የጀርመን መራሒተ መንግሥት የአፍሪቃ ጉብኝት | አፍሪቃ | DW | 08.10.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የጀርመን መራሒተ መንግሥት የአፍሪቃ ጉብኝት

የጀርመን መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ለሶስት ቀናት ጉብኝት የፊታችን እሁድ ወደ ሳህል አካባቢ ሀገራት ይጓዛሉ። ጉብኝታቸው በዋነኝነት ስደተኞች በብዛት ወደ አውሮጳ እየመጡ ባለበት ሁኔታ በተፈጠረው ቀውስ ላይ ያተኩራል።  ሜርክል ከአፍሪቃ ጋር ባለው ግንኙነት ላይ አዲስ አሰራር ለመፍጠር ይፈልጋሉ። 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:19
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
10:19 ደቂቃ

የሜርክል የአፍሪቃ ጉዞ

አንድ የጀርመን መራሒ መንግሥት ወደ ማሊ ሲጓዝ አንጌላ ሜርክል የመጀመሪያዋ ይሆናሉ።  ኒጀር እና ኢትዮጵያም በመራሒተ መንግሥቷ ጉዞ የተካተቱ ሌሎቹ ሀገር ናቸው።  አንጌላ ሜርክል ገና ጉዟቸውን ሳይጀምሩ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ የአውሮጳ ህብረት መረጋጋት በአፍሪቃ ከሚታየው ሂደት ጋር በቀጥታ ጥገኛ ነው። አውሮጳውያኑ ለአፍሪቃ የሚሰጡትን የልማት ርዳታ ማሳደግ እና ከአህጉሩ ጋር የሚያደርጉትን የልማት ትብብር በአዲስ መልክ ማቀናጀት እንደሚኖርባቸው፣ እንዲሁም፣  በአፍሪቃውያቱ ሀገራት ውስጥ የሚያንቀሳቅሱትን ወረትም ሊያጠናክሩት እና አፍሪቃውያኑ መንግሥታት መልካም አስተዳደርን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጫና ሊያሳርፉ እንደሚገባ ነው ሜርክል ያስታወቁት። መራሒተ መንግሥቷ ይህን ያሉት ባለፈው ረቡዕ በርሊን ላይ ለተካሄደው የትልቆቹ እና የውጭ ንግድ ፌዴራዊ ማህበራት ስለ ጀርመን አፍሪቃ ፖሊሳቸው ባሰሙት ንግግር ላይ ነበር።     
የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር የመራሒተ መንግሥቷን ጉብኝት ለማዘጋጀት ቀደም ባሉ ወራት ወደ ማሊ እና ወደ ኒጀር ተጉዘው ነበር።  የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች እንደሚያሳዩት፣ ከምዕራብ አፍሪቃ ወደ አውሮጳ ለመግባት የሚሞክሩ ብዙዎቹ ስደተኞች  ማሊ እና ኒጀር ን መተላለፊያ አድረገዋቸዋል። ሁለቱም የምዕራብ አፍሪቃ ሀገራት የዓለም አቀፉ ሽብርተኝነት ሰለባ ናቸው። በሰሀራ አካባቢ ሀገራት ውስጥ እና በኩል የሚንቀሳቀሰው በእገታ እና ሕገ ወጡ የአደንዛዥ ዕፅ ንግድ የሚገኘውን ገቢ አል ቃይዳ የመሳሰሉ አሸባሪ ድርጅቶች እኩይ ተግባራቸውን ማራመጃ አድርገው ሲጠቀሙበት ይታያል።


የአሸባሪዎች ተግባር በአካባቢው ፀጥታ ላይ ከደቀነው ትልቅ ስጋት በተጨማሪ፣ እጎአ መጋቢት 2012 ዓም ላይ በማሊ የተካሄደው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት በሀገሪቱ አለመረጋጋት አስከትሎዋል። በማሊ የፖለቲካው አለመረጋጋት፣ የማያስተማምነት የሀገሪቱ ፀጥታ እና የምግብ እና የመጠጥ ውሀ እጥረት በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ የሀገሪቱ ዜጎች ሀገራቸውን ለቀው እንዲሰደዱ ገፋፍቷቸዋል። በጎረቤት ማሊ ያለው ሁኔታም ከማሊ የተለየ አይደለም። በሰሜናዊ ናይጀሪያ የሚንቀሳቀሰው ዓማፂ ቡድን ቦኮ ሀራምን የመሳሰሉ አሸባሪ ቢድኖችም በኒጀር ጥቃታቸውን አጠናክሮዋል። ከትናንት በስቲያ እንኳን ማንነታቸው በግልጽ ባልታወቁ አሸባሪዎች በደቡብ ኒጀር የሚገኝ አንድ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ አጥቅተው 22 የመንግሥቱን ወታደሮች ከመግደላቸው ሌላ፣ ብዙ የጦር መሳሪያ እና የጦር ኃይሉን ተሽከርካሪ ይዘው መሸሻቸው ተመልክቶዋል። የሸማቂዎቹ ማንነት በግልጽ ባይታወቅም፣ በሚገባ ታቅዶ ከተካሄደው ጥቃት በስተጀርባ ከማሊ የሄዱ የቱዋሬግ ዓማፅያን ሳይሆኑ እንዳልቀረ የዓይን እማኞች ገልጸዋል።  ይህን ዓይነቱ ተደጋጋሚ ጥቃትም ያካባቢው ሕዝቦች ከቀያቸው መፈናቀልን እና ወደ አውሮጳም መሰደድን ያባባሰ ሌላ ዋና ምክንያት ነው።
ፍልሰት፣ የተለመደ አማራጭ 
በሜድትሬንየን ባህር በኩል ከአፍሪቃ ወደ አውሮጳ የሚታየውን ፍልሰት የጀርመን መንግሥት እና ህብረተሰብ ካለፉት ጊዚያት ወዲህ  በቅርብ የሚከታተለው ጉዳይ መሆኑን ከዶይቸ ቬለ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት መንበሩን በርሊን ያደረገው ሽቲፍቱንግ ፊውር ፖሊቲክ ኡንድ ቪስንሻፍት» የተባለው የፖለቲካ ጥናት ተቋም ባልደረባ ዴኒስ ቱል አስረድተዋል። 
«  የአንጌላ ሜርክል ጉዞ በርግጥ ከፍልሰቱ ጉዳይ ጋር የተያያዘ ነው፣ እንደሚታወቀው፣ ይኸው ርዕስ በመላ ጀርመን ሀገር ውስጥ በወቅቱ በጣም ትልቅ ትኩረት አግኝቷል። »
እንደ ዴኒስ ቱል ትዝብት ለምዕራብ አፍሪቃ ሀገራት ፍልሰት አዲስ ክስተት ሳይሆን እንደ አማራጭ የተያዘ የተለመደ ክስተት ነው።
« በማሊ እና በሴኔጋል ፍልሰት ከብዙ ምዕተ ዓመታት ወዲህ የሚታይ ክስተት ነው፤ ማሊ ቀውስ ውስጥ ሳትወድቅ በፊት ጀምሮ ማለት ነው። በነዚህ ሀገራት ውስጥ ፍልሰት እንደ ማህበራዊ ባህላዊ ደንብ እውን ሲሆን የሚታይ የተለመደ ሂደት ነው። ይኸው ደንብ የአንድ ግለሰብን ለአካለ መጠን መድረስ የሚያረጋግጥ መታወቂያ ዓይነት ሆኖ ነው የሚወሰደው። እና፣ ይህን የኖረ አሰራር በጠቅላላ ማስወገድ አይቻልም። »

በሳህል አካባቢ ሀገራት እና በአውሮጳ መካከል በሁሉም ዘርፎች ያለው ልዩነት ግዙፍ በመሆኑ የሰዎች ወደ አውሮጳ የመፍለስ ፍላጎት ወደፊትም ሊገታ እንደማይችል፣ የልማት ትብብርም ቢሆን ፍልሰትን ለማስቆም ድርሻ እንደማያበረክት ነው ዴኒስ ቱል ያመለከቱት፤  የልማት ትብብሩን በማጠናከር ምናልባት የፍልሰትን መጠን መቀነስ ይቻል ይሆናል ባይ ናቸው። 
የልማት ትብብር ማጠናከርም የጀርመን መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል እቅድ ሳይሆን አልቀረም።  ከአፍሪቃ ሀገራት ጋር የተጀመሩ የልማት ትብብር ፕሮዤዎችን፣ ማለትም፣  በመሰረተ ልማት ግንባታ ማስፋፋቱ ስራ ላይ መሳተፍ፣ የሙያ ስልጠና  መስጠት እና የስራ ቦታ ፈጠራን ማበረታታት የጀርመን እቅድ መሆኑ ከመራሒተ መንግሥቷ ጽሕፈት ቤት ተሰምቶዋል።  ይሁንና፣ በዚሁ የሜርክል ጉብኝት የኤኮኖሚ የልዑካን ቡድን አብሮ አይጓዝም፤ ምክንያቱም፣ እንደ ቱል ገለጻ፣ ጀርመን በተለይ ከማሊ እና ከኒጀር ጋር በኤኮኖሚው ዘርፍ የምታደርገው ግንኙነት ያን ያህል አልዳበረም።
የጦር ሰፈር በኒጀር
በዚህ ፈንታ ግን ጀርመን የሳህል አካባቢን ለማረጋጋት በወታደራዊ ርምጃ የራሷን ድርሻ ልታበረክት እንደምትችል ዴኒስ ቱል ገልጸዋል። በመሆኑም፣ ጀርመን በኒጀር ማዕከል አንድ የራሷን ጦር ሰፈር ታቋቁማለች። ይኸው የጦሩ ሰፈር በጎረቤት ማሊ የተሰማራውን እና የጀርመን ወታደሮችም የተሳተፉበትን በምህፃሩ  « ሚኑስማ» በመባል የሚታወቀውን የተመድ ሰላም አስከባሪ ጓድ የመደገፍ ሚና እንደሚጫወት በጀርመናውያኑ የአድናወር የፖለቲካ ጥናት ተቋም ፣ ከሰሀራ በስተደቡብ ያሉ ሀገራት መልካም አስተዳደርን እና ፀጥታ ጉዳይ ተመልካች ኦዝዋልድ ፓዶኑ አመልክተዋል።
« በሳህል አካባቢ የጀርመን ወታደራዊ ትሳትፎ የማጠናከሩ ድርጊት ጀርመን በአፍሪቃ ያላትን አቋም በማሳደጉ ረገድ ትልቅ መሻሻል ነው። ጀርመን በአፍሪቃ ይዛው የቆየችው አቋም ያን ያህል የጎላ አይደለም። ይሁንና። ጀርመን በአውሮጳ ጠንካራ የኤኮኖሚ ኃያል መንግሥት ብቻ ሳትሆን፣ ወደፊት በተመድ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ውስጥ ቋሚ መንበር የመያዝ ዓላማም እንዳላት ይታወቃል። በዚህም የተነሳ ጀርመን በዓለም አቀፍ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ፣ በተለይ የፀጥታ ጥያቄዎች ዋነኛ ቦታ በያዙባት አፍሪቃን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ሚና መጫወት መቻል ይኖርባታል። »


መልዕክት ለሜርክል መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል በመ/ጨረሻ የሚጎበኙዋት በመብት ጥሰት ጠንካራ ትችት የሚሰነዘርባትን  ኢትዮጵያ ናት። ሜርክል በዚያ በአፍሪቃ ህብረት ቅጥር ግቢ ውስጥ በጀርመን የገነዘብ ድጋፍ የተገነባውን  በቀድሞው የታንዛንያ ፕሬዚደንት ጁልየስ ኔሬሬ ስም የሚጠራውን የህብረቱን የሰላም እና ፀጥታ ምክር ቤት ሕንፃ መርቀው ይከፍታሉ። በወቅቱ በኢትዮጵያ ካለፉት በርካታ ወራት ወዲህ ስለቀጠለው ተቃውሞ ከኢትዮጵያ መንግሥት እና ከሲቭል ማህበረሰብ ጋር እንደሚወያዩ ተገልጿል። ባለፈው እሁድ በቢሾፍቱ በኢሬቻ በዓል ወቅት የበርካቶች ሕይወት የጠፋበትን ድርጊት በመቃወም በጀርመን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን  ባለፈው ረቡዕ በመራሒተ መንግሥቷ ጽሕፈት ቤት ባካሄዱት ተቃውሞ ላይ አንጌላ ሜርክል  በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫና እንዲያሳርፉ ጥሪ አስተላልፈዋል።  
  
« በኢትዮጵያ በየቀኑ ሰዎች ይሞታሉ። ይሁንና፣ በአሁኑ ጊዜ ራሳቸውን ለመከላከል፣ ተጠያቂ የሆኑ የመንግሥት ባለስልጣናትን ለማንሳት፣ ተቃውሞ በማድረግ እና መንገዶችን በመዝጋት  ርምጃ በመውሰድ ላይ ናቸው። ካላንዳች ርምጃ ተተኩሶብህ የምትሞትበት ጊዜ አይደለም። እንዲያውም፣ ባንዳንድ አካባቢዎች አስተዳደሩን ይዘዋል። አውሮጳ ይህን ልትረዳው ይገባል። የኢትዮጵያን መንግሥት ካሁን በኋላ መደገፍ አይቻልም። »

ማርቲና ሺቪኮቭስኪ/አርያም ተክሌ

ነጋሽ መሀመድ
   
 

Audios and videos on the topic