1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን መንግስት ለዩክሬን ስደተኞች የሚሰጠውን ልዩ ድጋፍ እንዲቀንስ ጥሪ ቀረበ

ዓርብ፣ ሰኔ 14 2016

የጀርመን የጥምር መንግስቱ አጋር የሆነው የነፃ ዴሞክራቲክ ፓርቲ በርመንኛው ምህፃሩ AFD ለዩክሬን ስደተኞች የሚሰጡ ጥቅማ ጥቅሞችን መንግስት እንዲቀንስ ጥሪ አቅርቧል።የሀገሪቱ መንግስት ግን ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል።

https://p.dw.com/p/4hMK5
የጀርመን መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ እና የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቦለድሚር ዘሌንስኪ በጋራ መግለጫ ሲሰጡ
የጀርመን መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ እና የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቦለድሚር ዘሌንስኪ በጋራ መግለጫ ሲሰጡምስል SERGEI SUPINSKY/AFP/Getty Images

ለዩክሬን ስደተኞች የሚሰጡ ጥቅማ ጥቅሞችን መንግስት እንዲቀንስ ጥሪ ቀረበ

 

የጀርመን ጥምር መንግስት አባሉ ነጻ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ኤፍ.ዲ.ፒ.) ለዩክሬን ስደተኞች የሚሰጠው ድጋፍ እንዲቀነስ ጠይቋል። ከዚህ ቀደም በተቃዋሚው ወግ አጥባቂ ክርስቲያን ዴሞክራቲክ ኅብረት (ሲ.ዲ.ዩ.) ይቀነቀን የነበረው ይህ ኃሳብ አሁን በኤፍ.ዲ.ፒ. መነሳቱን ተከትሎ የጀርመን መንግስት እና ቀሪዎቹ ሁለቱ የመንግስት ተጣማሪ ፓርቲዎች ተቃውሞ አሰምተዋል።

በጀርመን የሚገኙ ዩክሬናውያን ስደተኞች በአሁኑ ጊዜ መሰረታዊ የስራ አጥነት ጥቅም በተባለው ማዕቀፍ ውስጥ የሚገኘውን የገንዘብ ድጋፍ ነው የሚያገኙት።

የነጻ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ኤፍ.ዲ.ፒ.) ዋና ጸሐፊ ቢጃን-ዲዬር-ዛራይ በሳምንቱ መጀመሪያ ቢልድ ለተባለው ጋዜጣ በሰጡት ቃለምልልስ፣ “ከአሁን በኋላ የሚመጡ ዩክሬናውያን፣ ስራ ላይ ባለው ሕግ መሰረት ለጥገኝነት ጠያቂዎች የሚሰጠውን ጥቅም ብቻ ማግኘት አለባቸው” ብለዋል። “ይህን ውሳኔ ከተገበርን ሰርተው እንዲያድሩ ልናደርጋቸው እንችላለን” ባይ ናቸው ፖለቲከኛው።

“በሬስቶራንት፣ በኮንስትራክሽን እና በጤና ክብካቤ ዘርፎች የሰራተኛ እጥረት ባለበት ሁኔታ፣ በግብር ከፋዩ ገንዘብ ሰዎች ስራ እንዲሰሩ ማስቻል እንጂ ስራ አጥነትን መደገፍ የለብንም” ሲሉም አክለዋል።የዩክሬን ስደተኞች አያያዝና የስራ ሁኔታ በጀርመንና በሌሎች የአውሮጳ ሀገራት

ከዚህ ቀደም ይህንኑ አቋም ሲያራምድ የቆየው ተቃዋሚው ወግ አጥባቂ ክርስቲያን ዴሞክራቲክ ኅብረት (ሲ.ዲ.ዩ.) ኃሳቡን ሲደግፍ፣ የኦላፍ ሾልስ ሶሻል ዴሞክራት ፓርቲ (ኤስ.ፒ.ዲ.) እና ሌላኛው የጥምር መንግስቱ አባል አረንጓዴ ፓርቲ ግን ኃሳቡን ውድቅ አድርገውታል።

ዩክሬንን ለመደገፍ ሰላማዊ ሰልፍ ያደረጉ የዩክሬን ማህበረሰብ በጀርመን
ዩክሬንን ለመደገፍ ሰላማዊ ሰልፍ ያደረጉ የዩክሬን ማህበረሰብ በጀርመንምስል Roman Chorniuk/DW

የጀርመን መንግስት በሰጠው መግለጫ “የጥምሩ ፓርቲ አቋም የኦላፍ ሾልስን አስተዳደር አይወክልም፤ የዩክሬናውያንን ድጋፍ የመቀነስ ኃሳብም የለም” ብሏል። ይልቁኑ እ.አ.አ. ከ2022 መጀመሪያ አንስቶ የአውሮፓ ኅብረት ስራ ላይ ያዋለውን የዩክሬን ስደተኞች ልዩ ጥበቃ የሚያገኙበትን አሰራር እስከ 2026 ማራዘሙን አስታውቋል። በዚህም መሰረት ዩክሬናውያኑ ስደተኞች በመደበኛው ረጅም የጥገኝነት ማግኛ ሂደት ውስጥ አያልፉም። የመኖሪያ ቦታቸውን መምረጥ ይችላሉ። የገንዘብ ድጋፍ፣ የትምህርት እና የስራ ፈቃድም ወዲያው ማግኘት ይችላሉ።

የዩክሬን-ራሺያ ጦርነትን ተከትሎ በአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት ውስጥ ከሚገኙ ስድስት ሚሊዮን ገደማ የዩክሬን ስደተኞች ውስጥ አንድ ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ገደማዎቹን በማስጠጋት ጀርመን ቀዳሚ ናት። ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ ሴቶች እና ሕጻናት እንደሆኑ የጀርመን መንግስት ባለፈው መጋቢት ወር ያወጣው መረጃ ያሳያል። የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደሚለው ከአጠቃላዩ ዩክሬናውያን፣ 260 ሺህዎቹ ከ18 እስከ 60 ዓመት ያሉ ወንዶች ናቸው።የዩክሬን ስደተኞች አያያዝና የስራ ሁኔታ በጀርመንና በሌሎች የአውሮጳ ሀገራት

በአሁኑ ጊዜ መሰረታዊ የስራ አጥነት ጥቅም በተባለው ማዕቀፍ ውስጥ የሚገኘውን የ563 ዩሮ ወርሃዊ የገንዘብ ድጋፍ በነፍስ ወከፍ የሚያገኙት ዩክሬናውያን ቁጥር ከ700 ሺህ በላይ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ ከ500 ሺህ በላዮቹ ለስራ ብቁ የሆኑ ናቸው።

የዩክሬን ስደተኞች ከሁለት ዓመት በፊት በርሊን ሲደርሱ
የዩክሬን ስደተኞች ከሁለት ዓመት በፊት በርሊን ሲደርሱ ምስል Hannibal Hanschke/Getty Images

የፍሬድሪክ ኤበርት ፋውንዴሽን ጥናት እንደሚያሳየው ግን፣ 18 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው ስራ የጀመሩት፤ ይህም ከጀርመን በመቀጠል ብዙ ዩክሬናውያንን ባስጠጉት ፖላንድ እና ቼክ ሪፐብሊክ ካለው ጋር ሲነጻጸር እጅግ ዝቅተኛ ነው።የዩክሬን ጦርነት በአውሮጳ ያስከተለው የስደተኞች ቀውስ

በስራ ጉዳዮች ላይ ጥናት የሚያደርግ አንድ ተቋም በዩክሬናውያኑ ዙሪያ ባካሄደው ጥናት ደግሞ፣ 90 በመቶ ዩክሬናውያን ስደተኞች ሰርተው ማደር እንደሚፈለጉ አረጋግጫለሁ ብሏል። ነገር ግን ቋንቋውን መናገር ሳይችሉ እንዲሁም የትምህርት እና የስራ ማስረጃዎቻቸው በመንግስት ሳይረጋገጡ ስራ ሊጀምሩ አልቻሉም ይላል ጥናቱ።

አሁን ያለውን ሁኔታ መስመር ለማስያዝም ከሚሰጠው የገንዘብ ድጋፍ ሌላ ስደተኞቹ በፍጥነት ከማኅበረሰቡ ጋር እንዲዋሃዱ የሚያስችሉ መጠነ ሰፊ ፕሮግራሞች ሊተገበሩ እንደሚገባ ምክር አቅርቧል።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።


መሳይ ወንድሜነህ

አዜብ ታደሰ

ፀሀይ ጫኔ