የጀርመን ቅኝ ገዢዎችና ናሚቢያ | አፍሪቃ | DW | 17.03.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የጀርመን ቅኝ ገዢዎችና ናሚቢያ

ጀርመን አንድ መቶ አስራ-ሁለት ዓመታት ያስቆጠረዉ ግፍ መፈፀሙን ካመነች፤ጉዳዩን በጀርመን በኩል የሚከታተሉት ልዩ መልዕክተኛ ሩፕሬሽት ፖሌንስ እንደሚሉት ፤ ናሚቢያዎች «ረጅም ጊዜ የጠበቅነዉ ደረሰ፤» ብለዉ ይደሰታሉ። ለየሔሬሮ ተወካዮች ግን ይሕ በቂ አይደለም።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:03
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:03 ደቂቃ

የጀርመን ካሳ ለናሚቢያ

የጀርመን ቅኝ ገዢ ጦር እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር 1904 እስከ 1908 በናሚቢያ ሕዝብ ላይ ለፈፀመዉ ጭፍጨፋ ጀርመን በይፋ ይቅርታ እንድትጠይቅ በሚያሳስበዉ ረቂቅ ላይ የጀርመን ምክር ቤት ዛሬ ተነጋግሯል።በምክር ቤቱ የግራ የፖለቲካ ፓርቲ እንደራሴ ኒማ ሞሳቫት ከአንድ ሌላ የምክር ቤት ባልደረባቸዉ ጋር ሆነዉ ያረቀቁት ሰነድ የጀርመን መንግሥት ለተበዳይ ወገኖች ካሳም እንዲከፍል የሚጠይቅ ነዉ።ጀርመን ለተበዳዮች ካሳ ይከፈል የሚለዉን ሐሳብ ብትደግፍም፤ የሚከፈላቸዉ ወገኖች ማንነት፤ የክፍያዉ አፈፃፀም፤የናሚቢያ መንግሥትና የጎሳ ተጠሪዎች ሐላፊነት እስካሁን ቁርጥ ብያኔ አላገኘም።የይቅርታዉም ጉዳይ ብዙ እንዳከራከረ ነዉ።

የጀርመን ቅኝ ገዢ ጦር አገዛዙን አንቀበልም ባሉ የናሚቢያ ተወላጆች በተለይ በሔሬሮ እና ናማ ጎሳ ተወላጆች ላይ ከ1904 (እጎአ) ጀምሮ አራት ዓመት በዘለቀ ጭፍጨፋዉ 70 ሺሕ በላይ የሐሬሮ ተወላጆችን ፈጅቷል።ከግማሽ የሚበልጥ የናም ጎሳ አባላትን አጥፍቷል።ፀረ-ቅኝ ገዢ አርበኞች በተለይም የናሚቢያ ሕዝብ ዘግናኙን ግፍ በየጊዜዉ ቢያነሱ-ቢያወሱትም የጀርመን መንግሥት እስካለፈዉ ዓመት ድረስ ሥለ ጅምላ ጭፍጨፋዉ በግልፅ ያለዉ ነገር አልነበረም።

ለጭፍጨፋዉ ይቅርታ መጠየቅማ ላሁኑ የሚታሰብ አይመስልም።በጀርመን የናሚቢያ አምባሳደር አንድርያስ ጉይቤድ ግን ሒደቱ ጥሩ ነዉ ይላሉ።

«ወደፊት በተጓዝን ቁጥር ለናሚቢያ ጥሩ አቅጣጫ እንደሚሆን ተስፋ አለን።ፕሬዝደንቱ ወይም መራሔ-መንግሥቱ ይቅርታ ከጠየቀ እሱ ወይም እሷ የጀርመንን ሕዝብ እንደሚወክሉ ጥርጥር አይኖረዉም።»

ጀርመን አንድ መቶ አስራ-ሁለት ዓመታት ያስቆጠረዉ ግፍ መፈፀሙን ካመነች፤ጉዳዩን በጀርመን በኩል የሚከታተሉት ልዩ መልዕክተኛ ሩፕሬሽት ፖሌንስ እንደሚሉት ናሚቢያዎች «ረጅም ጊዜ የጠበቅነዉ ደረሰ፤» ብለዉ ይደሰታሉ። ለየሔሬሮ ተወካዮች ግን ይሕ በቂ አይደለም።የሔሬሮ መሪ ቬኩዪ ሩኮሮ «ለዉዝግቡ ሁነኛ እልባት ለማግኘት የጀርመን፤ የናም እና የሔሬሮ ጎሳ ተጠሪዎች እና የናሚቢያ መንግሥት የሰወስትዮሽ ድርድርና ሥምምነት ማድረግ አለባቸዉ።» ብለዉ ነበር በቅርቡ።

የጀርመን ምክር ቤት እንዲነጋገርበት ረቂቁን ካቀረቡት ዋናዉ የግራ ፖለቲከኛ ኒማ ሞሳቫት ተመሳሳይ እምነት አላቸዉ።በተለይ የሲቢል ማሕበረሰብ አባላት በድርድር-ሥምምነቱ ሒደት መሳተፍ አለባቸዉ ይላሉ።

«ወሳኙ ጥያቄ ሁለቱ መንግሥታት በሚያደርጉት ሥምምነት የሔሬሮ እና የናማ ተወካዮች እንዴት ይሳተፋሉ? ነዉ።ያለነሱ እንደማይሆን አስታዉቀዋል።እነሱ ያልተሳተፉበትን ዉል እንደማይቀበሉት ግልፅ አድርገዋል።ዉሉ አሳማኝ መሆን አለበት።የተበዳዮች ወገኖች በድርድሩም ሆነ በሥምምነቱ በሆነ ደረጃ መሳተፍ አለባቸዉ።»

ሁለቱም መንግሥታት ግን የጎሳዎቹ ተወካዮች በድርድሩም በስምምነቱም መካፈላቸዉን አይፈቅዱትም።ድርድር-ሥምምነቱ የመንግሥት ለመንግሥት ይፋዊና ሕጋዊ መሆን አለበት ባዮች ናቸዉ።የናሚቢያዉ አምባሳደርማ ይጠይቃሉ-ስንቱን የጎሳ ተጠሪ እናሳትፋለን? እያሉ።

«ድርድር የሚደረገዉ በሁለቱ የተመረጡ መንግሥታት ተወካዮች መካከል እንጂ ከሁሉም ማሕበረሰብ ጋር አይደለም።ናሚቢያ ዉስጥ መንግሥት እዉቅና የሰጣቸዉ ብዙ ባሕላዊ ባለሥልጣናት አሉ።ሁሉንም እናሳትፍ ከተባለ አንድ ብሔራዊ ምክር ቤት ይኖረናል ማለት ነዉ።ከብሔራዊ ምክር ቤት ጋር መደራደር ማለት ነዉ።ይሕ ደግሞ የማይሆን ነገር ነዉ።»

ላለቁት ወገኖች የሚሰጠዉ ካሳና የሚሰጥበት መንገድም ሌላ የዉዝግብ ምክንያት ነዉ።የሔሬሮዉ መሪ ቬኩዪ ሩኮሮ ሕዝባቸዉ ጠቀም ያለ ገንዘብ ማግኘት አለበት ባይናቸዉ።እንደራሴ ኒማ ሞሳቫትም ይሕን ሐሳብ ይጋራሉ።ሔሬሮች የሚኖሩበት አካባቢ እጅግ ከደኸዩት የናሚቢያ ግዛቶች አንዱ ነዉ፤ ክድሕነቱ ምክንያቶች፤ ሞሳቫት እንደሚያምኑት ጭፍጨፋዉ አንዱ ነዉ።

የጀርመን ልዩ መልዕክተኛ ሩፕሬሽት ፖሌንስ ግን ለሔሬሮ ይሁን ለናማ ጎሳ አባላት በቀጥታ ገንዘብ ይከፈል የሚለዉ ሐሳብ አይቀበሉትም።ፖሌንስ ካሳ ከተከፈለ ለአካባቢዉ ልማት መዋል አለበት ባይ ናቸዉ።ናሚቢያ ነፃ ከወጣች 1982 ጀምሮ ከጀርመን 800 ሚሊዮን ዩሮ ርዳታ አግታለች።ይሕ የጀርመን ቅኝ ገዢዎች ላደሩስት ጭፍጨፋ እንደካሳ የሚቆጠር አይደለም።

ነጋሽ መሀመድ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች