በማድረግ ላይ ከሚገኙት የጀርመኑ ፕሬዝዳንት ፍራንክ ዋልተር ሽታየንማየር ጋር ወደ ኢትዮጵያ ከመጣና በቴክኖሎጅ ዘርፍ ከሚሰራ የልዑካን ቡድን  ጋር ያለፈዉ ሰኞ ምክክር አካሂዷል።በምክክሩም የጀርመን አነስተኛ የቴክኖሎጅ ኢንተርፕራይዞች ማህበር በኢትዮጵያ ለመስራት ፈቃደኛ መሆኑን በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጅ ሚንስቴር የሚዲያና የፕሬስ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ተስፋዬ ዓለምነዉ ገልፀዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ  በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ቴክኖሎጅን በማሻሻል በማላመድና በመቅዳት ላይ የተመሰረተ የስራ ዕድል በመፍጠር  የህብረተሰቡን ገቢ የማሳደግ ዓላማ ያለዉ፤ ወደ ሁለት ሺህ በሚጠጉ የቴክኖሎጅ ስራዎች 20 ሺህ የስራ ዕድል በመፍጠርና ሁለት ቢሊዮን ዶላር ለማግኜት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጅ ሚንስቴር አቅዷል።። ይህንን ዕቅድ ወደ ተግባር ለመቀየር  ደግሞ  የጀርመን ተሞክሮ አጋዥ በመሆኑ የኢትዮጵያ መንግስት አብሮ መስራት እንደሚፈልግ ነዉ አቶ ተስፋዬ ያስረዱት።
በዚህም የሀገሪቱ ገቢ በግብርናዉ ዘርፍ ብቻ ሳይታጠር በአገልግሎትና በዕዉቀት ዘርፉም  ሀብት እንዲመነጭ ይደረጋል ብለዋል።ለዚህ ደግሞ አጋዥ ቴክኖሎጅዎችን መጠቀም ወሳኝ በመሆኑ ሁለቱ ሀገራት በቴክኖሎጅዉ ዘርፍ የሚያደርጉት ትብብር  እንደ አቶ ተስፋዬ  ጠቀሜታዉ ከፍ ያለነዉ።


በምክክሩ እንደ «ሲመንስ«ያሉ ትልልቅ ስምና አቅም ያላቸዉ የጀርመን የቴክኖሎጅ ኩባንያዎችም በኢትዮጵያ በስፋት ለመስራት ፈቃደኝነታቸዉን ገልፀዋል።የእነዚህ ኩባንያዎች ወደ ሀገሪቱ መምጣት የቴክኖሎጅ አቅምን ለማሳደግ  ከማገዙም በላይ ሌሎች ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ለመሳብ ዕድል ሊፈጥር እንደሚችል ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።
በሌላ በኩልም በኩባንያዎቹ የሚቀርቡ የቴክኖሎጅ ምርቶች ተጠቅሞ ኑሮን ለማሻሻልና ገቢን ለማሳደግ ፣ዓለም የደረሰበትን ቴክኖሎጅ  አይቶ ለመቅዳት፣አሻሽሎ ለማቅረብ  እንዲሁም የፈጠራ ሀሳቦችን በህብረተሰቡ ዘንድ ለማጎልበትም አስተዋፅኦ ያደርጋል ነዉ ያሉት።


የጀርመን ዓመታዊ የግኝት ዘገባ እንደሚያሳየዉ በጎርጎሮሳዉያኑ 2016 ዓ/ም ብቻ በሀገሪቱ ከ158 ቢሊዮን ዩሮ በላይ በቴክኖሎጅ የፈጠራ ስራዎች ገቢ ተገኝቷል።ከዚህም ሶስት አራተኛዉ ከኢንደስትሪዉ ዘርፍ የተገኜ ነዉ።
ለዚህም በሀገሪቱ ለሳይንስና ለቴክኖሎጅ የሚሰጠዉ ዋጋ ከፍ ያለ መሆን፤ቴክኖሎጅዉን ከፖለቲካና ከኢንደስትሪ ጋር አጣምሮ መጓዝ፣አዳዲስ ፈጠራዎችን በገንዘብ መደገፍ፣ከወቅቱና ከነባራዊዉ ሁኔታ ጋር የሚሄዱ ዘርፎችን መለየትና በራዕይ የተቃኜ የኢኮኖሚና የቴክኖሎጅ ዕቅድ በዘርፉ ለተመዘገበዉ ስኬት በምክንያትነት ይጠቀሳሉ።እንደ ኢትዮጵያ በቴክኖሎጅ ልማት ጀማሪ የሆኑ ሀገራትም መሰረታቸዉን በእነዚህ ተሞክሮዎች ላይ ቢጥሉ በዘርፉ የተሻለ እድገት ሊያመጡ እንደሚችሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነዉ ያድምጡ።

 

ፀሐይ ጫኔ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic