«የጀርመን ለአፍሪቃ ሽልማት» አሸናፊ ኒኮላስ ኦፕዮ  | አፍሪቃ | DW | 24.11.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

«የጀርመን ለአፍሪቃ ሽልማት» አሸናፊ ኒኮላስ ኦፕዮ 

ዩጋንዳዊው የሰብዓዊ መብቶች ጠበቃ ኒኮላስ ኦፒዮ የዘንድሮውን «የጀርመን ሽልማት ለአፍሪቃ»  ትናንት ከጀርመን ፕሬዝዳንት ከፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ተቀበሉ። ሽልማቱ  የጀርመን መንግሥት ለዲሞክራሲ፣ ለሰላም ፣ለሰብዓዊ መብቶች ፣ለጥበብ ፣ለባህል እንዲሁም ለማህበራዊ ገበያ ምጣኔ ሀብት የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አፍሪቃውያን የሚበረከት ነው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:29

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ዩጋንዳዊው ኒኮላስ ኦፕዮ

 

የጎርጎሮሳዊው 2017 «የጀርመን ሽልማት ለአፍሪቃ»  አሸናፊ ኒኮላስ ኦፒዮ የሰብዓዊ መብቶች ጠበቃ እና «ቻፕተር ፎር ፣ዩጋንዳ» የተባለው የሰብዓዊ መብቶች ተከራካሪ ድርጅት መሥራች ናቸው። የዛሬ 12 ዓመት በመሰረቱት በዚህ ድርጅት አማካይነት በዩጋንዳ ለሲቪሎች ነጻነት እና ለሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ያለመታከት ይሰራሉ።  የ37 ዓመቱ ታዋቂው ጠበቃ ኦፕዮ ሌሎች ባልደረቦቻቸው በፍርሃት የማይነኳቸውን ብዙም የማይደፈሩ ጉዳዮችን በማንሳት ይታወቃሉ።  በጥብቅ ከሚተቿቸው ጉዳዮች ውስጥ የሀገሪቱ የምርጫ ህግ፣ የተገደበው የመሰብሰብ ነጻነት  እንዲሁም የታፈነው የመናገር እና የፕሬስ ነጻነት ይገኙበታል። ኦፕዮ የሲቪል መብቶችን ጥበቃ እና ፖለቲካዊ ተሳትፎን በሚመለከቱ ታዋቂ ፍርድ ቤቶች ትልቅ ሚና ይጫወታሉ።ይህም በዩጋንዳ ተሰሚነት ካላቸው ሰዎች አንዱ አድርጓቸዋል። ጀርመን ለአፍሪቃውያን ለምትሰጠው ለዚህ ሽልማት ያበቃቸውም  ይህ ተግባራቸው መሆኑን ትናንት ሽልማቱ በርሊን ውስጥ በተበረከተበት ስነ ስርዓት ተገልጿል። የሽልማቱ ዳኞች ሊቀመንበር ፎልከር ፌይግል ፣ እንዳሉት ኦፕዮ በተሰማሩበት የሰብዓዊ መብቶች ጥብቅና ለህብረተሰቡ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ትልቅ ስፍራ አለው።
«ኒኮላስ ኦፕዮ ምንም እንኳን ከፍተኛ ተቃውሞ ጥላቻ እና ማስፈራሪያ ቢደርስባቸውም ከቆሙለት ዓላማ ዝንፍ ሳይሉ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ሲያገለግሉ የቆዩ ልዩ ሰው ናቸው ። «ቻፕተር ፎር ኡጋንዳ» በተባለው ድርጅታቸው ውስጥ ለሚሰሩ ባልደረቦቻቸው አርአያ ሆነዋል። ያለመታከት የወደፊቱ ጊዜ የተሻለ እንደሚሆን ባላቸው እምነት ተስፋ ባለመቁረጥ ለተሻለች ዓለም በንቃት ታግለዋል።» 

ትናንት ሽልማቱን በበርሊን ውስጥ ለኦፕዮ ያበረከቱት የጀርመን ፕሬዝዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ባሰሙት ንግግርም የኦፕዮን አርአያነት አጉልተዋል። ኦፕዮ በአፍሪቃ አዲስ ለውጥ በማምጣት ለሌሎች አርአያ መሆናቸውን የተናገሩት ሽታይንማየር ተግባራቸው በአውሮጳ የአፍሪቃን ገጽታ መቀየር መቻሉንም ገልጸዋል።
«ከሁለት ዓመት በፊት ዩጋንዳ በነበርኩበት ወቅት በሀገርዎ ያሉትን ችግሮች ፣ግዙፍ ፈተናዎች እና መከናወን ያለባቸውን ተግባራት በአይኔ ለመመልከት ችያለሁ። መሻሻል እንዳለም እንዲሁ አይቻለሁ ። ይህ ግን አቶ ኦፕዮ ያለ እርስዎ እና ያለ ሥራ ባልደረቦችዎ የሚታሰብ አልነበረም። እድሜ ለርስዎ ባደረጉት አስተዋጽኦ በአውሮጳ ስለ አፍሪቃ ያለው አመለካከት እየተለወጠ ነው። አፍሪቃ ከአሁን በኋላ ጨለማዋ ክፍለ ዓለም አይደለችም። አውሮጳም ቀስ በቀስ አፍሪቃ ቀውሶች ያሉባት ክፍለ ዓለም ብቻ አለመሆንዋን እየተረዳ ነው። ተስፋ፣ እድገት፣ እና በአንዳንድ ሁኔታዎች አስደናቂ አዎንታዊ ለውጦች የሚታዩባቸው ቦታዎች አሉ።»
የኦፕዮ ዐብይ ተግባር ሥልጣን በአንድ ወገን ብቻ በተያዘበት በዩጋንዳ ህገ መንግሥታዊ ሥርዓት እና የህግ የበላይነት እንዲከበር መታገል ነው። ያደጉት ከሰሜን ዩጋንዳዋ ጉሉ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኝ አካባቢ ነው። አካባቢው የዩጋንዳ መንግሥት እና ራሱን «የጌታ ተከላካይ ጦር» በምህጻሩ LRA ብሎ የሚጠራው አማጺ ቡድን የውጊያ ማዕከል ነበር። አማጺው ኤል.አር.ኤ ህጻናትን በውትድርና በማሰልፍ እና በማሸበር ይታወቃል። እህታቸው በድርጅቱ ታግታ ነበር። ኦፕዮ ይህን እያዩ ማደጋቸው የሰብዓዊ መብት ጠበቃ ለመሆን እንዳበቃቸው ይናገራሉ።
«በህግ ያገኘሁትን ዲግሪ እና ሥልጠና ለተገፉ እና በህብረተሰቡም ውስጥ ጥሩ እድል ላልገጠማቸው ሰዎች  መብቶች ጥብቅና ለመቆም እጠቀምበታለሁ። የሰዎችን ህይወት የተሻለ ማድረግ የወደቁትን መደገፍ፣ መብታቸው የተገፈፈውን በማገዝ ሙሉ አቅማቸውን እንዲጠቀሙ ማድረግ ሁል ጊዜም ለስራ ያነሳሳኛል። ሀገራችንን ይበልጥ ዴሞክራሲያዊ እንደምትሆን እና ሁሉም በህግ ፊት እኩል ሆኖ እንደሚታይ ተስፋዬ ነው።»
የጀርመን አፍሪቃ ሽልማት መሰጠትከጀመረ ዘንድሮ 24 ዓመት ሆነው።

ኂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic