1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን ሕገ-መንግስት 70ኛ ዓመት

ማክሰኞ፣ ግንቦት 13 2011

"ጊዜያዊ ነው" ተብሎ የታወጀው የጀርመን ህገ መንግስት ቋሚ ሆኖ 70ኛውን ዓመት በዚህ ዓመት እያከበረ ነው። በምዕራቡ ጀርመን ያኔ የታወጀው ህገ መንግስት ዲሞክራሲ እና ሰላምን፣ ብልጽግናን እና ነጻነትን ለጀርመን አምጥቶ ይቺን ሀገር በ70 ዓመት ጊዜ ውስጥ ትልቅ ደረጃ ላይ አድርሷታል። 

https://p.dw.com/p/3IqgI
Deutschland 70 Jahre Grundgesetz | Grundgesetz mit Konfetti
ምስል Imago Images/C. Ohde

የጀርመን ሕገ-መንግሥት 70ኛ ዓመት

ጀርመናውያን በጎርጎሮሳዊው 1949 ያጸደቁትን ህገ መንግስት ጊዜያዊ ነው ያሉት በአንድ ምክንያት ነበር። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ለሁለት የተከፈሉት ጀርመናውያን ምናልባት አንድ ቀን፣ ከውህደቱ በኋላ፣ ቋሚ የጋራ ህገ መንግስት ለማውጣት ሀሳብ ስለነበራቸው ነው።

መሰረታዊ የሆኑ የሰብዓዊ እና የዲሞክራሲያዊ መብቶች በጎርጎሮሳዊው 1949 ሲታወጅ የመጀመሪያው ጊዜ አይደለም። ፋሽስቶቹ ስልጣን ላይ ሳይወጡ ቀደም ሲል፣ የቫይመር ሪፐብሊክ ዘመን ተብሎ ከሚታወቀው የንጉስ አገዛዝ በኋላ የዲሞክራሲ መብቶች በሀገሪቱ ታውጀው ነበር። ያ የዲሞክራሲ ስርዓት ግን ፋሽስቶቹን ስልጣን ላይ እንዲያውጡ ሊያግዳቸው አልቻለም። 

የህግ ምሁሩ ፕሮፌሰር ኡልሪሽ ባቲስ እንደሚሉት ይህ ሊሆን የቻለው ህገመንግስቱ ይህን ለመከላከል ደካማ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን ለህገ መንግስቱ መከበር ተነስተው የሚዋደቁ እና ለእርሱም መኖር የሚታገሉ ዲሞክራቶች ቁጥር ትንሽ ስለነበር ነው። በዲሞክራቶቹም መካከል ስምምነት አልነበረም። ያም ለቀጣዩ ትውልድ ትምህርት ሰጥቷል።ይህ ሁኔታ ተመልሶ እንዳይደገም አዲሱ የጀርመን ህገመንግስት በጎርጎሮሳዊው 1949 ሲታወጅ በተለይ የርዕሰ ብሔሩን  ማለት የፕሬዝዳንቱን ስልጣን ውስን አድርጓል። ህገ መንግስቱ ጠቅላላ የሀገሪቱን አመራር በተለያዩ አካሎች ስር ሸንሽኖ እና አከፋፍሎ አንዱ አካል እንዲሁም የሀገሪቱን ባለስልጣኖች እንዲቆጣጠር አድርጎት አልፏል። 

Grundgesetz
ምስል picture_alliance/dpa/Bildfunk/ZB/M. Skolimowska

የጀርመን ህገ መንግስት በዘር ጥላቻ እና በዘር ርዕዩተ ዓለም ላይ ተመስርቶ የነበረውን የፋሽስቶች ስርዓት ተመልሶ እንዳያንሰራራ ለማገድ በደንብ ታስቦበት የተነደፈ ቋሚ ህግ ነው። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የኮሚዩኒስቶቹ አምባገነን ስርዓት በመላው ጀርመን ተስፋፍቶ ስልጣኑን እንዳይዝ ገደብ ያበጃል።

ለሰብዓዊ መብቶች እና ለሰው ልጅ ክብር ዕውቅና የሚሰጠው የጀርመን ህገ መንግስት ከጸደቀ ሰባት አስርትን ደፍኗል። ሰባ ዓመት ለአንድ ሰው ረጅም ዕድሜ ነው። በአንድ ህዝብ ረጅም ታሪክ ውስጥ ግን ሰባ ዓመት ይህ እንደ አይን ጥቅሻ ያህል በጣም ትንሽ ነው። ያም ሆኖ ይህ በምዕራቡ ጀርመን ያኔ የታወጀው ህገ መንግስት ዲሞክራሲ እና ሰላምን፣ ብልጽግናን እና ነጻነትን ለጀርመን አምጥቶ ይቺን ሀገር በ70 ዓመት ጊዜ ውስጥ ትልቅ ደረጃ ላይ አድርሷታል። 

 ሙሉ መሰናዶውን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ። 

ይልማ ኃይለሚካኤል

ተስፋለም ወልደየስ