የጀርመን መራሂተ መንግስት የአፍሪቃ ጉዞ | አፍሪቃ | DW | 02.10.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የጀርመን መራሂተ መንግስት የአፍሪቃ ጉዞ

የጀርመን መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ሀገራቸው በኢንዱስትሪ የበለጸጉትን የስምንት ሀገሮች ቡድን ወቅታዊ ፕሬዚደንትነትን ስልጣን በያዘችበት በአሁኑ ወቅት ከአፍሪቃውያን ጋር ግልጹን ውይይት ለማካሄድ ቆርጠው ተነስተዋል።

አንጌላ ሜርክል

አንጌላ ሜርክል

ሜርክል ይህንኑ ውይይት እአአ ከነገ ጥቅምት ሶስት እስከ ፊታችን እሁድ ጥቅምት ሰባት ድረስ አፍሪቃን ለመጀመሪያ ጊዜ በሚጎበኙበት ጉዞዋቸው ያካሂዳሉ ተብሎ ይጠበቃል። ሜርክል በዚሁ ጉዞቸው የሚጎበኙዋቸው ሶስት ሀገሮች ኢትዮጵያ፡ ደቡብ አፍሪቃ እና ላይቤሪያ ናቸው።
በብዙ አፍሪቃውያን መንግስታት ውስጥ መሻሻልና አዳዲስ ዕድል ማየታቸውን የገለጹት ሜርክል በአህጉሩ በመጀመሪያ የሚጎበኙዋቸው ሀገሮችም ተሀድሶ ለውጥ ያነቃቁ ከጀርመን ጋር ጠንካራ የጀርመን የኤኮኖሚ ተጓዳኝ የሆነችው ደቡብ አፍሪቃ፡ ለአህጉሩ ሰላምና ዴሞክራሲ ለማስገኘት የሚጥረው የአፍሪቃ ኅብረት መንበር የሆነችው ኢትዮጵያ እና ከብዙ ዓመቱ የርስበርስ ጦርነት መዘዝ በቁርጠኛ ርምጃ የተላቀቀችው ላይበሪያ ናቸው። የፖለቲካ በጎ ፈቃድና ይህንኑ የሚያስፈጽሙ ተቋማት እሳሉ ድረስ ለአህጉሩ የሚሰጠው የልማት ርዳታ ጥሩ ውጤት እንደሚያስገኝ ጀመናዊትዋ መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል በሙሉ እምነት ይናገራሉ።
« ድህነትን መታገሉ ትልቁ ተግባር ነው። ይህም የልማቱን ትብብር ይጠቅማልና። ድህነትን ለመታገል የሚያስችሉ ፕሮዤዎችን፡ ለዚሁ ተግባር አስፈላጊ የሆኑ መዋቅሮችንና አውታሮችን ሳናዘጋጅ በምናነቃቃበት ጊዜ፡ የፈለገውን ያህል ገንዘብ ብናፈስበትም ድህነትን በርግጥ ማስወገድ እንደማንችል ከተሞክሮአችን ልንረዳው ችለናል። ሀገራቱ በከፋ ሙስና የተዘፈቁ ከሆነና ገንዘቡም ትክክለኛ ላልሆነ ፕሮዤ ከወጣ የሚያስገኘው ውጤት አይኖርም። የሕዝቦቻቸውን (ከድህነት የተላቀቀውንም) መብት የሚያከብሩ፡ በልማት ርዳታ የሚቀርበውን ገንዘብም የማያጠፉ ሀገሮች ብቻ ናቸው ድህነትን ለዘለቄታው ሊታገሉ የሚችሉት። »
በቆራጥዋና በዴሞክራሲያዊው መንገድ በተመረጡት ፕሬዚደንት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ የምትመራው ላይቤሪያ፡ እንዲሁም፡ ደቡብ አፍሪቃ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና ለሕግ የበላይነት ከፍተኛ ትርጓሜ ሰጥተው በመከተላቸው በአህጉሩ እንደ ጥሩ የተሀድሶ ለውጥ ምሳሌ ይጠቀሳሉ። እነዚህ ሀገሮች ወደፊት ከሌሎቹ ሀገሮች ሁሉ የልማቱ ትብብር ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ሜርክል አስረድተዋል።
መልካም አስተዳደርና የፖለቲካ ተሀድሶ የአፍሪቃ ኅብረት በግልጽ ያስቀመጣቸው ዓላማዎች ናቸው። በመሆኑም፡ ሜርክል የአፍሪቃ ጉብኝታቸውን የሚጀምሩት ለቡድን ስምንት፡ እንዲሁም፡ ለአውሮጳ ኅብረት ዋነኛ የውይይት ተጓዳኝ የሆነው ይኸው ተቋም መንበር በሚገኝባት አዲስ አበባ፡ ኢትዮጵያ ነው። ሜርክል ነገ በአዲስ አበባ ከአፍሪቃ ኅብረት ተወካዮች ጋር በሚያደርጉት ውይይት ላይ ከሚያነሱዋቸው ጉዳዮች መካከል በሶማልያ፡ ሱዳንና በቻድ የቀጠለው ውዝግብ ይገኙበታል። በዚሁ አኳያ ጀርመን፡ ኡተ ሼፈር እንደዘገበችው፡ በአንድ የጋራ የአውሮጳ የውጭና የጸጥታ ፖለቲካ ፖሊሲ አማካይነት ተጨማሪ ኃላፊነት መውሰድ ይኖርባታል።
በኢንዱስትሪ የበለጸጉትን የቡድን ስምንት ፕሬዚደንትነት ስልጣን የያዘችውና ለአፍሪቃም ልዩ ትኩረት እንደምትሰጥ ያስታወቀችው የጀርመን መንግስት በቡድን ስምንት ጉባዔ ላይ ቃል መግባት ብቻ ሳይሆን፡ ይህንኑ ቃሉን በተግባር ለመተርጎም ዕቅድ አለው። በዚሁ መሰረት ጀርመን ለአፍሪቃ የምትሰጠው የልማት ርዳታ እአአ በ 2008 ዓም በ 750 ሚልዮን ዩሮ ከፍ ይላል። ጀርመን የተከተለችው የአፍሪቃ ፖለቲካ እስከዛሬ ድረስ በልማቱ ፖለቲካ ላይ ብቻ የተወሰነ ነው፤ ይህ፡ በሜርክል አስተያየት መቀየር አለበት። ይህንን ብዙዎች በተለይ ቻይና ከተገነዘቡት ቆይቶዋል። አፍሪቃ ከሚመጣው የጸጥታ ስጋት ጎን አህጉሩ የሚከፍተውን ዕድል፡ ለምሳሌ እንደ ኃይል ምንጭ አቅራቢ፡ የወደፊቱ የስራ ገበያ፡ ለጀርመናውያን ተቋማት እንደማምረቻ ቦታም ማየት አስፈላጊ መሆኑን ነው መራሂተ መንግስትዋ የአፍሪቃ ጎዞአቸውን ሊጀምሩ ጥቂት እንደቀራቸው ያሳሰቡት። ቻይና በጥሬ አላባ ከበለጸጉት የጎረቤት አፍሪቃ ሀገሮች ጋር የጀመረችው ግንኙነት አውሮጳ በአጽንዖት ነው የምትመለከተው። አውሮጳና ቻይና አፍሪቃ ውስጥ ባንድነት እንድትሰራ ሜርክል ያቀረቡት ሀሳባቸው እስካሁን ከቻይና አንዳችም ምላሽ አላገኘም።
«ከቻይና ጋር ያለውን የቻይና ግንኙነትን በስጋት ነው የምንመለከተው፤ ምክንያቱም፡ ከአፍሪቃ የሚገዛው ጥሬ አላባ በትክክለኛ መንገድ አይሰራበትም ብለን እናምናለንና። በመሆኑም፡ ወደፊት በአፍሪቃ የሚነቃቁ ፕሮዤዎች በሚታቀዱበት ጊዜ እኛም እኩል የመፎካከር ዕድል ቢኖረን ጠቃሚ ሊሆን ይችል ይሆናል። »
አፍሪቃውያኑ የሜርክል የውይይት ተጓዳኞች ለየት ያለ አመለካከት ነው ያላቸው። ቻይና የጀመረችውን ታታሪነት ለአህጉሩ ኤኮኖሚ መነቃቃት አዲስ ኃይል የሚሰጥ አድርገው ስለሚመለከቱት በደስታ ነው የተቀበሉት። የሜርክል የአፍሪቃ ጉዞ እስካሁን ግልጽ ያልሆነው፡ በአህጉሩ አኳያ ተጓድሎ የቆየው ትኩረትና ሁነኛ የውይይት ተጓዳኝ ያልነበረበት የጀርመንና የአፍሪቃ ፖሊሲ ግልጽ መልክ ሊያስይዘው እንደሚችል ይታመናል። ለዚህም፡ የጀርመን ፕሬዚደንት ሆርስት ከለር በተደጋጋሚ፡ እንዲሁም፡ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ባለፈው ነሀሴ ወር ወደ አፍሪቃ ያደረጉዋቸው ጉዞዎች መንገዱን አስተከክለዋል።