የጀርመን ቅኝ ግዛት ዘመን በናሚቢያ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 06.03.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የጀርመን ቅኝ ግዛት ዘመን በናሚቢያ

ትናንት በርሊን ላይ ሻሪቴ የህክምና ዩኒቨርሲቲ ሶስት ሙሉ እና 18 የጭንቅላት አጽም ለናሚቢያ ልዑካን አስረከበ። አፅሞቹ ከአንድ መቶ ዓመታት በላይ የሆናቸዉ ሲሆኑ ጀርመን ናሚቢያን በቅኝ ገዢነት የያዘችበት ወቅት ያመላክታሉ። በወቅቱ ሄሬሮ እና ናማ የተሰኙት ጎሳዎች በጀርመን ቅኝ ገዢዎቻቸዉ ላይ አምፀዉ ነበር።

ቅኝ ገዢዎቻቸዉም ጭካኔ በተሞላበት ርምጃ አመፁን አስክነዋል። ያኔም በሺና አስር ሺዎች የሚገመቱት ተገድለዋል። የታሪክ ምሁራን ድርጊቱን የዘር ማጥፋት ይሉታል፤ የጀርመን መንግስታት ግን ቃሉን አለመጠቀም ብቻ ሳይሆን ካሳም ለመክፈል አልደፈሩም ይላል በርክክቡ ወቅት የተገኘዉ የዶቼ ቬለዉ ሚኻኤል ሳክቱሮ።

በበርሊኑ የሻሪቴ ህክምና ዩኒቨርሲቲ ዲፕሎማቶች እና የጀርመን አፍሪቃ ማኅበረሰብ ተገኝተዋል። የተሰባሰቡትም በደቡብ ምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት በቅኝ ገዢ መንግስት በወቅቱ የተፈፀመን የጭካኔ ድርጊት ለመዘከር ነዉ። ትናንት ናሚቢያ ነበረች ባለተራ። ጀርመን ደቡብ ምዕራብ አፍሪቃን በጎርጎሪዮሳዊዉ 1885 እስከ 1915ዓ,ም ድረስ በእኝ ገዢነት ስትቆጣጠር ቆይታለች። በወቅቱም በቅኝ ገዢዎቻቸዉ ላይ ያመፁ የናሚቢያ ዜጎች ተፈጅተዋል። የናሚቢያ የባህል ሚኒስትር ጄሪ ኤካንጆ፤

«የናሚቢያ መንግስት ከነዚህ የዘግናኝ ወንጀል ሰለቦች ጎን በጥብቅ ይቆማል። ይህ ወንጀል የ20ኛዉ ክፍለ ዘመን የመጀመሪያዉ የሰዉ ዘር ማጥፋት መሆኑ ታዉቋል።»

የጀርመን የዜና ወኪል üዴ ፔ አ» እንደዘገበዉ አብዛኞቹ ቅኝ ገዢዎች አፍሪቃዉያን ዝቅ ያሉ ዘሮች ናቸዉ ብለዉ ከማሰብ አልፈዉ፤ አጥንት አፅማቸዉን ለምርምር ይወስዳሉ። የሄሬሮ፣ ዳማራ፣ ናማ፣ ሳን እና ኦዋምቦ ሕዝቦች አፅምም ለዚሁ ሳይንሳዊ ምርምር ባህር ተሻግሯል። የሻሪቴ ሃኪም ቤት ኃላፊ ካርል ማክስ አይንሃዉፕል እንደአንድ ሳይንቲስት ለተደረገዉ በግላቸዉ አፅሙን የተረከቡትን ልዑካን ይቅርታ ጠይቀዋል። እሳቸዉ እንዳመለከቱትም አፅሞቹ የተሰባሰቡት የዘረኛ ቅኝ ገዢዎችን ርዕዮተዓለም ለመተንተን ላለመ ምርምር ነዉ። የባህል ሚኒስትሩ በሌሎች የጀርመን ሃኪም ቤቶችም ሆነ ቤተ መዘክሮች የተሰበሰበ ካለ እንዲያስረክቡ ጠይቀዋል።

በስርዓቱ ላይ የተገኙት የጀርመን መንግስት ወኪል ንግግር ከማድረግ ዉጭ በጉዳዩ ላይ ዝርዝር ጉዳዮች ለመገናኝ ብዙሃን ከመናገር ተቆጥበዋል። በጀርመን የናሚቢያ አምባሳደር ኒቭል ገርትዘ ግን የተከናወነዉ ሥርዓት የጀርመን ናሚቢያን ግንኙት አንድ ደረጃ ወደፊት መራመዱን ያመክታል ነዉ ያሉት።

«ይህ በቅኝ አገዛዝ ታሪክ ለተጎዱ ሰዎች ፍትህ የማስገኘትና እዉቅና የመስጠት ቀጣይ ጥረታችን አካል ነዉ። ከዚህ በኋላም በርካታ ደረጃዎች ይቀጥላሉ።»

የአፍሮ ጀርመን የመብት ተሟጋቾች ግን በትናንቱ የርክክብ ስርዓት አልተደሰተም። መፈክር ያነገቡ በርካታ አፍሪቃዉያን ቡድኖችም ከጎርጎሪዮሳዊዉ 1904 እስከ 1908ዓ,ም ድረስ በተካሄደዉ የሄሬሮ አመፅ ወቅት ለጠፋዉ ህይወት ካሳ እንዲሰጥ እና ይፋ ይቅርታም እንዲጠየቅ ጥሪ አስተላልፈዋል። ሞክታ ካማሬ ይህን ከሚሉት አንዱ ነዉ።

«የናሚቢያ ሚኒስትር በግልፅ እንደተናገሩት የጀርመን መንግስትም የሰዉ ዘር ማጥፋት ነዉ እንዲል እፈልጋለሁ። ምክንያቱም የጀርመን መንግስት ይህን ቃል መጠቀም አልፈለገም። የጦርነት ሰለቦች ነዉ የሚለዉ። ስለዘር ማጥፋት አይናገሩም። እናም በግልፅ የዘር ማጥፋት ነዉ እንዲሉና ለሰለባዎቹ ካሳ እንዲከፍሉ እፈልጋለሁ።»

ልክ የዛሬ መቶ ዓመት የናማ እና ኤሬሮ ጎሳዎች በጀርመን ቅኝ ገዢዎቻቸዉ ላይ አመፁ። ቅኝ ገዢዎቻቸዉ ደግሞ እነሱን የማጥፋት እቅድ አዘጋጁ። እናም በአራት ዓመታት ዉስጥ 80,000ዎቹ አለቁ። ከዚያም በመቶዎች የሚቆጠሩ አፅሞች ወደበርሊን ተወሰዱ የዘር ጥናት ምርምር ሊደረግባቸዉ። የዛሬ 10ዓመት የጀርመን የልማት ሚኒስትር ለጅምላ ግድያዉ ይቅርታ ጠየቁ። ከዚያ ወዲህ ግን ጥፋቱ መፈፀሙን የማመን ነገር ከጀርመን መንግስት ወገን አልተሰማም። የናሚቢያ ብሄራዊ ቤተ መዘክር ዋና ኃላፊ ኤስተር ሞምቦላ ጉዋጎሴስ እሳቸዉ ግልፅ የዘር ማጥፋት ነዉ የሚሉትን ጀርመን ችላ ለማለት መሞከሯ አሳሳቢ ነዉ ይላሉ፤

«የያኔዉ የጀርመን መንግስት የፈጸመዉ ተግባር በወጣት ጀርመናዉያንም ቢታወቅ እንመኛለን። ምክንያቱም በዚህ መንገድ ሰዎች እርቅ ሊያወርዱና ሊያዉቁ የሚችሉት።»

ወጣት ጀርመናዉያን ስለቅኝ ግዛት ዘመን እጅም የሚያዉቁት እንደሌለ ነዉ የሚናገሩት። በስፍራዉ ከተገኙት አንዳንዶችም ስለቀድሞዉ ታሪክ ማወቅ ቢፈልጉም ስለዘር ማጥፋት ሳይሆን በርካቶች መገደላቸዉን የሚገልፁ መረጃዎችን በጥቂቱ በትምህርት ቤት ደረጃ መስማታቸዉን ነዉ ያመለከቱት።

«እንደሚመስለኝ አስረኛ ክፍል ላይ ብቻ ነዉ በጥቂቱ ስለዚህ ጉዳይ የተነገረን። ያዉም በርካታ ሰዎች ስለመገደላቸዉ ብቻ ነዉ።»

የጀርመን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣዉ መግለጫ ናሚቢያ ነፃ ከወጣችበት ከጎርጎሪዮሳዊዉ 1990ዓ,ም ጀምሮ በርሊን ታሪካዊ፣ ፖለቲካዊና ሞራላዊ ኃላፊነት እንዳለባት አመልክቷል። በቅኝ ግዛቱ የጦርነት ወቅት ለተፈጸሙ ድርጊቶችም ጥልቅ ፀፀቱን ገልጿል።

ሚኻኤል ሳክቱሮ/ ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic