የጀርመን ባለሃብቶች በሩስያ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 15.05.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የጀርመን ባለሃብቶች በሩስያ

በሩስያና በምዕራባውያን መካከል የተፈጠረው ቅራኔ ተካሯል ። በሩስያ ላይ የኤኮኖሚ ማዕቀብ የመጣሉ ዛቻ አሁንም እንደቀጠለ ነው ። የሩስያ የኤኮኖሚ እድገት እምርታ ቀደም ካለ ጊዜ አንስቶ ቀንሷል ። በአሁኑ ቀውስ ደግሞ እድገቱ ተገቷል ። ይህ ደግሞ በጀርመን የውጭ ንግድ ላይ ተፅእኖ እያሳደረ ነው ።

በርካታ ሩስያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የጀርመን ኩባንያዎች ገቢያቸው እየቀነሰ ሲሆን አንዳንዶቹም በሃገሪቱ የጀመሩትን የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት እያቋረጡ ነው ። ክላስ ሃላፊነቱ የተወሰነ ኩባንያ ሩስያ ውስጥ ለረዥም ጊዜ በመሥራቱ ኩራት ይሰማዋል ። የጀርመኑ የግብርና ማሽኖች አምራች ኩባንያ ክላስ እጎአ ከ1980 አንስቶ ሩስያ ውስጥ ውስጥ በትጋት ይሰራል ። ከ10 ዓመት በፊት ኩባንያው በደቡብ ሩስያዋ ከተማ ክራስኖዳር ለአካባቢው የእርሻ መሣሪዎች የሚያቀርብ ፋብሪካ ገንብቷል ።በቅርቡም ኩባንያው ከ100 ሚሊዮን ዩሮ ወይም ከ137 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ በማውጣት የሚያመርታቸውን የሰብል ማጨጂያና መውቂያ ማሽኖችን እንዲሁም ትራክተሮችን መጠን በእጥፍ ለማሳደግ ወስኗል ። ይሁንና አሁን ገበያው እንቀደቀድሞው ጥሩ አይደለም ። የኩባንያው ቃል አቀባይ ቮልፍራም ኤበርሃርድ

«በአጠቃላይ ማለት የሚቻለው በአሁኑ ጊዜ የሩስያ ና የዩክሬን የንግድ እንቅስቃሴ መቀዝቀዝ በርግጠኝነት በዚህ ዓመት በምናገኘው ገቢ ላይ ተፅእኖ ያሳድራል ። »

ከሩስያ ጋር የተፈጠረው የፖለቲካ ፍጥጫ በጀርመን ኤኮኖሚ ላይ ተፅእኖ ማሳደር ጀምሯል ። በጀርመን የውጭ ንግድ ምክር ቤት የተካሄደ የዳሰሳ ጥናት 61 በመቶ የጀርመን ኩባንያዎች የፖለቲካው ቀውስ የእለት ተእለት እንቅስቃሴያቸውን እየጎዳው መሆኑን ጠቁሟል ።አንድ ሶስተኛ ያህሉ ደግሞ ገቢያቸው ማሽቆልቆሉን አስረድተዋል ። የጀርመንን ማሽኖች በመግዛት ሩስያ ከዓለም አራተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ አገር ናት ።

በጎርጎሮሳውያኑ 2013 የጀርመን ኩባንያዎች ለሩስያ በሸጧቸው ማሽኖች ያስገቡት ገንዘብ 7.8 ቢሊዮን ዩሮ ይደርሳል ። ሆኖም በያዝነው በጎርጎሮሳውያኑ 2014 የመጀመሪያዎቹ 2 ወራት ወደ ሩስያ ከሚላክ ምርት የገባው ገንዘብ በ19 በመቶ መቀነሱን የጀርመን የማሽን ኢንዱስትሪ ማህበር አስታውቋል ። ይህ የሆነውም ከዩክሬን ቀውስ አስቀድሞም ነው ። ባለፈው ዓመት የሩስያ ገንዘብ ሩብል፣ከዩሮ ጋር ሲነፃፀር ከቀደመው ዋጋ በአንድ አምስተኛ ቀንሶ ነበር ። የፖለቲካ ቀውሱ ደግሞ የሩብልን ዋጋ ማሽቆልቆል አፋጥኖታል ። የሩስያ ኩባንያዎች አሁን ብድር ለማግኘት እየተቸገሩ ነው ፤ ባለሃብቶችም ሩስያ ውስጥ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ወደ ኋላ እያሉ ነው ። በሩብል የመግዛት አቅም መቀነስ

ምክንያት ደግሞ ጀርመን ውስጥ የተሰሩ ማሽኖች ዋጋ እየተወደደ ነው ። በዚህ ሰበብም በሩስያ የአንዳንድ የጀርመን ኩባንያዎች ገቢ ቀንሷል ። የጀርመኑ የመድሃኒት አምራች ኩባንያ ስታዳ ለምሳሌ በሩስያ ገቢው በ13 በመቶ ሲያሽቆለቁል መኪና አምራቹ ቮክስ ዋገንም የሚሸጣቸው መኪናዎች ቁጥር ቀንሷል ። የቀውሱ መባባስ ያሳሰባቸው በርካታ የጀርመን ኩባንያዎች በሃገሪቱ ሊያካሂዱ ያቀዷቸውን ውረታዎች እያዘገዩ ነው ። ለምሳሌ ክዩነ የተባለው የጀርመን የምግብ ኩባንያ በሩስያ ፋብሪካ ለመገንባት መሬት ገዝቶ አስፈላጊውንም መስፈርት አሟልቶ ነበር ። ሆኖም ግንባታውን ላልተወሰነ ጊዜ ገፍቶታል ። የጀርመን ኢንዱስትሪዎች ምክር ቤት እንደሚለው ሩስያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ወደ 6 ሺህ የሚጠጉ የጀርመን ድርጅቶችና ኩባንያዎች አሉ ። በማህበሩ የሩስያ ጉዳዮች አዋቂ ቶብያስ ባውማን ግን ሩስያ ውስጥ የሚሰሩ በርካታ የጀርመን ኩባንያዎች በቀውሱ ምክንያት ገበያቸው መቀዝቀዙ ያን ያህል አሳሳቢ አይደለም ይላሉ

« የሩስያ ገበያ ጠቃሚ ነው ። ከቅርብ ዓመታት ወዲህም የሩስያ ገበያችን ከሌሎቹ ሃገራት በፍጥነት እያደገ ነው።ሆኖም ያን ያህል ትልቅ የሚባል አይደለም።ጀርመን ከሌላው ዓለም ጋር ከምታካሂደው የውጭ ንግድ ጋር ሲነፃፀር ወደ ሩስያ የሚሄደው የጀርመን ምርት ገበያ ድርሻ 3.2በመቶ ብቻ ነው። »

በተናታኙ አባባልየሩስያ የኤኮኖሚ እድገት በማዝገም ላይ መሆኑ በጀርመን ላይ አሳሳቢ የሆነ መዘዝ ሊያስከትል አይችልም ።

ሂሩት መለሰ

ነጋሽ መሀመድ

Audios and videos on the topic