የጀርመን ምርጫ በአዉሮጳ ኅብረት ዕይታ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 21.09.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

 የጀርመን ምርጫ በአዉሮጳ ኅብረት ዕይታ

በጎርጎሪዮሳዊ 2017በተለያዩ የአዉሮጳ ሃገራት ወሳኝ የተባሉ ምርጫዎች ተካሂደዋል። ብሔርተኛ ፓርቲዎች ሰፊ ቦታ ሊያገኙ ይችላሉ ወይም የሩሲያ የኢንተርኔት ጠላፊዎች ጥቃት ሊያደርሱ ይችላሉ በሚል የአዉሮጳ ኅብረት ስጋት ገብቶት ታይቷል። የዶቼ ቬለዋ ቴሪ ሹልዝ እንደምትለዉ ጀርመኑን ምርጫ አስመልክቶ ግን ብራስልስ ላይ ያን ያህል ፍርሃት አይታይም።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:11
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:11 ደቂቃ

ምርጫዉ የአውሮጳዉያንን ትኩረት ብዙም አሳበም፤

የአዉሮጳዋ ባለጠንካራ ኤኮኖሚ እና የፖለቲካ ኃይል ሚዛን ጀርመን፤ ለአዉሮጳ ኅብረት ሕልዉና የሚደራደሩት አንጌላ ሜርክል እና ጥሩ ተናጋሪ የሚባሉት ተፎካካሪያቸዉ ማርቲን ሹልስ የፊታችን እሁድ ለምርጫ ይቀርቡባታል። ምርጫዉ በመላዉ አህጉር መፃኢ ዕድላቸዉ ከጀርመን ጋር መተሳሰሩን የሚያዉቁ አውሮጳዉያንን ትኩረት የሚስብ የፖለቲካ ድራማ በሆነ ነበር። ይህ ግን አልሆነም። ለዚህ ደግሞ መነሻ አለዉ፤ ሜርክል እና ሹልስ በቴሌቪዥን ባካሄዱት ክርክር አንዳቸዉ ከሌላቸዉ የሚለዩበትን ጉዳይ በግልፅ አዉጥተዉ ለመራጮቻቸዉ  ከማሳየት ይልቅ፤  ምንም ልዩነት እንደሌላቸዉ ሁሉ ከክርክር ይልቅ ያካሄዱት «ዉይይት» ነበር የሚል ትችት ተሰምቷል። 
የጀርመን ምርጫ ከወዲሁ በሀገር ዉስጥም ሆነ በዉጭ ተመልካች ሲመዘን ሜርክል ተደላድለዉ የመሪነቱን መንገድ የተያያዙት ነው የሚያስመስለዉ። ይህም ሆኖ የአዉሮጳ ማሻሻያ ማዕከል ባልደረባዋ ሶፊያ ባኽ፤ አሁንም ትኩረት ማግኘት የሚገባቸዉ ጠቃሚ ጉዳዮች እንዳሉ ይናገራሉ።
«ከጀርመን ምርጫ አስቀድሞ አዉሮጳ ዉስጥ የሚካሄድ ክርክር በእርግጥ የለም። እንዲያም ሆኖ ለአዉሮጳ ትርጉም ያላቸዉ ጥቂት ጉዳዮች አሉ። የጀርመን የዉጭ ፖሊሲ ለመጪዎቹ ዓመታት  የሚይዘዉ አቋም እንዴት ያለ ይሆናል? በበርሊን እና በአንካራ መካከል ያለዉ ግንኙነት ባለፉት ጥቂት ቀናት ዉስጥ በፍጥነት ሲበላሽ አይተናል። በዚህም ላይ አሁንም የስደተኞች ቀዉስ እና የአዉሮጳን መከላከያ እንዴት ማጠናከር ይቻላል የሚለዉ ጥያቄም እንዳለ ነዉ።»


ስለስደተኞች ቀውስ ሲነሳ የጀርመን ሚና በመላው አውሮጳ ትኩረትን ከሚስቡ ጉዳዮች አንዱ ነዉ። ምንም እንኳን በጀርመኑ የምርጫ ዘመቻ ላይ ወሳኝ የሚባል ሚና እየተጫወተ ባይሆንም የሜርክል ፖሊሲ አሁንም በቀሪው አዉሮጳ ጠንካራ የክርክር ነጥብ እንደሆነ ነው። ሜርክል ከሚሊየን የሚበልጡ ተሰዳጆች ወደሀገራቸዉ ይግቡ ብለዉ መወሰናቸዉ አንዳንዶች እንደሚገምቱት ዳግም ምርጫ እንዲካሄድ ያደርጋል ተብሎ አይጠበቅም። 
ለመራሄ መንግሥትነት የሚወዳደሩት የጀርመን እጩዎች የቴሌቪዥን ክርክራቸዉን ካካሄዱ በኋላ፤ የዶቼ ቬለ ቴሌቪዥን የብራስልስ ስቱዲዮ ኃላፊ ማክስ ሆፍማን፤ የአዉሮጳ ፓርላማ አባል የሆኑትን የፖላንድ የሕግ እና የፍትህ የበላይነት ፓርቲ አባል ኮስማ ዝሎቶቭስኪን እንግዳዉ አድርጎ ነበር። በወቅቱም ዝሎቶቭስኪ በርካታ ስደተኞች ወደሀገራቸዉ እንዲገቡ የፈቀዱት ሜርክል ብቻቸዉን ነዉ በማለት፤ የአዉሮጳን መርሆዎች የጣሰ ድርጊት ፈፅመዋል ሲሉ ተችተዋል።
እሳቸዉ ይህን ይበሉ እንጂ አየርላንዳዊቷ የአዉሮጳ ምክር ቤት አባል ክርስቲያን ዴሞክራቷ ማይራድ ማክጉኒስ የመራሂተ መንግሥቷ ርምጃ አግባብ አለዉ ሲሉ ይከራከሩላቸዋል።
«ሰብዓዊ ቀዉስ እንዳይፈጠር ለመከላከል ነዉ። እናም በወቅቱ የነበረዉን ሁኔታ ማስተዋል ይኖርብናል። አዉሮጳ ለተፈጠረዉ ዝግጁ አልነበረችም። መራሂተ መንግሥት ሜርክል ያን ከዚያ ውሳኔ ላይ መድረሳቸዉ ትክክለኛ እና በወቅቱ የተደረገ ድፍረት የተሞላዉ ርምጃ ነው ብዬ አስባለሁ። እናም ውሳኔያቸው በሀገር ውስጥ አስቸጋሪ መዘዝ አስከትሏል። »
ስሎቬንያዊቱ የአዉሮጳ ምክር ቤት አባል ታንያ ፋያን በበኩላቸዉ ይህ ጉዳይ የቀሪውን አውሮጳ ችግር አጉልቶ እንደሚያሳይ ነዉ የሚናገሩት። በአውሮጳ ኅብረት ውሳኔዎች ሁሉ የጀርመን ተፅዕኖ ሚዛን መድፋቱንም ያስረዳሉ።
«የወቅቱን እዉነታ ስንመለከት እዚህ የምንወስናቸው ጉዳዮች፤ ብራስልስ ዉስጥ የሚዘጋጁ ፖሊሲዎችም ሁሉ ከበርሊን በስልክ ጥሪ የሚከናወኑ ናቸዉ። ይህ ያለንበት ወቅት እዉነታ ነዉ። የጀርመንን የመሪነት ሚና ደካማነት አይታየኝም፤ በፍፁም። እናም አሁን ወደያዝነዉ ወደሌላኛዉ ዉይይት እንምጣ። ለመሆኑ እንዴት ያለች አውሮጳን ነዉ ለወደፊት የምንፈልገው? ይህ የጀርመን ተፅዕኖ አለ። እርግጥ ነዉ እንፈልገዋለን፤ ሆኖም የጀርመን ብቻ ላይሆነም ጠንካራ አመራር ያስፈልገናል።»
ፋዮን ጀርመናዊ ቢሆኑ ኖሮ በጀርመኑ ምርጫ ለቀድሞ የአውሮጳ ምክር ቤት ፕሬዝደንት ማርቲን ሹልዝ ድምጼን እሰጥ ነበር ነዉ ያሉት። ምክንያታቸዉ ሹልስ ስልጣን ቢይዙ በምሥራቅ እና ምዕራብ አውሮጳ መካከል ያለዉ የኃይል ሚዛን ላይ ያተኩሩ ነበር የሚል ነው። 


ሶፊያ ባኽ ግን በዚህ አይስማሙም። በእሳቸዉ እምነት ሹልስ በአውሮጳ ምክር ቤት ውስጥ ያተረፉትን እውቅና ለመሪነት ለመወዳደር ወደቀረቡባት ሀገራቸው ማሸጋገር አልተሳካላቸዉም። ይህም ምናልባት ለመራሂተ መንግሥቷ መልካም አጋጣሚ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ለጀርመን ዴሞክራሲ ችግር ነዉ ይላሉ፤ 
«ሰፋ አድርጎ ሲታይ በእኔ አመለካከት ይህ ለጀርመን ዴሞክራሲ ችግር ነዉ የሚሆነዉ፤ ምክንያቱም ምንም አይነት ክርክር አይኖርም፤ ለምን ቢባል እጅግ በጣም በጣም ደካማ የሆነ ተቃዋሚ ፓርቲ ብቻ ነዉ ያለዉ፤ በዚም ላይ ሜርክል በጣም ዕድለኛ ናቸዉ፤ በስደተኞች ቀውስ ሳቢያ ተጠናክሮ የወጣዉ ቀኝ ዘመሙ ፓርቲ ፤ በራሱ የውስጥ አመራር ሽኩቻ፤ በዚያም ላይ በአሁኑ የጀርመን ሕዝብ በተገለለ የቀኝ ክንፍ ንግግሮች  ምክንያት ራሱን አዳክሟል። እንዲያም ሆኖ ግን አሁንም ሕዝቡ አመለካከቱን የሚገልፅለት የለም ብሎ ካሰበ እና ሜርክልን የሚተቹ የሚወክለን ሌላ ፓርቲ የለም የሚል ስሜት ካደረባቸዉ በቀላሉ ይህ ቡድን ዳግም ስጋት መሆኑ አይቀርም። »
እናም ባኽ የሜርክል በዚህ ምርጫ ማሸነፍ በወቅቱ ያለዉ ነባራዊ ሁኔታ ዳግም እንዲመለስ የሚሰጠዉ ጊዜ ከአራት ዓመታት አይዘልም። በዚህም ምክንያት ብሔርተኛ ፖለቲከኞች በሌሎች የአውሮጳ መሪዎች ላይ ያሳደሩት ስጋት ፋታ የሚሰጠዉ ለጊዜ ብቻ ነዉ በማለት ያስጠነቅቃሉ።    

 ሸዋዬ ለገሠ /ቴሪ ሹልዝ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች