የጀርመንኛ ቋንቋና ጎተ የባህል ተቋም በኢትዮጵያ | ባህል | DW | 27.08.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

የጀርመንኛ ቋንቋና ጎተ የባህል ተቋም በኢትዮጵያ

በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የኦሎምፒክ ዉድድርን ጨምሮ የዓለምን ሕዝብ የሚያሳትፉ  ብዙ ግዙፍ የመዝናኛም ሆነ የስብሰባ መድረኮች ተሰርዘዋል ። በስረዛዉ መረሃ-ግብርም ኢትዮጵያን ጨምሮ እንዲሁ በርካታ  የዓለም ሃገራት ለምርጫ የያዙትን ቀነ-ቀጠሮ ላልተወሰነ ጊዜ ማራዘማቸዉ ይታወቃል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 16:32

በዓለማችን በ 45 ሃገራት ጀርመንኛ ቋንቋ በስፋት ይነገራል

በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የኦሎምፒክ ዉድድርን ጨምሮ የዓለምን ሕዝብ የሚያሳትፉ  ብዙ ግዙፍ የመዝናኛም ሆነ የስብሰባ መድረኮች ተሰርዘዋል ። በስረዛዉ መረሃ-ግብርም ኢትዮጵያን ጨምሮ እንዲሁ በርካታ  የዓለም ሃገራት ለምርጫ የያዙትን ቀነ-ቀጠሮ ላልተወሰነ ጊዜ ማራዘማቸዉ ይታወቃል።

ይሁንና በዓለም ዙርያ የሚገኘዉ የጀርመኑ የባህል ጎተ ተቋም ማለትም «ጎተ ኢኒስቲቲዩት» የጀርመን ቋንቋ ኦሎምፒክ በሚል በየሁለት ዓመቱ የሚካሄደዉን ዉድድር  በኮሮና ሰበብ አልተቋረጠም። «ዶቼ ኦሎምፒያደ»  የተሰኘዉ የጀርመንኛ ቋንቋ ዉድድር በየሃገራቱ ባሉ የጀርመን የባህል ተቋማት፤ ወጣት ተማሪዎች ዉድድሩን አካሂደዉ በመጨረሻ ወደ ጀርመን መጥተዉ የመጨረሻዉን ዉድድር አድርገዉ አሸናፊዉ ተለይቶአል። ይህ ዶቼ ኦሎምፒያደ የሚባለዉ ዉድድር ግን ምን ይሆን?  በአዲስ አበባ በሚገኘዉ የጀርመኑ የጎተ የባህል ተቋም የቋንቋ ክፍል ዋና ተጠሪ አቶ ኤርሚያስ ገብረየስ ያስረዳሉ።

« የጀርመንኛ ቋንቋን የሚማሩ ወጣቶች የሚወዳደሩበት በየሁለት ዓመቱ የሚደረግ ዝግጅት ነዉ። ወጣቶቹ መጀመርያ በየሃገራቸዉ ዉድድሩን ያካሂዱና ከዝያም የመጨረሻ አሸናፊዎቹ ወደ ጀርመን ለ 15 – 20 ቀናት ግብዣ ወደ ጀርመን መጥተዉ በተለያዩ ዝግጅቶች ላይ ተሳታፊ ይሆናሉ።» 

በታዋቂዉ ጀርመናዊ ገጣሚና ባለቅኔ በዮሃን ዎልፍጋን ፎን ጎተ የተሰየመዉ የጀርመን የባህል ተቋም በተለያዩ የዓለም ሃገራት ቢሮዉን በመክፈት የጀርመንን ባህል እና ቋንቋ ብሎም በሃገራቱ ትስስርና የባህል ልዉዉጥ ላይ ይሰራል። በኢትዮጵያ አዲስ አበባ የሚገኘዉ ይኸዉ የጀርመን የባህል ተቋም «ጎተ ኢንስቲትዮት» በጎርጎረሳዉያኑ 1962 በንጉሱ ዘመን የተቋቋመ ነዉ። በኬንያ ናይሮቢ እንዲሁም አዲስ አበባ ኢትዮጵያ የሚገኙት እነዚህ  ተቋማት ጀርመን የጎተ የባህል ተቋም ስትል በአፍሪቃ ዉስጥ የከፈተቻቸዉ የመጀመርያዎቹ  የባህል ልዉዉጥ ቢሮዎች መሆናቸዉ ተመልክቶአል። በአዲስ አበባ የሚገኘዉ የጀርመኑ የባህል ተቋም በአሁኑ ጊዜ በርካታ የ4ንቋ ተማሪዎችን መዝግቦ ጀርመንኛ ቋንቋ ስልጠና እንደሚሰጥ የቋንቋ ክፍል ኃላፊ አቶ ኤርሚያስ ገብረየስ ተናግረዋል።  

   

የጀርመኑ የባህል ተቋም «ጎተ ኢኒስቲዩት» ፤ ጀርመንን ከኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያን ከአውሮጳ የባህል ልውውጥ እንዲኖር ሲሰራ የቆየና አሁንም በማድረግ ላይ ያለ ተቋም ነዉ። ጎተ ኢንስቲቲዩት የጀርመንን ባህል ቋንቋ ለማስፋፋት እና በሁለቱ አገሮች መካከል የባህል ልዉዉጦች ያጠናክራል ባሕላዊ ክንውኖችን በሰፊ ይደግፋልም።የአዲስ አበባዉ የጎተ የባህል ተቋም ዉስጥ የጀርመንኛ ቋንቋን የሚማሩት ኢትዮጵያዉያን ብቻ አይደሉም። ሶማልያዉያን ኤርትራዉያን እና የጅቡቲ ዜጎችም በብዛት እንዳሉም አቶ ኤርሚስ ተናግረዋል።

ጀርመንኛ ቋንቋ በአዉሮጳ ዉስጥ በጀርመን በኦስትርያ እና በሊሽተንሽታይን በምትባለዉ ትንሽዋ የአዉሮጳ ሃገር ዉስጥ ይፋዊ የስራ እና የመግባብያ ቋንቋ ነዉ። 38 ሺህ ሕዝብ ያላት ትንሽዋ የአዉሮጳ ሃገር ሊሽተንሽታይን በኦስትርያ እና በስዊዘርላን መካከል የምትገኝ ሃገር ስትሆን 35 ሺህ የሚሆነዉ ሕዝቧ  የጀርመን ቋንቋ ተናጋሪ ነዉ። በኦስትርያም 7, 5 ሚሊዮን ሕዝብ ጀርመንኛን ይናገራል። በጀርመንም ከ 80 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ጀርመንኛ ቋንቋን ይናገራል። በስዊዘርላንድ ከጣልያንኛ ከፈረንሳይኛና የሃገሪዉ የትዉልድ ቋንቋ ተብሎ ከሚጠራዉ ከሮማን ቋንቋ በተጨማሪ ጀርመንኛ ቋንቋ ይፋዊ የስራ ቋንቋ ነዉ። በላክሰንበርግም እንዲሁ ጀርመንኛ ቋንቋ ከጎርጎረሳዉያኑ 1984 ጀምሮ ይፋዊ የስራ ቋንቋ ሆንዋል።  ከ 600 ሺህ ነዋሪ መካከል ወደ 470 ሺዉ የጀርመንኛ ቋንቋ ተናጋሪ ነዉ። ከ 11 ሚሊዮን በላይ ነዋሪ ባላት ቤልጂየምም ወደ 75 ሺህዉ ሕዝብ የጀርመንኛ ቋንቋ ተናጋሪ በመሆኑ ፤ በሃገሪቱ ከደች እና ከፈረንሳይኛ ቋንቋ ቀጥሎ ጀርመንኛ ይፋዊ የስራ ቋንቋ ነዉ። አዲስ አበባ የሚገኘዉ የጎተ ተቋም በዓለማችን የኮሮና ወረርሽኝ መስፋፋት ከጀመረ በኋላ የቋንቋ ትምህርቱን በኢንተርኔ በመታገዝ መስጠቱን ቀጥሎአል።    

      

በዓለማችን በ 45 ሃገራት ጀርመንኛ ቋንቋ በስፋት ይነገራል። በጣልያን ደቡባዊ ቲሮል፤ እና በፈረንሳይ ጀርመን ድንበር  ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ነዋሪዎች የጀርመንኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ናቸዉ። ጀርመናዉያን ለእረፍት የሚጓዙባት ስፔንም በአሁኑ ጊዜ ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆን ሕዝብ የጀርመንኛ ቋንቋ ተናጋሪ ሆንዋል።  ብዙ ጀርመናዉያንም የመኖርያ  ስፍራቸዉን በስፔን የተለያዩ ግዛቶች ሲያደርጉ ይታያል። በኔዘርላንድና ጀርመን ድንበር ላይ ወደ 360 ሺህ የሚሆን ሕዝብ እንዲሁ የጀርመንኛ ቋንቋ ተናጋሪ ነዉ። በኔዘርላንድ የጀርመን ቋንቋ እንደ ከእንጊሊዘኛ ሁሉ በትምህርት መልክ ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ የሚሰጥ የትምህርት አይነት ነዉ።   በአየርላንድ 100 ሺህ የሚሆን ሕዝብ በእስራኤልም እንዲሁ  100 ሺህ የሚሆን ሕዝብ የጀርመን ተናጋሪ ነዉ። በሩስያ የጀርመንኛ ቋንቋ ከ 250 ዓመት በላይ ታሪክ አለዉ። ታላቅዋ ኢካቴሪና  የምትባለዉ ሩስያዊትዋ ንግስት በጎርጎረሳዉያኑ 1763 ለአንድ ሺህ ጀርመናዉያን ገበሪዎችን ሩስያ ዉስጥ ቮልጋ ወንዝ ዳርቻ ቦታ ሰጥታ አስፋ ራቸዉ እንደነበር የታሪክ መዝገባት ያሳያሉ። ከጀርመን ዉህደት ወዲህ ማለት ከጎርጎረሳዉያኑ 1990 ዓመት ጀምሮ 2,3 ሚሊዮን የሩስያ ጀርመናዉያን ወደ ሃገራቸዉ ጀርመን ተመልሰዋል። እንደ አንዳንድ መረጃዎች አሁንም ሩስያ ዉስጥ ወደ 390 ሺህ ጀርመናዉያን ይኖራሉ።

ይሁንና ሁሉም ጀርመንኛ ቋንቋን መናገር አይችሉም። በሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ወቅት ወደ 444ሺህ የሚሆኑ ጀርመናዉያን ወደ ካዛኪስታን ተጠርዘዋል። ቅጣት መሆኑ ነዉ ። ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት በፊት ወደ 92 ሺህ ጀርመናዉያን እዝያዉ ካዛኪስታን ዉስጥ ይኖሩ ነበር። በአሁኑ ወቅት ሁለት ሦስተናዉ የካዛኪስታን ነዋሪ ማለትም 350 ሺህ የካዛኪስታን ነዋሪ ጀርመንኛ ቋንቋን ይናገራል።  ጀርመናዉያን ደቡብ አፍሪቃን ለመኖርያ የሚመርጡዋት ሃገር ናት። በኬፕታዉን የጀርመን መንደር የሚባል በርካታ ጀርመናዉያን የሚኖሩበት ሰፈርም አለ ተብሎአል።   በደቡብ አፍሪቃ ከ 100 እስከ 500 ሺህ ትዉልደ ጀርመናዉያን እንዳሚገኙ ይገመታል። በጀርመን የቀድሞ ቅኝ ግዛት ሃገር በሆነችዉ ናሚቢያ ደግሞ 20 ሺህ ሕዝብ ጀርመንኛ ቋንቋን ተናጋሪ ነዉ። በሃገሪቱ በበርካታ ትምህርት ቤቶች ጀርመንኛ ቋንቋ በትምህርት መልክ ይሰጣል። በደቡብ አሜሪካ ማለትም በብራዚል፤ አርጄንቲና ኡራጉዋይ ፤ በጥንት ጊዜ የፈለሱ ጀርመናዉያን ትዉልድን  ተክተዋል፤ ቋንቋዉንም የሚናገረዉ ነዋሪ መጠን ጥቂት የሚባል አይደለም። በዩናትድ ስቴትስ ካናዳም በርካታ ጀርመናዉያን ለኑሮ የሚመርጡዋቸዉ ሃገራት  በመኖኑ በየሃገራቱ የቋንቋዉ ተናጋሪ ቀላል የሚባል አይደለም።

በአዲስ አበባ በጀርመን የጎተ ባህል ተቋም የቋንቋ ክፍል ኃላፊ አቶ ኤርሚያስ ገብረየስ ለሰጡን ቃለ ምልልስ በዶቼ ቬለ ስም እያመሰገንን ሙሉ ቃለ-ምልልሱን እንዲያደምጡ እንጋብዛለን።  

አዜብ ታደሰ

እሸቴ በቀለ

Audios and videos on the topic