የጀርመን ምክርቤት የዶይቸ ቬለን ሕግ አፀደቀ | የጋዜጦች አምድ | DW | 29.10.2004
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

የጀርመን ምክርቤት የዶይቸ ቬለን ሕግ አፀደቀ

የጀርመን ምክርቤት/ቡንደስታክ ስለ ዶይቸ ቬለ ራዲዮ በአዲስ አደራረስ የተዘጋጀውን ሕግ ትናንት አጽድቆታል። በዚህም መሠረት፥ መልእክቶቹን ወደ ውጭ የሚያሰራጨው ይኸው የጀርመን ባለአጭር ሞገድ ጣቢያ የወ’ጭ ዕቅዱን ወደፊት ለአራት ዓመታት መዘርጋት ይኖርበታል፤ ለዚሁ የጊዜ ሰሌዳ አስተማማኝ የፊናንስ አቅም ይሰጠዋል።

አሁን 265 ሚሊዮን ኦይሮ የሚደርሰው ዓመታዊ በጀቱ፥ የራዲዮ መርሐግብሩን በ፴ ቋንቋዎች፣ የቴሌቪዚዮን መርሐግብሩንም በጀርመንኛ፣ በእንግሊዝኛ እና በእስጳንኛ ለማሰራጨት፤ የኢንተርኔት አገልግሎቱንም ለማስፋፋት ያስችለዋል።

ስለ ዶይቸ ቬለ ራዲዮ በአዲስ ይዘት የተዘጋጀውን የሕግ ሠነድ የጀርመኑ ምክርቤት/ቡንደስታክ በሙሉ ድምጽ ነው ያፀደቀው። በዚህ አኳኋን፥ መልእክቶቹን በራዲዮ፣ በቴለቪዚዮንና በኢንተርኔት ወደ ውጭ የሚያሰራጨው ይኸው የጀርመኑ ባለአጭር ሞገድ ጣቢያ፥ በጀርመንና በተቀረው ዓለም መካከል አገናኝ ድልድይ የሚሆንበትን ሚና አሳክቶ ለማከናወን ይችላል። ለባሕልና ለመገናኛ-ብዙሃን ቋሚ የሆኑት ሚኒስትር-ዴታ ክሪስታ ቫይስ ስለዚሁ የሰጡት መግለጫ፥ “...........የዶይቸ ቬለ አቅርቦት--ማለት የራዲዮ፣ የቴሌቪዚዮንና የኢንተርኔት ስርጭት ራሱ ግብ አይደለም፣ ዶይቸ ቬለም እንዲያው የዜና ጣቢያ ብቻ ሆኖ አይደለም የሚታየው። ዶይቸ ቬለ የባሕል ሀገር ጀርመንን በየዘርፎቿ ቀርጾ እንዲያቀርብ ይጠየቅበታል። ይህንኑ ነው ተሻሽሎ የቀረበው ሕግ የሚያስፈጽመው፤ ይህ በመገናኛብዙሃን እና በባሕል መርሕ ረገድ ከፍተኛ ትርጓሜ ያለው አዲስ ነገር ነው።”

የዶይቸ ሼለ ፊናንስ-ፍላጎት በአንድ ገለልተኛ ገምጋሚ እንዲወሰን ባለመደረጉ፣ በበርሊኑ ፈደራዊ ምክርቤት/ቡንደስታክ ውስጥ የተቃውሞውን ሚና የሚይዙት ክርስቲያንዴሞክራቶች አባል በርንት ኖይማን ሂስ ሰንዝረዋል። እንደ ሁኔታው መጠን የዶይቸ ቬለም በጀት በያመቱ መፈተሽ እንዳለበትም ነው ምክርቤቱ በአዲሱ ሕግ ውስጥ መመሪያ የሰጠው።

ዶይቸ ቬለ በበጀት አመዳደብ ረገድ ከሌሎቹ ተቋማት የተለየ ሆኖ መታየት እንዳለበት የሚያስገነዝቡት የክርስቲያን-ዴሞክራቶቹ ወኪል ኖይማን፥ “...........ዶይቸ ቬለን የመሰለ አንድ ራዲዮ-ተቋም ከተቀሩት የሕዝብ ተቋማት ጋር እኩል የሚደረግ አይደለም። አንድ ራዲዮ ጣቢያ በሌሎች መስፈርቶች መሠረት ነው የሚሠራው፥ ማለት በጋዜጣዊው መስፈርት--ይኸው ጋዜጣዊ መሥፈርት የሐሳብን ነፃነት እና ከመንግሥት ተጽእኖ መራቅን እጅግ ነው የሚያከብረው።”

ለዶይቸ ቬለ ሥራ ዋና ቀዳሚ ግዴታ የሚሆነው፥ የተፍታታው በጀት አደላደል ነው። ይኸው መመሪያ ራዲዮ-ጣቢያው በአንዱ የበጀት ዓመት ያልተጠቀመበትን ገንዘብ ያለቅናሽ ወደ አዲሱ የበጀት ዓመት እንዲያዛውረው ይፈቅድለታል። ይኸው ማረጋገጫ ርግጥ ሕግ ውስጥ በአበክሮ አልተያዘም፣ ግን ምክርቤቱ በተስማማበት ውሳኔ ጥብቀትን አግኝቷል።

ዶይቸ ቬለ የወጭ ዕቅዱን ለየአራት ዓመታት እያዘጋጀ ያቀርብ ዘንድ፥ በአዲሱ ሕግ ውስጥ ግዴታ ተደርጎበታል። ስለዚሁ የሶሻልዴሞክራቶቹ ምክርቤተኛ ሞኒካ ግሪፍሃን የሰጡት አስተያየት፥ “........ከእንግዲህ ወዲያ ግልጽ በሆነ ሥርዓት ከምክርቤት፣ ከፈደራዊው መንግሥት እና ከኅብረተሰቡ ጋር በሚደረግ ምክክር አማካይነት፣ ስለ ትኩረት አግጣጫዎች፣ ስለ ወ’ጭ እቀዳ፣ ስለ ስርጭት አካባቢዎችና መንገዶች በመጀመሪያ ሐሳብ እንዲቀርብልን፣ እኛም ይህንኑ እየተወያየንበት ገንቢውን አስተዋጽኦ እንድናበረክት የሚደረግ ይሆናል። እኔ ይህ ጥሩ ነገር ሆኖ ነው የማየው።”

ከ፶ ዓመታት በፊት የተመሠረተው ዶይቸ ቬለ የራዲዮ ስርጭት መርሐግብሮቹን በ፴ ቋንቋዎች ነው የሚያሰራጨው፤ ለቴሌቪዚዮን ስርጭት መርሐግብሩ በ፫ ቋንቋዎች--ማለት በጀርመንኛ፣ በእንግሊዝኛና በእስጳንኛ ነው የሚገለገለው፤ የኢንተርኔት አቅርቦቱም በጣም የሰፋ ነው። በቦንና በበርሊን የሚሠሩት፣ ከስድሳ ሀገሮች የመጡት ባልደረቦቹ ፩ሺ፭፻ ይደርሳሉ። ዶይቸ ሼለ ለመጭው የበጀት ዓመት የተመደበለት የፊናንሱ መንቀሳቀሻ ወደ ፪፻፷ ሚሊዮን ኦይሮ ግድም ነው።