የጀርመን ብሔራዊ ጦር የሶማልያ ተልዕኮ ማብቃት | አፍሪቃ | DW | 31.03.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የጀርመን ብሔራዊ ጦር የሶማልያ ተልዕኮ ማብቃት

በሶማልያ የፖለቲካው ውዝግብ  አሁንም መፍትሔ አላገኘም። ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ በሶማልያ መንግሥት አንፃር የሚታገለውን አሸባብ እንዳዳከመ ቢናገሩም፣ ዓማፂው ቡድን የሽብር ጥቃት መጣሉን አላቋረጠም።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 12:45

በሶማሊያ የሚታየው አዳጋቹ የፖለቲካ ሁኔታም ትልቅ ተግዳሮት  ደቅኗል

ዩኤስ አሜሪካ በአብራሪ የለሽ የጦር አይሮፕላኖች ጭምር በሚታገዘው ወታደራዊው ርምጃ ላይ አትኩራለች። የአውሮጳ ህብረት ደግሞ የሶማልያን ጦር ሠራዊት በፀጥታ አጠባበቅ ረገድ ብቁ ይሆን ዘንድ በማሠልጠን ላይ ይገኛል።

በህብረቱ የስልጠና ተልዕኮ የተሳተፈው የጀርመን ብሔራዊ መከላከያ ሰራዊት የአውሮጳ ህብረት በሶማልያ በጀመረው የፀጥታ ኃይላትን የማሰልጠን ተልዕኮ ውስጥ የሚያደርገውን ተሳትፎ ዛሬ በጎርጎሪዮሳዊው መጋቢት 31፣ 2018 ዓም ያበቃል። በጀርመን መከላከያ ሰራዊት ዘገባ መሰረት፣ ከ12 ሀገራት የተውጣጡ 155 አባላት ያጠቃለለው  እና ከስምንት ዓመት በፊት የተቋቋመው የአውሮጳውያኑ የስልጠና ተልዕኮ ከ5,000 የሚበልጡ ሶማልያ ወታደሮችን አሰልጥኗል። የጀርመን መንግሥት ተሳትፎውን ለሚያቋርጥበት ድርጊት በሶማልያ  ተጓድሎ የሚገኘውን ፖለቲካዊ እና ተቋማዊ መዋቅር እንደ ምክንያት ጠቅሷል። የሶማልያ ፀጥታ ኃይላት በቂ ጥንካሬ የሌላቸው እንደሆኑም ለዶይቸ ቬለ በደረሰው የመከላከያ ሚንስቴር መግለጫ ተነቧል። በዚህም የተነሳ የአውሮጳውያኑ የስልጠና ተልዕኮ  የሶማልያን ጦር በዘላቂነት ለማጠናከር የሚያስችለውን ስልጠና እንደሚፈልገው ማከናወን አልቻለም።

 
ስልጠና ያገኙት የሶማልያ ወታደሮች የሚያስፈልጋቸውን በቂ ትጥቅ አለማግኘታቸውን  የመከላከያ ሚንስቴሩ ካቀረባቸው ወቀሳዎች መካከል አንዱ ነበር። ከብዙ ዓመት ተሳትፎ በኋላ የጀርመን መከላከያ ሚንስቴር ይህን ዓይነት ወቀሳ መሰንዘሩ በጣም ጎጂ ቢሆንም፣ አስገራሚ እንዳልሆነ በአውሮጳ ህብረት የስልጠና ተልዕኮ ውስጥ አማካሪ የነበሩት ሽቴፋን ብሩነ አስታውቀዋል።
« በሶማልያ ቆይታዬ ያነጋገርኳቸው የብሔራዊው መከላከያ ሰራዊት ወታደሮች በጠቅላላ፣ ተልዕኮው ንዑስ በመሆኑ የሶማልያን ጦር ማሰልጠኑን ጉዳይ በተመለከተ ባጠቃላይ ያን ያህል ውጤት እንደማይጠብቁ ነበር የገለጹልኝ። »
በሀገሪቱ የሚታየው አዳጋቹ የፖለቲካ ሁኔታም ትልቅ ተግዳሮት  ደቅኗል። በዚህም የተነሳ  እንደሚታወሰው እስከ 2013 ዓም ድረስ ሶማልያውያን ወታደሮችን የማሰልጠኑ ተግባር ዩጋንዳ ውስጥ ነበር የተከናወነው። 
በ2017 ዓም ብዙ ተስፋ የተጣለባቸው መሀመድ አብዱላሂ መሀመድ ፕሬዚደንት ሆነው ቢመረጡም በ20 ዓመት የርስበርስ ጦርነት ደካማ የመንግሥት መዋቅር  እና በግዛቶችዋ መካከል ትልቅ ልዩነት በሚታይባት ሀገር ውስጥ ንዑሱን ስልጣን ብቻ ነው የያዙት። ውዝግቡ በተስፋፋባቸው ዓመታት የተለያዩት ግዛቶች ሰፊ ራስ ገዝ መዋቅር አቋቁመዋል። ሶማሊላንድ ነጻ መንግሥት መስርታ ዓለም አቀፍ እውቅና ለማግኘት እየሞከረች ነው። ይህን ሁኔታ ማዕከላዩ መንግሥት ለማብቃትን በፌዴራል ስርዓት ለመለወጥ ይፈልጋል። ግን ውጥረቱ እንደቀጠለ ነው።  


የሶማልያ ውስጣዊ ውዝግቦች ብቻ ግን አይደሉም ችግሩን ውስብስ ያደረጉት። ያልተቀናጀው በሶማልያ የሚንቀሳቀሱት የዓለም አቀፍ ተዋናዮች ተግባር እና ዩኤስ አሜሪካ አሸባብን በድሮን መውጋት የያዘችበትም  ርምጃ የራሳቸውን ተፅዕኖ እንዳሳረፉ ሽቴፋን ብሩነ ገልጸዋል።
«በአብራሪ አልባ የጦር አይሮፕላን ጥቃት ድርጅቱ ምናልባት እንደ መደበኛ ጦር የመዋጋት አቅሙን ሊያዳክመው ይችል ይሆናል። ይሁንና፣ ይህ ካለፉት 20 ዓመታት ወዲህ እየሞከረ ያለ ሲሆን፣ ይህ ዓይነቱ መፍትሔ የመፈለጉ ሙከራ እስካሁን ያን ያህል ውጤታማ አልሆነም። »
በዚህም የተነሳ ለሶማልያ ውዝግብ ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲገኝ ጥረት እንዲደረግ እና ይፋዊ ያልሆነ ንግግር የሚካሄድበት ሁኔታ ሊመቻቻች እንደሚገባ ነው ሽቴፋን ብሩነ ያሳሰቡት። 
በዚሁ ረገድ በጀርመን መከላከያ ሚንስቴር ዘገባ መሰረት፣ የጀርመን መንግሥት በፀጥታው ዘርፍ ሊያበረክተው የሚችለውን ርዳታ፣ ማለትም፣ በተጨባጭ ከፖሊስ ጋር የሚኖረውን ትብብር ማጠናከር የሚችልበትን ሁኔታ እየፈተሸ  ነው። ጀርመን በወቅቱ በሶማልያ ፌዴራዊውን ስርዓት በመገንባቱ፣ የቀድሞ የአሸባብ ተዋጊዎችን መልሶ በማዋኃዱ እና ላካባቢ ውዝግቦች የእርቀ ሰላሙ ሂደት በሚነቃቃበት ተግባራት ላይ ርዳታ እያደረገች ነው። ጀርመን የሶማልያ አሰልጣኞችን የማሰልጠኑ እና የማማከሩ ተግባር በተለይ ትኩረት ያገኝ ዘንድ በአውሮጳ ህብረት ውስጥ ጥረቷን ለማጠናከር ትፈልጋለች።

አርያም ተክሌ

ነጋሽ መሀመድ
 

Audios and videos on the topic