የጀርመን መራሔ መንግሥት የአፍሪቃ ጉብኝት ፍፃሜ | የጋዜጦች አምድ | DW | 26.01.2004
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

የጀርመን መራሔ መንግሥት የአፍሪቃ ጉብኝት ፍፃሜ

የጀርመን መራሔ መንግሥት ጌርሃርት ሽረደር በአራት የአፍሪቃ ሀገሮች የስድስት ቀናት ጉብኝታቸውን አጠናቀው አሁን ወደ ሀገራቸው ተመለሱ። ሽረደር ኢትዮጵያ፡ ኬንያ፡ ደቡብ አፍሪቃና ጋናን በአሁኑ ጊዜ የጎበኙበት ድርጊት አፍሪቃ በጀርመናውያኑ ፖለቲካ ላይ ሁነኛ ቦታ መያዝዋን የሚጠቁም ሆኖ ነው የታየው።

የጀርመን ሶሻል ዴሞክራቶቹ እና የአረንጓዴዎቹ ፓርቲዎች ባንድነት ጥምር መንግሥት ከመሠረቱ ከአምስት ዓመት በኋላ፡ ሽረደር በአውሮጷ በስተደቡብ የሚገኘው ትልቁ አህጉር በጀርመናውያኑ የውጭ ፖለቲካ ላይ አለመረሣቱን ለማጉላት በማሰብ ባለፈው ሣምንት በአፍሪቃ ያደረጉት ጉብኝት እጅግ ዘግይቶ መደረጉን ነው የፖለቲካ ታዛቢዎች የሚናገሩት። ይኸው ጉብኝታቸው ጀርመን በአፍሪቃ አኳያ በምትከተለው መርሕዋ ላይ እርግጥ አንዳችም ተሐድሶ አላሳየም። ይሁን እንጂ፡ ውጤቱ ወደፊት የሚታይ አንዳንድ የአሠራር ለውጥ አስገኝቶዋል። ግብኝቱ አፍሪቃውያንና ጀርመናውያን ሁኔታዎችን በጥሞና መለስ ብለው እንዲገመግሙ ዕድሉን ሰጥቶዋቸዋል። በአዲስ ዘዴ የተዋቀረ አፍሪቃ ይቋቋም በሚል በየጊዜው የሚጎላው ምኞት ገሀዳዊ የሚሆንበት ዕድሉም በምሕፃሩ ኔፓድ በመባል በሚታወቀው ለአፍሪቃ ልማት በተመሠረተው አዲሱ የጉድኝት ትብብር ሂደት የሚለይ ይሆናል። ይኸው የጉድኝት ትብብር አዎንታዊ ውጤት ማስገኘት አለማስገኘቱም ለብዙ አሠርተ ዓመታት በአህጉሩ ሲሠራበት የቆየውን በአንድ ሀገር ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ አለመግባት የተሰኘውን ፖሊሲ ርግፍ አድርጎ በመተዉ ሂደት ላይ ጥገኛ ይሆናል። ይሕንኑ ጥረት ለማሳካት በአህጉሩ ሰብዓዊ መብት የሚከበርበት፡ መልካም አስተዳደር የሚስፋፋበትና ሰላም የሚሰፍንበት ድርጊት ፍቱን በሆነ የቁጥጥር ዘዴ አማካይነት ተግባራዊ እንዲሆን ይጠበቃል። አህጉሩ ይህንን ከላይ የተጠቀሰውን አሠራር ተግባራዊ በሚያደርግበት ጥረቱ ላይ አፍሪቃውያኑ መንግሥታት ፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤ በሚመሩት የዚምባብዌ መንግሥት አኳያ ወደፊት የሚከተሉት ፖሊሲ እንደ መለኪያ ይታያል። የጀርመን ፖለቲካ፡ ምንም እንኳን ጊዜ መፍጀቱ ባይቀርም፡ በአፍሪቅጋዊነት የሚኖረው ፖለቲካዊ አውታር የሚቋቋምበትን ድርጊት የማበረታታት ዓላማ ይዞ ነው የተነሣው። ብዙ አፍሪቃውያን መንግሥታት ገና ዴሞክራሲያዊ ሂኢደቶችን ሳያሟሉ በፊት በአህጉሩ እንደ ተስፋ ሰጪ ሀገሮች ሲቆጠሩ ይታያል። ለምሳሌ፡ ጀርመን ትልእእቅ ትኩረት በሰጠቻት ኬንያ ውስጥ የሀገሪቱ ሕዝብ ፕሬዚደንት ምዋይ ኪባኪ የሚመሩት ጥምር መንግሥት በምርጫ ዘመቻ ወቅት ዴሞክራሲያዊ ሂደቶችን ለማንቀሳቀስ የገባውን ቃል እንዲያሟላ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል። ሽረደር በመጀመሪያ በጎበኙዋት ኢትዮጵያም ውስጥ ቢሆን የሰብዓዊ መብት እና የፕሬስ ነፃነት ይዞታ ያን ያህል የሚሰመሰገን አይደለም። ይሁንና፡ አፍሪቃ ረሀብን፡ ጦርነትን፡ የተፈጥሮ አሳባቢ ውድመትን፡ ወዘት፡ ከመሳሰሉ ችግሮች ለመላቀቅ፡ እንዲሁም፡ በአህጉሩ ውዝግቦችን ለማስወገድና ከተቻለም መፍትሔ ለማስገኘት በምታደርገው ጥረታ ላይ የጀርመን ድጋፍ እንደማይለያት የጌርሃርት ሽረደር ጉብኝት አጉልቶዋል።